የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ትንቢተ ሆሴዕ 8

8
1መለከትን ወደ አፍህ አቅርብ፥ ቃል ኪዳኔን ተላልፈዋልና፥ በሕጌም ላይ ዐምፀዋልና በእግዚአብሔር ቤት ላይ እንደ ንስር ይመጣል። 2እነርሱም፦ አምላክ ሆይ፥ እኛ እስራኤል አወቅንህ ብለው ወደ እኔ ይጮኻሉ። 3እስራኤል ደግነትን ጥሎአል፥ ጠላትም ያሳድዱታል። 4ለራሳቸው ነገሥታትን አነገሡ፥ ከእኔም ዘንድ አይደለም፥ አለቆችንም አደረጉ፥ እኔም አላወቅሁም፥ ለጥፋታቸውም ከብራቸውና ከወርቃቸው ጣዖታትን ለራሳቸው አደረጉ። 5ሰማርያ ሆይ፥ እምቦሳህን፥ ጥሎአል፥ ቍጣዬ በላያቸው ነድዶአል፥ እስከ መቼ ድረስ ንጹሕ ሊሆኑ አይችሉም? 6ይህ ደግሞ ከእስራኤል ዘንድ ነው፥ ሠራተኛ ሠራው፥ እርሱም አምላክ አይደለም፥ የሰማርያም እምቦሳ ይቈራረጣል። 7ነፋስን ዘርተዋል፥ ዐውሎ ነፋስንም ያጭዳሉ፥ አገዳ የለውም፥ ከፍሬውም ዱቄት አይገኝም፥ ቢገኝም እንግዶች ይበሉታል።
8እስራኤል ተውጦአል፥ በአሕዛብ መካከል ዛሬ እንደ ረከሰ ዕቃ ሆኖአል። 9ለብቻውም እንደሚቀመጥ እንደ ምድረ በዳ አህያ ወደ አሦር ወጥተዋል፥ ኤፍሬምም ወዳጆቹን በእጅ መንሻ ገዛ። 10ነገር ግን ለአሕዛብ እጅ መንሻ ቢሰጡ እኔ አሁን እሰበስባቸዋለሁ፥ ከንጉሥና ከአለቆችም ሸክም የተነሣ ይደክማሉ።
11ኤፍሬም ኃጢአትን ለመሥራት መሠዊያ አብዝቶአልና መሠዊያ ለኃጢአት ይሆንለታል። 12የሕጌን ብዛት ጽፌለታለሁ፥ እነርሱ ግን እንደ እንግዳ ነገር ቈጥረውታል። 13መሥዋዕቴን ያቀርባሉ፥ ሥጋንም ያርዳሉ፥ ይበላሉም፥ እግዚአብሔር ግን አይቀበላቸውም፥ በደላቸውንም ያስባል፥ ኃጢአታቸውንም ይቀጣል፥ እነርሱም ወደ ግብጽ ይመለሳሉ። 14እስራኤል ፈጣሪውን ረስቶአል፥ መስገጃዎችንም ሠርቶአል፥ ይሁዳም የተመሸጉትን ከተሞች አብዝቶአል፥ እኔ ግን በከተሞች ላይ እሳት እሰድዳለሁ፥ አዳራሾችንም ትበላለች።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ