ትንቢተ ሆሴዕ 7
7
1በሐሰት አድርገዋልና፥ ሌባም ገብቶአልና፥ በውጭም ወንበዴዎች ቀምተዋልና እስራኤልን እፈውስ ዘንድ በወደድሁ ጊዜ የኤፍሬም ኃጢአትና የሰማርያ ክፋት ተገለጠ። 2እኔም ክፋታቸውን ሁሉ እንዳሰብሁ በልባቸው አያስቡም፥ አሁንም ሥራቸው ከብባቸዋለች፥ በፊቴም አለች። 3ንጉሡን በክፋታቸው፥ አለቆቹንም በሐሰታቸው ደስ አሰኝተዋል። 4ሁሉም አመንዝራዎች ናቸው፥ ጋጋሪ እንደሚያነድድበት እንደ ምድጃ ናቸው፥ ሁሉ እስኪቦካ ድረስ እሳትን መቈስቈስና እርሾን መለወስ ይቆያል። 5በንጉሣችን ቀን አለቆች ከወይን ጠጅ ሙቀት የተነሣ ታመሙ፥ እርሱም ከዋዘኞች ጋር እጁን ዘረጋ። 6እያደቡ ልባቸውን እንደ ምድጃ አዘጋጅተዋል፥ አበዛቸውም ሌሊቱን ሁሉ አንቀላፋ፥ በጠባም ጊዜ እንደ እሳት ነበልባል ይነድዳል። 7ሁሉም እንደ ምድጃ ግለዋል፥ ፈራጆቻቸውንም በሉ፥ ነገሥታቶቻቸውም ሁሉ ወደቁ፥ ከእነርሱም ወደ እኔ የሚጮኽ የለም።
8ኤፍሬም ከአሕዛብ ጋር ተደባለቀ፥ ኤፍሬም እንዳልተገላበጠ ቂጣ ነው። 9እንግዶች ጕልበቱን በሉት፥ እርሱም አላወቀም፥ ሽበትም ወጣበት፥ እርሱም አላወቀም። 10የእስራኤልም ትዕቢት በፊቱ መሰከረ፥ ወደ አምላካቸው ወደ እግዚአብሔር ግን አልተመለሱም፥ በዚህም ሁሉ አልፈለጉትም። 11ኤፍሬምም አእምሮ እንደሌላት እንደ ሰነፍ ርግብ ነው፥ ግብጽን ጠሩ፥ ወደ አሦርም ሄዱ። 12ሲሄዱ አሽክላዬን እዘረጋባቸዋለሁ፥ እንደ ሰማይ ወፎች አወርዳቸዋለሁ፥ መከራቸውን ሲሰሙ እገሥጻቸዋለሁ። 13ከእኔ ፈቀቅ ብለዋልና ወዮላቸው! በእኔም ላይ ዐምፀዋልና ጥፋት ይምጣባቸው! እኔ ልታደጋቸው ወደድሁ፥ እነርሱ ግን በሐሰት ተናገሩብኝ። 14በመኝታቸው ላይ ሆነው ያለቅሱ ነበር እንጂ በልባቸው ወደ እኔ አልጮኹም፥ ስለ እህልና ስለ ወይን ጠጅ ይሰበሰቡ ነበር፥ በእኔም ላይ ዐመፁ። 15እኔም ክንዳቸውን አስተማርሁና አጸናሁ፥ እነርሱ ግን ክፉ ነገርን መከሩብኝ። 16ወደ ከንቱ ነገር ተመለሱ፥ እንደ ተንኰለኛ ቀስት ሆኑ፥ አለቆቻቸው ከምላሳቸው ቍጣ የተነሣ በሰይፍ ይወድቃሉ፥ ይህ በግብጽ ምድር ውስጥ መሳለቂያ ይሆንባቸዋል።
Currently Selected:
ትንቢተ ሆሴዕ 7: አማ54
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ