ላባም ያዕቆብን፣ “አንተማ የዐጥንቴ ፍላጭ፣ የሥጋዬ ቍራጭ ነህ” አለው። ያዕቆብ አንድ ወር ሙሉ አብሮት ከተቀመጠ በኋላ፣ ላባ ያዕቆብን፣ “ዘመዴ በመሆንህ ብቻ በነጻ ልታገለግለን አይገባምና ደመወዝህ ምንድን ነው?” አለው። ላባ ሁለት ሴቶች ልጆች ነበሩት፤ የታላቂቱ ስም ልያ የታናሺቱ ራሔል ነበር። ልያ ዐይነ ልም ስትሆን ራሔል ግን ቁመናዋ ያማረ መልኳም የተዋበ ነበር። ያዕቆብም ራሔልን ስለ ወደዳት፣ “ታናሺቱ ልጅህን ራሔልን የምትድርልኝ ከሆነ ሰባት ዓመት አገለግላለሁ” አለው። ላባም መልሶ፣ “ለሌላ ሰው ከምድራት ላንተ ብድራት ይሻላል፤ እዚሁ አብረኸኝ ተቀመጥ” አለው። ያዕቆብም ራሔልን ለማግኘት ሲል ሰባት ዓመት አገለገለ፤ አጥብቆ ይወድዳትም ስለ ነበረ፣ ሰባት ዓመት እንደ ጥቂት ቀን ሆኖ ታየው። ከዚያም ያዕቆብ ላባን፣ “እነሆ፤ የተባባልነው ጊዜ አብቅቷል፤ ስለዚህ ሚስቴን አስረክበኝና የባልና የሚስት ወጋችንን እናድርስ” አለው። ስለዚህ ላባ የአካባቢውን ሰዎች በሙሉ ጠርቶ ሰርግ አበላ። ሲመሽ ግን ላባ ልጁን ልያን አምጥቶ ለያዕቆብ ሰጠው፤ ያዕቆብም አብሯት ተኛ። ላባም ዘለፋ የተባለች አገልጋዩን ለልጁ ለልያ ደንገጡር እንድትሆን ሰጣት። ሲነጋም እነሆ፤ ልያ ሆና ተገኘች፤ ስለዚህም ያዕቆብ ላባን፣ “ምነው፣ እንዲህ ጕድ ሠራኸኝ? ያገለገልሁህ ለራሔል ብዬ አልነበረምን? ታዲያ ለምን ታታልለኛለህ?” አለው። ላባም እንዲህ አለው፤ “በአገራችን ታላቋ እያለች ታናሿን መዳር የተለመደ አይደለም፤ ይህን የጫጕላ ሳምንት ፈጽምና ሌላ ሰባት ዓመት የምታገለግለን ከሆነ፣ ታናሺቱን ደግሞ እንሰጥሃለን።” ያዕቆብም በነገሩ ተስማማ፤ ከልያ ጋር ተሞሽሮ ሰባት ቀን ከቈየ በኋላ፣ ላባ ልጁን ራሔልን ለያዕቆብ ዳረለት፤ ባላ የተባለች አገልጋዩንም ደንገጡር እንድትሆናት ለራሔል ሰጣት። ያዕቆብ ከራሔልም ጋር ተኛ፤ ራሔልን ከልያ አብልጦ ወደዳት፤ ከዚያም የተነሣ ሌላ ሰባት ዓመት ላባን አገለገለው። እግዚአብሔር (ያህዌ) ልያ እንዳልተወደደች ባየ ጊዜ ማሕፀኗን ከፈተላት፤ ራሔል ግን መካን ነበረች። ልያ ፀነሰች፤ ወንድ ልጅም ወለደች፤ “እግዚአብሔር (ያህዌ) መከራዬን ስለ ተመለከተልኝ፣ ከእንግዲህ ባሌ ይወድደኛል” ስትል ስሙን ሮቤል አለችው። እንደ ገናም ፀንሳ ወለደች፤ እርሷም “እግዚአብሔር (ያህዌ) እንዳልተወደድኩ ሰምቶ ይህን ልጅ በድጋሚ ሰጠኝ” አለች። ከዚያም የተነሣ ስምዖን ብላ ጠራችው። አሁንም እንደ ገና ፀንሳ ወንድ ልጅ ወለደች፤ እርሷም፣ ሦስት ወንዶች ልጆች ስለ ወለድሁለት “ከእንግዲህ ባሌ ያቀርበኛል” አለች፤ ስለዚህ ሌዊ ብላ ጠራችው። እንደ ገና ፀንሳ አሁንም ወንድ ልጅ ወለደች፤ እርሷም፣ “እንግዲህ እግዚአብሔርን (ያህዌ) አመሰግናለሁ” አለች፤ ስሙንም ይሁዳ ብላ ጠራችው። ከዚያም በኋላ መውለድ አቆመች።
ዘፍጥረት 29 ያንብቡ
ያዳምጡ ዘፍጥረት 29
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ዘፍጥረት 29:14-35
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos