ትንቢተ ሆሴዕ 9
9
1እስራኤል ሆይ፥ ከአምላክህ ተለይተህ አመንዝረሃልና እንደ አሕዛብ ደስ አይበልህ፥ ሐሴትንም አታድርግ፥ በእህሉ አውድማ ሁሉ ላይ የግልሙትናን ዋጋ ወድደሃል። 2አውድማውና መጥመቂያው አይመግባቸውም፥ ጉሽ ጠጅም ይጐድልባታል። 3በእግዚአብሔር ምድር ላይ አይቀመጡም፥ ኤፍሬምም ወደ ግብጽ ይመለሳል፥ በአሦርም ርኵስን ነገር ይበላሉ። 4ለእግዚአብሔርም የወይን ጠጅን ቍርባን አያፈስሱም፥ መሥዋዕታቸውም ደስ አያሰኘውም፥ የኀዘንም እንጀራ ይሆንላቸዋል፥ የሚበላውም ሁሉ ይረክሳል፥ እንጀራቸውም ለሰውነታቸው ይሆናል እንጂ ወደ እግዚአብሔር ቤት አይገባም። 5በዓመት በዓል ቀንና በእግዚአብሔር በዓል ቀን ምን ታደርጋላችሁ? 6እነሆ፥ ከጥፋት ሸሽተው ሄዱ፥ ግብጽም ትሰበስባቸዋለች፥ ሜምፎስም ትቀብራቸዋለች፥ ሳማም የብራቸውን ጌጥ ይወርሳል፥ እሾህም በድንኳኖቻቸው ውስጥ ይበቅላል። 7የበቀል ወራት መጥቶአል፥ የፍዳም ወራት ደርሶአል፥ እስራኤልም ያውቃል፥ ከኃጢአትህና ከጠላትነትህ ብዛት የተነሣ ነቢዩ ሰንፎአል፥ መንፈስም ያለበት ሰው አብዶአል። 8ኤፍሬም ከአምላኬ ጋር ተመልካች ነበረ፥ አሁን ግን ነቢዩ በመንገዱ ሁሉ ላይ የወፍ ወጥመድ ሆነ፥ በአምላኩም ቤት ጠላትነት አለ። 9በጊብዓ ዘመን እንደ ነበረ እጅግ ረከሱ፥ እርሱም በደላቸውን ያስባል፥ ኃጢአታቸውንም ይበቀላል።
10እስራኤልን በምድረ በዳ እንዳለ ወይን ሆኖ አገኘሁት፥ አባቶቻችሁንም ከመጀመሪያዋ ዓመት እንደ በለስ በኵራት ሆነው አየኋቸው፥ እነርሱ ግን ወደ ብዔልፌጎር መጡ፥ ለነውርም ተለዩ፥ እንደ ወደዱትም ርኩስ ሆኑ፥ 11የኤፍሬምም ክብር እንደ ወፍ በርሮ ይጠፋል፥ መውለድና መፅነስ ማርገዝም አይሆንላቸውም። 12ልጆቻቸውንም ቢያሳድጉ ሰው እንዳይቀርላቸው ልጅ አልባ አደረጋቸዋለሁ፥ ከእነርሱም በራቅሁ ጊዜ ወዮላቸው! 13እኔ እንዳየሁ የኤፍሬም ልጆች ለምርኮ ተሰጥተዋል፥ ኤፍሬምም ልጆቹን ወደ ገዳዩች ያወጣል። 14አቤቱ፥ ስጣቸው፥ ምን ትሰጣቸዋለህ? የሚጨነግፍን ማኅፀን የደረቀውንም ጡት ስጣቸው። 15ክፋታቸው ሁሉ በጌልገላ አለ፥ በዚያ ጠልቻቸዋለሁ፥ ስለ ሠሩት ክፋት ከቤቴ አሳድዳቸዋለሁ፥ ከእንግዲህ ወዲያ አልወድዳቸውም፥ አለቆቻቸው ሁሉ ዓመፀኞች ናቸው። 16ኤፍሬም ተመታ፥ ሥሩም ደረቀ፥ ፍሬም አያፈራም፥ ደግሞም ቢወልዱ የማኅፀናቸውን ፍሬ እገድላለሁ። 17አልሰሙትምና አምላኬ ይጥላቸዋል፥ በአሕዛብም መካከል ተቅበዝባዦች ይሆናሉ።
Currently Selected:
ትንቢተ ሆሴዕ 9: አማ54
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ