ትንቢተ ኢሳይያስ 25
25
1አቤቱ፥ አንተ አምላኬ ነህ፥ ድንቅን ነገር የዱሮ ምክርን በታማኝነትና በእውነት አድርገሃልና ከፍ ከፍ አደርግሃለሁ ስምህንም አመሰግናሁ። 2ከተማይቱን የድንጋይ ክምር፥ የተመሸገችውን ከተማ ውድማ እንድትሆን፥ የኀጥኣንንም አዳራሽ ከተማ እንዳትሆን አድርገሃል፥ ከቶ አትሠራም። 3ስለዚህ ኃያላኑ ወገኖች ያከብሩሃል፥ የጨካኞች አሕዛብ ከተማም ትፈራሃለች። 4የጨካኞችም ቍጣ እስትንፋስ ቅጥርን እንደሚመታ ዐውሎ ነፋስ በሆነ ጊዜ፥ ለድሀው መጠጊያ፥ ለችግረኛው በጭንቁ ጊዜ መጠጊያ፥ ከውሽንፍር መሸሸጊያ ከሙቀትም ጥላ ሆነሃል። 5እንደ ሙቀት በደረቅ ስፍራ የኀጥአንን ጩኸት ዝም ታሰኛለህ፥ ሙቀትም በደመና ጥላ እንዲበርድ እንዲሁ የጨካኞች ዝማሬ ይዋረዳል። 6የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔርም ለሕዝብ ሁሉ በዚህ ተራራ ላይ ታላቅ የሰባ ግብዣ፥ ያረጀ የወይን ጠጅ፥ ቅልጥም የሞላባቸው የሰቡ ነገሮች፥ የጥሩና ያረጀ የወይን ጠጅ ግብዣ ያደርጋል። 7በዚህም ተራራ ላይ በወገኖች ሁሉ ላይ የተጣለውን መጋረጃ፥ በአህዛብም ሁሉ ላይ የተዘረጋውን መሸፈኛ ያጠፋል። 8ሞትን ለዘላለም ይውጣል፥ ጌታ እግዚአብሔርም ከፊት ሁሉ እንባን ያብሳል፥ የሕዝቡንም ስድብ ከምድር ሁሉ ላይ ያስወግዳል፥ እግዚአብሔር ተናግሮአልና። 9በዚያም ቀን፦ እነሆ፥ አምላካችን ይህ ነው፥ ተስፋ አድርገነዋል፥ ያድነንማል፥ እግዚአብሔር ይህ ነው፥ ጠብቀነዋል፥ በማዳኑ ደስ ይለናል ሐሤትም እናደርጋለን ይባላል። 10የእግዚአብሔርም እጅ በዚህ ተራራ ላይ ታርፋለች፥ ጭድም በጭቃ ውስጥ እንደሚረገጥ እንዲሁ ሞዓብ በሥፍራው ይረገጣል። 11ዋናተኛም ሲዋኝ እጁን እንደሚዘረጋ፥ እንዲሁ በመካከሉ እጁን ይዘረጋል፥ ነገር ግን እግዚአብሔር ትዕቢቱን ከእጁ ተንኮል ጋር ያዋርዳል። 12የተመሸገውንም ከፍ ከፍ ያለውንም ቅጥርህን ዝቅ ያደርገዋል፥ ያዋርደውማል፥ ወደ መሬትም እስከ አፈር ድረስ ይጥለዋል።
Currently Selected:
ትንቢተ ኢሳይያስ 25: አማ54
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ