የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ትንቢተ ኢሳይያስ 27

27
1በዚያም ቀን እግዚአብሔር ፈጣኑን እባብ ሌዋታንን ጠማማውንም እባብ ሌዋታንን በጠንካራ በታላቅም በብርቱም ሰይፍ ይቀጣል፥ በባሕርም ውስጥ ያለውን ዘንዶ ይገድላል። 2በዚያም ቀን ለተወደደው የወይን ቦታ ተቀኙለት። 3እኔ እግዚአብሔር ጠባቂው ነኝ፥ ሁልጊዜ አጠጣዋለሁ፥ ማንም እንዳይጎዳው በሌሊትና በቀን እጠብቀዋለሁ። 4አልቈጣም፥ እሾህና ኵርንችት በእኔ ላይ ምነው በሰልፍ በነበሩ! በእነርሱ ላይ ተራምጄ በአንድነት ባቃጠልኋቸው ነበር። 5ወይም ጕልበቴን ይያዝ፥ ከእኔ ጋር ሰላም ያድርግ፥ ከእኔ ጋር ሰላም ያድርግ። 6በሚመጣው ዘመን ያዕቆብ ሥር ይሰድዳል፥ እስራኤልም ያብባል ይጨበጭብማል፥ በፍሬያቸውም የዓለሙን ፊት ይሞላሉ። 7በውኑ የመቱትን እንደ መታ እንዲሁ እርሱን መታውን? ወይስ እነርሱ እንደ ተገደሉበት መገደል እርሱ ተገድሎአልን? ነዳቸው ሰደዳቸው ቀሰፋቸው፥ 8የምሥራቅ ነፋስ እንደሚነፍስበት ቀን በጠንካራ ዐውሎ አስወገዳቸው። 9ስለዚህም የማምለኪያ ዐፀዶችና የፀሐይ ምስሎች ዳግመኛ እንዳይነሡ የመሠዊያውን ድንጋይ ሁሉ እንደ ደቀቀ እንደ ኖራ ድንጋይ ባደረገ ጊዜ፥ እንዲሁ የያዕቆብ በደል ይሰረያል፥ ይህም ኃጢአትን የማስወገድ ፍሬ ሁሉ ነው። 10የተመሸገችው ከተማ ብቻዋን ሆነች፥ እንደ ምድረ በዳ ሆና የተፈታችና የተተወች መኖሪያ ናት፥ በዚያም ጥጃ ይሰማራል በዚያም ይተኛል ቅርንጫፍዋንም ይበላል። 11ጫፎችዋ በደረቁ ጊዜ ይሰበራሉ፥ ሴቶችም መጥተው ያቃጥሉአቸዋል፥ የማያስተውል ሕዝብ ነውና ስለዚህ ፈጣሪው አይራራለትም ሠሪውም ምሕረት አያደርግለትም። 12በዚያም ቀን እንዲህ ይሆናል፥ እግዚአብሔር ከወንዝ ፈሳሽ ጀምሮ እስከ ግብጽ ወንዝ ድረስ እህሉን ይወቃል፥ እናንተም የእስራኤል ልጆች ሆይ፥ አንድ በአንድ ትሰበሰባላችሁ። 13በዚያም ቀን እንዲህ ይሆናል፥ ታላቅ መለከት ይነፋል፥ በአሦርም የጠፉ፥ በግብጽ ምድርም የተሳደዱ ይመጣሉ፥ በተቀደሰውም ተራራ በኢየሩሳሌም ለእግዚአብሔር ይሰግዳሉ።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ