የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ትንቢተ ኢሳይያስ 24

24
1እነሆ፥ እግዚአብሔር ምድርን ባዶ ያደርጋታል፥ ባድማም ያደርጋታል፥ ይገለብጣትማል፥ በእርስዋም የተቀመጡትን ይበትናል። 2እንደ ሕዝቡም እንዲሁ ካህኑ፥ እንደ ባሪያውም እንዲሁ ጌታው፥ እንደ ባሪያይቱም እንዲሁ እመቤትዋ፥ እንደሚገዛም እንዲሁ የሚሸጠው፥ እንደ አበዳሪውም እንዲሁ ተበዳሪው፥ እንደ ዕዳ አስከፋዩም እንዲሁ ዕዳ ከፋዩ ይሆናል። 3ምድር መፈታትን ትፈታለች፥ ፈጽማም ትበላሻለች፥ እግዚአብሔር ይህን ቃል ተናግሮአልና። 4ምድርም አለቀሰች ረገፈችም፥ ዓለም ደከመች ረገፈችም፥ የምድርም ሕዝብ ታላላቆች ደከሙ። 5ምድርም ከሚቀመጡባት በታች ረክሳለች፥ ሕጉን ተላልፈዋልና፥ ሥርዓቱንም ለውጠዋልና፥ የዘላለሙንም ቃል ኪዳን አፍርሰዋልና። 6ስለዚህ መርገም ምድርን ትበላለች በእርስዋም የተቀመጡ ይቀጣሉ፥ ስለዚህ የምድር ሰዎች ይቃጠላሉ ጥቂት ሰዎችም ይቀራሉ። 7የወይን ጠጅ አለቀሰች፥ የወይን ግንድ ደከመች፥ ልባቸው ደስ ያለው ሁሉ ተከዙ። 8የከበሮው ሐሤት ቀርቷል፥ የደስተኞች ድምጽ ዝም ብሏል፥ የመሰንቆ ደስታ ቀርቶአል። 9እየዘፈኑም የወይን ጠጅን አይጠጡትም፥ የሚያሰክር መጠጥ ለሚጠጡት መራራ ይሆናል። 10ባድማ የሆነችው ከተማ ፈረሰች፥ ማንም እንዳይገባበት ተዘጋ። 11ስለ ወይኑም ጠጅ በአደባባይ ጩኸት ይሆናል፥ ደስታ ሁሉ ጨልሞአል፥ የምድርም ሐሤት ፈርሶአል። 12ከተማይቱም ባድማ ሆናለች፥ በርዋም በጥፋት ተመትቶአል። 13የወይራን ዛፍ እንደ መምታት፥ ከወይንም መከር በኋላ ቃርሚያውን እንደ መልቀም፥ እንዲሁ በምድር መካከል በአሕዛብም መካከል ይሆናል። 14እነዚህ ድምፃቸውን ያነሣሉ፥ እልልም ይላሉ፥ ስለ እግዚአብሔር ክብርም ከባሕር ይጣራሉ። 15ስለዚህ እግዚአብሔርን በምሥራቅ፥ የእስራኤልንም አምላክ የእግዚአብሔርንም ስም በባሕር ደሴቶች አክብሩ። 16ለጻድቁ ክብር ይሁን የሚለውን ዝማሬ ከምድር ዳርቻ ሰምተናል። እኔ ግን፦ ከሳሁ፥ ከሳሁ፥ ወዮልኝ! ወንጀለኞች ወንጅለዋል፥ ወንጀለኞች እጅግ ወንጅለዋል አልሁ። 17በምድር ላይ የምትኖር ሆይ፥ ፍርሃትና ገደል ወጥመድም በአንተ ላይ አሉ። 18የሰማይ መስኮቶች ተከፍተዋልና፥ የምድርም መሠረት ተናውጣለችና ከፍርሃት ድምጽ የሸሸ በገደል ይወድቃል፥ ከገ ደልም የወጣ በወጥመድ ይያዛል። 19ምድር ተሰባበረች፥ ምድር ፈጽማ ደቀቀች፥ ምድር ተነዋወጠች። 20ምድር እንደ ሰካር ሰው ትንገዳገዳለች፥ እንደ ዳስም ትወዛወዛለች፥ መተላለፍዋ ይከብድባታል፥ ትወድቅማለች ደግማም አትነሣም። 21በዚያም ቀን እንደዚህ ይሆናል፥ እግዚአብሔር በከፍታ ያለውን ሠራዊት በከፍታ ላይ፥ በምድርም ያሉትን ነገሥታት በምድር ላይ ይቀጣቸዋል። 22ግዞተኞች በጕድጓድ እንደሚከማቹ በአንድነት ይከማቻሉ፥ በግዞት ቤትም ውስጥ ተዘግተው ይኖራሉ፥ ከብዙ ቀንም በኋላ ይጎበኛሉ። 23የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔርም በጽዮን ተራራና በኢየሩሳሌም ላይ ይነግሣልና፥ በሽማግሌዎቹም ፊት ክብር ይሆናልና ጨረቃ ይታወካል ፀሐይም ያፍራል።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ