የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ትንቢተ ሆሴዕ 5

5
1ካህናት ሆይ፥ ይህን ስሙ የእስራኤል ቤት ሆይ፥ አድምጡ፥ የንጉሥ ቤት ሆይ፥ ልብ አድርጉ፥ በምጽጳ ላይ ወጥመድ፥ በታቦርም ላይ የተዘረጋ አሽክላ ሆናችኋልና ፍርድ በእናንተ ላይ ነው። 2ዓመፀኞችም እርድ አብዝተዋል፥ እኔ ግን እነዚያን ሁሉ እዘልፋለሁ። 3ኤፍሬምን አውቀዋለሁ፥ እስራኤልም ከእኔ አልተሰወረም፥ ኤፍሬም ሆይ፥ ዛሬ አመንዝረሃል፥ እስራኤልም ረክሶአል። 4ወደ አምላካቸው ይመለሱ ዘንድ ሥራቸውን አላቀኑም፥ የግልሙትና መንፈስ በውስጣቸው አለና፥ እግዚአብሔርንም አላውቁምና። 5የእስራኤልም ትዕቢት በፊቱ ይመሰክራል፥ ስለዚህ እስራኤልና ኤፍሬም በኃጢአታቸው ይሰናከላሉ፥ ይሁዳም ደግሞ ከእነርሱ ጋር ይሰናከላል። 6እግዚአብሔርንም ለመሻት በጎቻቸውንና ላሞቻቸውን ነድተው ይሄዳሉ፥ ነገር ግን እርሱ ከእነርሱ ተመልሶአልና አያገኙትም። 7ዲቃሎችን ልጆች ወልደዋልና እግዚአብሔርን ወንጅለዋል፥ አሁንም አንድ ወር እነርሱንና ርስታቸውን ይበላቸዋል።
8በጊብዓ መለከትን፥ በራማ እንቢልታን ንፉና፦ ብንያም ሆይ፥ ከአንተ በኋላ እያላችሁ በቤትአዌን ላይ እሪ በሉ። 9ኤፍሬም በዘለፋ ቀን የፈረሰ ይሆናል፥ በእስራኤል ነገዶች ዘንድ በእርግጥ የሚሆነውን ነገር ገልጫለሁ። 10የይሁዳ አለቆች ድምበርን እንደሚነቅሉ ሆነዋል፥ እኔም መዓቴን እንደ ውኃ አፈስስባቸዋለሁ። 11ኤፍሬም ከትእዛዝ በኋላ መሄድን ወድዶአልና የተገፋና በፍርድ የተጐዳ ሆኖአል። 12እኔም ለኤፍሬም እንደ ብል፥ ለይሁዳም ቤት እንደ ነቀዝ ሆኜአለሁ። 13ኤፍሬምም ደዌውን፥ ይሁዳም ቍስሉን ባየ ጊዜ ኤፍሬም ወደ አሦር ሄደ ወደ ንጉሡም ወደ ኢያሪም መልእክተኛን ላከ፥ እርሱ ግን ይፈውሳችሁ ዘንድ፥ ከቍስላችሁም ያድናችሁ ዘንድ አልቻለም። 14እኔም ለኤፍሬም እንደ አንበሳ፥ ለይሁዳም ቤት እንደ አንበሳ ደቦል እሆናለሁና፥ እኔም ነጥቄ እሄዳለሁ እወስድማለሁ፥ የሚያድንም አይገኝም። 15በደላቸውንም እስኪያውቁ ድረስ፥ ፊቴንም እስኪሹ ድረስ ሄጄ ወደ ስፍራዬ እመለሳለሁ፥ በመከራቸው ጊዜ እጅግ አድርገው ፊቴን ይፈልጋሉ።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ