ላባም፦ በእውነት አንተ አጥንቴ ሥጋዬም ነህ አለው። አንድ ወር የሚያህልም ከእርሱ ጋር ተቀመጠ። ላባም ያዕቆብን፦ ወንድሜ ስለሆንህ በከንቱ ታገለግለኛለህን? ምንዳህ ምንድር ነው? ንገረኝ አለው። ለላባም ሁለት ሴቶች ልጆች ነበሩት፤ የታላቂቱ ስም ልያ የታናሺቱ ስም ራሔል ነበረ። ልያም ዓይነ ልም ነበረች፤ ራሔል ግን መልከ መልካም ነበረች ፊትዋም ውብ ነበረ። ያዕቆብም ራሔልን ወደደ እንዲህም አለ፦ ስለ ታናሺቱ ልጅህ ስለ ራሔል ሰባር ዓመት እገዛልሃለሁ። ላባም፦ ለሌላ ሰው ከምሰጣት ይልቅ ለአንተ ብሰጣት ይሻላል ከእኔ ጋር ተቀመጥ አለ። ያዕቆብም ስለ ራሔል ሰባት ዓመት ተገዛ እርስዋንም ይወድዳት ስለነበረ በእርሱ ዘንድ እንደ ጥቂት ቀን ሆነለት። ያዕቆብም ላባን፦ ወደ እርስዋ እገባ ዘንድ ሚስቴን ስጠኝ ቀኔ ተፈጽሞአልና አለው። ላባም የዚያን ስፍራ ሰዎች ሁሉ ሰበሰበ ሰርግም አደረገ። በመሸም ጊዜ ልጁን ልያን ወስዶ ለያዕቆብ አገባለት፤ ያዕቆብም ወደ እርስዋ ገባ። ላባም ለልጁ ለልያ ባሪያይቱን ዘለፋን ባርያ ትሆናት ዘንድ ሰጣት። በነጋም ጊዜ እንሆ ልያ ሆና ተገኘች፤ ላባንም፦ ምነው እንደዚህ አደረግህብኝ? ያገለግልሁህ ስለ ራሔል አልነበረምን? ለምን አታለልኸኝ? አለው። ላባም እንዲህም አለ፦ በአገራችን ታላቂቱ ሳለች ታናሺቱን እንስጥ ዘንድ ወግ አይደለም፤ ይህችንም ሳምንት ፈጽም ሌላ ሰባት ዓመት ደግሞ እኔን ስለምታገለግለኝ አገልግሎት እርስዋን ደግሞ እሰጥሃለሁ። ያዕቆብም እንዲህ አደረገ ይህችንም ሳምንት ፈጸመ፤ ልጁን ራሔልንም ለእርሱ ሚስት ትሆን ዘንድ ሰጠው። ላባም ለልጁ ለራሔል ባርያይቱን ባላን ባርያ ትሆናት ዘንድ ሰጣት። ያዕቆብም ወደ ራሔል ደግሞ ገባ። ራሔልንም ከልያ ይልቅ ወደዳት ሌላ ሰባት ዓመትም ተገዛለት። እግዚአብሔርም ልያ የተጠላች መሆንዋን ባየ ጊዜ ማኅፀንዋን ከፈተላት፤ ራሔል ግን መካን ነበረች። ልያም ፀነሰች ወንድ ልጅንም ወለደች ስሙም ሮቤል ብላ ጠራችው እግዚአብሔር መከራዬን አይቶአልና፥ እንግዲህም ወዲህ ባሌ ይወድደኛል ብላለችና። ደግሞም ፀነሰች ወንድ ልጅንም ወለደች፤ እኔ እንደ ተጠላሁ እግዚአብሔር ስለ ስማ ይህን ደገመኝ አለች ስምዖን ብላ ጠራችው ደግሞም ፀነሰች ወንድ ልጅንም ወለደች አሁንም ባሌ ወደ እኔ ይጠጋል ሦስት ወንዶች ልጆችን ወልጄለታለሁና አለች፤ ስለዚህም ስሙን ሌዊ ብላ ጠራችው። ደግሞም ፀነስች ወንድ ልጅንም ወለደች በዚህም ጊዜ እግዚአብሔርን አመሰግናለሁ አለች፤ ስለዚህም ስሙን ይሁዳ ብላ ጠራችው። መውለድንም አቆመች።
ኦሪት ዘፍጥረት 29 ያንብቡ
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ኦሪት ዘፍጥረት 29:14-35
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos