ኦሪት ዘፍጥረት 40
40
1ከዚህ ነገር በኍላም እንዲህ ሆነ የግብፅ ንጉሥ የጠጅ አሳላፊና የእንጀራ አበዛ ጌታቸውን የግብፅ ንጉሥን በደሉ። 2ፈርዖንም በሁለቱ ሹማምቱ በጠጅ አሳላፊዎቹ አለቃና በእንጀራ አበዛዎቹ አለቃ ላይ ተቆጣ፤ 3ዮሴፍ ታሰሮ በነበረበትም በግዛት ስፍራ በዘበኞቹ አለቃ ቤት አስጠበቃቸው። 4የዘበኞቹም አለቃ ለዮሴፍ አሳልፎ ሰጣቸው እርሱም ያገልግላቸው ነበር በግዞት ቤትም አያሌ ቀን ተቀመጡ። 5በግዞት ቤት የነበሩት የግብፅ ንጉሥ ጠጅ አሳላፊና እንጀራ አበዛ ሁለቱም በአንዲት ሌሊት እንደ ሕልሙ ትርጓሜ እየራሳቸው ሕልምን አለሙ። 6ዮሴፍም ማልዶ ወደ እነርሱ ገባ እነሆም አዝነው አያቸው። 7በጌታው ቤት ከእርሱ ጋር በግዞት የነበሩትንም የፈርዖንን ሹማምት እንዲህ ብሎ ጠየቃቸው፦ እናንተ ዛሬ ስለ ምን አዝናችኍል? 8እነርሱም፦ ሕልምን አልመን የሚተረጕምልን አጣን አሉት ዮሴፍም አላቸው፦ ሕልምን የሚተረጕም እግዚአብሔር የሰጠው አይደለምን? እስቲ ንገሩኝ።
9የጠጅ አሳላፊዎች አለቃም ለዮሴፍ ሕልሙን እንዲህ ብሎ ነገረው፦ 10በሕልሜ የወይን ዛፍ በፊቴ ሆና አየሁ በዛፊቱም ሦስት አረግ አለበት እርስዋም ቅጠልን አበባ አወጣች፥ ዘለላም አንጠለጠለች፥ 11የዘለላዋም ፍሬ በሰለ የፈርዖን፥ ጽዋ በእጄ ነበረ ፍሬውንም ወስጄ በፈርዖን ጽዋ ጨመቅሁት ጽዋውንም ለፈርዖን በእጁ ሰጠሁት። 12ዮሴፍም አለው፦ የዚህ ትርጓሜው ይህ ነው፤ ሦስት አረግ ሦስት ቀን ነው እስከ ሦስት ቀን ድረስ ፈርዖን ራስህን ከፍ ያደርጋል፥ 13ወደ ቀደመው ሹመትህም ይመልስሃል ጠጅ አሳላፊ በነበርህበት ጊዜ ስታድርግ እንደ ነበረው እንደ ቀድሞው ሥርዓትም የፈርዓንን ጽዋ በእጁ ትሰጣለህ። 14ነገር ግን በጎ ነገር በተደረግልህ ጊዜ እኔን አስበኝ ምሕረትንም አድርግልኝ የእኔንም ነገር ለፈርዖን ነግረህ ከዚህ ቤት አውጣኝ፤ 15እኔን ከዕብራውያን አገር ሰርቀው አምጥተውኛልና ከዚህም ደግሞ በግዞት ያኖሩኝ ዘንድ ምንም አላደረግሁም።
16የእንጀራ አበዛቹ አለቃም ሕልሙን በመልካም እንደ ተረጎመ ባየ ጊዜ ዮሴፍን እንዲህ አለው፦ እኔም ደግሞ ሕልም አይቼ ነበር እነሆም ሦስት መሶብ ነጭ እንጀራ በራሴ ላይ ነበረ፤ 17በላይኛውም መሶብ ፈርዖን ከሚበላው ከጋጋዎች ሥራ ሁሉ ነበረበት፤ ወፎችም በራሴ ላይ ከመሶቡ ይበሉ ነበር። 18ዮሴፍም መልሶ እንዲህ አለው፦ የዚህ ትርጓሜው ይህ ነው ሦስት መሶብ ሦስት ቀን ነው። 19እስከ ሦስት ቀን ድረስ ፈርዖን ራስህን ከፍ ያደርጋል፥ በእንጨትም ላይ ይስቅልሃል ወፎችም ሥጋህን ይበሉታል። 20በሦስተኛውም ቀን ፈርዖን የተወለደበት ቀን ነበረ ለሠራዊቱም ሁሉ ግብር አደረገ የጠጅ አሳላፊዎቹን አለቃና የእንጀራ አበዛዎቹን አለቃ በአሽከሮቹ መካከል ከፍ አደረገ። 21የጠጅ አሳለፊዎቹንም አለቃ ወደ ስፍራው መለሰው ጽዋውንም በፈርዖን እጅ ሰጠ። 22የእንጀራ አበዛዎቹንም አለቃ ሰቀለው ዮሴፍ እንደተረጎመላቸው። 23የጠጅ አሳላፊዎች አለቃ ግን ዮሴፍን አላሰበውም ረሳው እንጂ።
Currently Selected:
ኦሪት ዘፍጥረት 40: አማ54
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ