የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ትንቢተ ኢሳይያስ 26

26
1በዚያም ቀን ይህ ቅኔ በይሁዳ ምድር ይዘመራል፦ የጸናች ከተማ አለችን፥ ለቅጥርና ለምሽግ መድኃኒትን ያኖርባታል። 2እውነትን የሚጠብቅ ጻድቅ ሕዝብ ይገባ ዘንድ በሮችን ክፈቱ። 3በአንተ ላይ ታምናለችና በአንተ ለምትደገፍ ነፍስ ፈጽመህ በሰላም ትጠብቃታለህ። 4ጌታ እግዚአብሔር የዘላለም አምባ ነውና ለዘላለም በእግዚአብሔር ታመኑ። 5በከፍታ የሚኖሩትን ሰዎች ዝቅ ያደርጋል፥ ከፍ ያለችውን ከተማ ያዋርዳል፥ እስከ መሬትም ድረስ ያወርዳታል፥ እስከ አፈርም ድረስ ይጥላታል። 6እግር፥ የድሀ እግርም የችግረኛም አረጋገጥ፥ ትረግጣታለች። 7የጻድቃን መንገድ ቅን ናት፥ አንተ ቅን የሆንህ የጻድቃንን መንገድ ታቀናለህ። 8አቤቱ፥ በፍርድህ መንገድ ተስፋ አድርገንሃል፥ ስምህንም መታሰቢያህም የነፍሳችን ምኞት ነው። 9ፍርድህን በምድር ባደረግህ ጊዜ በዓለም የሚኖሩ ጽድቅን ይማራሉና ነፍሴ በሌሊት ትናፍቅሃለች፥ መንፈሴም በውስጤ ወደ አንተ ትገሠግሣለች። 10ለኃጢአተኛ ሞገስ ቢደረግለት ጽድቅን አይማርም፥ በቅኖች ምድር ክፉን ነገር ያደርጋል፥ የእግዚአብሔርንም ግርማ አያይም። 11አቤቱ፥ እጅህ ከፍ ከፍ አለች አላዩምም፥ ነገር ግን በሕዝብህ ላይ ያለህን ቅንዓት አይተው ያፍራሉ፥ እሳትም ጠላቶችህን ትበላለች። 12አቤቱ፥ ሥራችንን ሁሉ ሠርተህልናልና ሰላምን ትሰጠናለህ። 13አቤቱ አምላካችን ሆይ፥ ከአንተ በቀር ሌሎች ጌቶች ገዝተውናል፥ ነገር ግን በአንተ ብቻ ስምህን እናስባለን። 14እነርሱ ሞተዋል፥ በሕይወት አይኖሩም፥ ጠፍተዋል፥ አይነሡም፥ ስለዚህ አንተ ጎብኝተሃቸዋል አጥፍተሃቸውማል፥ መታሰቢያቸውንም ሁሉ ምን ምን አድርገሃል። 15ሕዝብን አበዛህ፥ አቤቱ፥ ሕዝብን አበዛህ፥ አንተም ተከበርህ፥ የአገሪቱንም ዳርቻ ሁሉ አሰፋህ። 16አቤቱ፥ በመከራ ጊዜ ፈለጉህ፥ በገሠጽሐቸውም ጊዜ ልመናቸውን ወደ አንተ አፈሰሱ። 17የፀነሰች ሴት ለመውለድ ስትቀርብ እንደምትጨነቅና በምጥ አንደምትጮኽ፥ አቤቱ፥ እንዲሁ በፊትህ ሆነናል። 18እኛ ፀንሰናል ምጥም ይዞናል፥ ነፋስንም እንደምንወልድ ሆነናል፥ በምድርም ደኅንነት አላደረግነም፥ በዓለምም የሚኖሩ ይወድቃሉ። 19ሙታንህ ሕያዋን ይሆናሉ፥ ሬሳዎችም ይነሣሉ። በምድር የምትኖሩ ሆይ፥ ጠልህ የብርሃን ጠል ነውና፥ ምድርም ሙታንን ታወጣለችና ንቁ ዘምሩም። 20ሕዝቤ ሆይ፥ ና ወደ ቤትህም ግባ፥ ደጅህን በኋላህ ዝጋ፥ ቍጣ እስኪያልፍ ድረስ ጥቂት ጊዜ ተሸሸግ። 21በምድር በሚኖሩት ላይ በበደላቸው ምክንያት ቍጣውን ያመጣባቸው ዘንድ፥ እነሆ፥ እግዚአብሔር ከስፍራው ይወጣል፥ ምድርም ደምዋን ትገልጣለች፥ ሙታኖችዋንም ከእንግዲህ ወዲህ አትከድንም።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ