ኦሪት ዘፍጥረት 24
24
1አብርሃምም ሸመገለ በዘመኑም አረጀ፤ እግዚአብሔርም አብርሃምን በሥራው ሁሉ ባረከው። 2አብርሃምም ሎሌውን የቤቱን ሽማግሌ የከብቱን ሁሉ አዛዥ አለው፦ 3እጅህን ከጭኔ በታች አድርግ እኔም አብሬ ከምኖራቸው ከከነዓን ሴቶች ልጆች ሚስት እንዳትወስድለት በሰማይና በምድር አምላክ በእግዚአብሔር አምልሃለሁ፤ 4ነገር ግን ወደ አገሬና ወደ ተወላጆቼ ትሄዳለህ፥ ለልጄ ለይስሐቅም ሚስትን ትወስድለታለህ። 5ሎሌውም፦ ሴቲቱ ምናልባት ወደዚህ አገር ከእኔ ጋር ለመምጣት እንቢ ያለች እንደ ሆነ ልጅህን ወደ ወጣህበት አገር ለመልሰውን? አለው። 6አብርሃምም አለው፦ ልጄን ወደዚያ እንዳትመልስ ተጠንቀቅ፤ 7ከአባቴ ቤት ከተወለድሁባት ምድርም ያወጣኝ፦ ይህችንም ምድር እሰጥሃለሁ ብሎ የነገረኝና የመለልኝ የሰማይ አምላክ እግዚአብሔር እርሱ መልአኩን በፊትህ ይሰድዳል ከዚያም ከልጄ ሚስትን ትወስዳለህ። 8ሴቲቱም ከአንተ ጋር ለመምጣት እንቢ ያለች እንደ ሆነ ከዚህ ካቀረብሁህ መሐላ ንጽሕ ነህ፤ ልጄን ግን ወደዚያ አትመልሰው። 9ሎሌውም ከጌታው ለአብርሃም ጭን በታች እጁን አደረገ ስለዚህም ነገር ማለለት።
10ሎሌውም ከጌታው ግመሎች መካከል አሥር ግመሎችን ወስዶ ከጌትውም ዕቅ መልካም መልካሙን ይዞ ተነሣ፤ ተነሥቶም ወደ መስዼጦምይ ወደ ናኮር ከተማ ሄደ። 11ሲመሽም ሴቶች ውኃ ሊቀዱ በሚወጡበት ጊዜ ከከተማይቱ ውጪ በውኃው ጕድጓድ አጠገብ ግመሎቹን አሰበ ረከከ። 12እንዲህም አለ፦ የጌታዬ የአብርሃም አምላክ እግዚአብሔር ሆይ እለምንሃለሁ መንገዴን ዛሬ በፊቴ አቅናልኝ ለጌታዬም ለአብርሃም ምሕረትን አድርግ። 13እነሆ በዚህ የውኃ ምንጭ አጠገብ እኔ ቆሜአለሁ የዚህችም ከተማ ሴቶች ልጆች ውኃውን ሊቀዱ ይመጣሉ፤ 14ውኃ እጠጣ ዘንድ እንስራሽን አዘንብዩ የምላት እርስዋም፦ አንተ ጠጣ፥ ግመሎችህን ደግሞ አጠጣለሁ የምትለኝ ቆንጆ እርስዋ ለባሪያህ ለይስሐቅ ያዘጋጀሃት ትሁን፤ በዚህም ለጌታዬ ምሕረትን እንዳደረግህ አውቃለሁ። 15ይህን መናገሩንም ሳይፈጽም እነሆ ሚልካ የወለደችው የባቱኤል ልጅ ርብቃ እንስራዋን በጫንቃዋ ተሸክማ ወጣች፤ ሚልካም የአብርሃም ወንድም የናኮር ሚስት ናት 16ብላቴናይቱም መልክዋ እጅግ ያማረ ወንድ የማያውቃት ድንግልም ነበረች፤ ወደ ምንጭም ወረደች እንስራዋንም ሞላች ተመልሳም ወጣች። 17ሎሌውም ሊገናኛት ሮጠና፦ ከእንስራሽ ጥቂት ውኃ ታጠጪኝ ዘንድ እለምንሻለሁ አላት። 18እርስዋም፦ ጌታዬ ሆይ ጠጣ አለችው ፈጥና፥ እንስራዋን በእጅዋ አውርዳ አጠጣችው። 19እርሱንም ካጠጣች በኍላ፦ ለግመሎችህ ደግሞ ሁሉም እስኪረኩ ድረስ ውኃ እቀዳለሁ አለች። 20ፈጥናም ውኃውን ከእንስራዋ በማጠጫው ውስጥ ገለበጠችው ደግሞም ልትቀዳ ወደ ጕድጓዱ ሮጠች ለግመሎቹም ሁሉ ውኃ ቀዳች። 21ሰውዮውም ትክ ብሎ ይመለከታት ነበር እግዚአብሔር መንገዱን አቅንቶለት እንደ ሆነ ወይም እንዳልሆነ ለማወቅም ዝም አለ። 22ግመሎቹም ከጠጡ በኍላ እንዲህ ሆነ ሰውዮው ግማሽ ሳቅል የሚመዘን የወርቅ ቀለበት ለእጆችዋም አሥር ሰቅል የሚመዘን ጥንድ የወርቅ አምባር አወጣ 23እንዲህንም አላት፦ አንቺ የማን ልጅ ነሽ? እስኪ ንገሪኝ በአባትሽ ቤት የምናድርበት ስፍራ ይገኛልን? 24አለችውም፦ እኔ ሚልካ ለናኮር የወለደችው የባቱኤል ልጅ ነኝ 25በእኛ ዘንድ ገለባና ገፈራ የሚበቃ ያህል አለ፥ ለማደሪያም ደግሞ ስፍራ አለን። 26ሰውዮውም አጎነበሰ፥ ለእግዚአብሔር ሰገደ። 27እንዲህም አለ፦ ቸርነቱንና እውነቱን ከጌታዬ ያላራቀ የጌታዬ የአብርሃም አምላክ እግዚአብሔር ይመስገን፤ እኔ በመንገድ ሳለሁ እግዚአብሔር ወደ ጌታዬ ወንድሞች ቤት መራኝ።
28ብላቴናይቱም ሮጠች ለእናትዋም ቤት ይህን ነገር ሁሉ ተናገርች 29ለርብቃም ላባ የተባለ ወንድም ነበራት ላባም ወደ ውጪ ወደ ውኃው ምንጭ ወደ ሰውዮው ሮጠ 30ቀለበቱንን አምባሮቹን በእኅቱ እጅ ባየ ጊዜ የእኅቱን የርብቃንም ነገር፦ ያ ሰው እንዲህ አለኝ ያለችውን በሰማ ጊዜ እርሱ ወደዚያ ሰው መጣ እነሆም በውኃው ምንጭ አጠገብ ከግመሎቹ ዘንድ ቆሞ ነበር። 31እርሱም አለው፦ አንተ የእግዚአብሔር ቡሩክ ግባ፤ ስለምን አንተ በውጪ ቆመሃል? እኔም ቤቱን ለግመሎችህም ስፍራ አዘጋጅቼአለሁ። 32ሰውዮውም ወደ ቤት ገባ ግመሎቹንም አራገፈ ገለባና ገፈራም ለግመሎቹ አቀረበ፤ እግሩን ይታጠብ ዘንድ ከእርሱም ጋር ላሉት ሰዎች እግር ውኃ አቀረበ። 33መብልንም በፊቱ አቀረበለት፤ እርሱ ግን፦ ነገሬን እስክናገር ድረስ አልበላም አለ። 34እርሱም አለ፦ እኔ የአብርሃም ሎሌ ነኝ። 35እግዚአብሔርም ጌታዬን እጅግ ባረከው አገነነውም፤ በጎችንና ላሞችን፥ ብርንም፥ ወርቅንም፥ ወንዶም ባሪያዎችንና ሴቶች ባሪያዎችን ግመሎችንም አህዮችንም ሰጠው። 36ሣራም የጌታዬ ሚስት በእርጅናዋ ለጌታዬ ወንድ ልጅን ወለደች፤ የነበረውንም ሁሉ ሰጠው። 37ጌታዬም እንዲህ ሲል አማለኝ፦ እኔ ካለሁበት አገር ከከነዓናውያን ሴቶች ልጆች ለልጄ ሚስትን አትውሰድ፤ 38ነገር ግን ወደ አባቴ ቤት ወደ ወገኔም ሂድ ለልጄም ሚስትን ውሰድለት። 39ጌታዬንም፦ ሴቲቱ ምናልባት ባትከተለኝሳ? አልሁት። 40እርሱም አለኝ፦ አካሄዴን በፊቱ ያደረግ ሁለት እግዚአብሔር መልአኩን ከአንተ ጋር ይልካል መንገድህንም ያቀናም፤ ለልጄም ከወገኖቼ ከአባቴም ቤት ሚስትን ትወስዳለህ 41የዚያን ጊዜ ከመሐላዬ ንጹሕ ነህ፤ ወደ ዘመዶቼ ሄደህ እነርሱ ባይሰጡህ ካማልሁህ መሐላ ንጹሕ ትሆናለህ። 42ዛሬም ወደ ውኃው ምንጭ መጣሁ እንዲህም አልሁ፦ የጌታዬ የአብርሃም አምላክ እግዚአብሔር ሆይ፥ ዛሬ የምሄድበትን መንገዴን ብታቀናልኝ፤ 43እነሆ እኔ በውኃው ምንጭ ላይ ቆሜአለሁ፤ ውኃ ልትቀዳ ለምትመጣውም ቆንጆ፦ ጥቂት ውኃ ከእንስራሽ አጠጪኝ ስላት 44እርስዋም፦ አንተ ጠጣ ደግሞም ለግመሎችህ እቀዳለሁ የምትለኝ እግዚአብሔር ለጌታዬ ልጅ ያዘጋጃት ሴት እርስዋ ትሁን። 45እኔም የልቤን መናገር ገና ሳልፈጽም እነሆ፥ ርብቃ እንስራዋን በትከሻዋ ተሸክማ ወጣች ወደ ምንጭም ወርዳ ውኃ ቀዳች እኔም፦ እስኪ አጠጭኝ አልኍት። 46ፈጥናም እንስራዋን ከጫንቃዋ አወረደችና፦ አንተ ጠጣ፥ ግመሎችህንም ደግሞ አጠጣለሁ አለች፤ እኔም ጠጣሁ፥ ግመሎቼንም ደግሞ አጠጣች። 47እኔም፦ አንቺ የማን ልጅ ነሽ? ብዬ ጠየቅኍት። እርስዋም ሚልካ ለናኮር የወለደችለት የባቱኤል ልጅ ነኝ አለች፤ ቀለበትም አደረግሁላት ለእጆችዋም አምባሮች አደረግሁላት። 48በግምባሬም አጎነበስሁ፥ ለእግዚአብሔርም ሰገድሁ፤ የጌታዬን የወንድሙን ልጅ ለልጁ እወስድ ዘንድ በቀና መንገድ የመራኝን የጌታዬን የአብርሃም አምላክ እግዚአብሔርን አመሰገንሁ። 49አሁንም ቸርንትና እውነት ለጌታዬ ትሠሩ እንደ ሆነ ንገሩኝ፤ ይህም ባይሆን ንገሩኝ ወደ ቀኝ ወይም ወደ ግራ እል ዘንድ።
50ላባና ባቱኤልም መለሱ እንዲህም አሉ፦ ነገሩ ከእግዚአብሔር ዘንድ መጥቶአል ክፉም በጎ፥ ልንመልስልህ አንችልም 51ርብቃ እንኍት በፊትህ ናት ይዘሃት ሂድ እግዚአብሔር እንደ ተናገረ ለጌታህም ልጅ ሚስት ትሁን። 52የአብርሃምም ሎሌ ነገራቸውን በሰማ ጊዜ ወደ ምድር ወድቆ ለእግዚአብሔር ሰገደ። 53ሎሌውም የብርና የወርቅ ጌጥ ልብስም አወጣ፥ ለርብቃም ሰጣት፤ የከበረ ስጦታንም ለወንድምዋና ለእናትዋ አቀረበ። 54እርሱም ከእርሱም ጋር ያሉት በሉ ጠጡም ከዚያም አደሩ ማልደውም ተነሡና፦ ወደ ጌታዬ እሄድ ዘንድ አሰናብቱኝ አላቸው። 55ወንድምዋና እናትዋም፦ ብላቴናይቱ አንድ አሥር ቀን ያህል እንኳ ከእኛ ዘንድ ትቀመጥ ከዚያም በኍላ ትሄዳለች አሉ። 56እርሱም፦ እግዚአብሔር መንገዴን አቅንቶልኛልና አታዘግዩኝ፤ ወደ ጌታዬ እሄድ ዘንድ አሰናብቱኝ አላቸው። 57እነርሱም፦ ብላቴናቱን እንጥራና ከአፍዋ እንጠይቅ አሉ። 58ርብቃንም ጠርተው፦ ከዚህ ሰው ጋር ትሄጃለሽን? አሉአት። እርስዋ፦ እሄዳለሁ አለች። 59እኅታቸውንም ርብቃን ሞግዚትዋንም የአብርሃምን ሎሌና ሰዎቹንም አሰናበቱአቸው። 60ርብቃንም መረቁአትና፦ አንቺ እኅታችን እልፍ አእላፋት ሁኚ፤ ዘርሽም የጠላቶችን ደጅ ይውረስ አሉአት።
61ርብቃም ተነሣች ደንገጥሮችዋም በግመሎችም ላይ ተቀምጠው ያንን ሰው ተከተሉት፤ ሎሌውም ርብቃን ተቀብሎ ሄደ። 62ይስሐቅም ብኤርለሃይሮኢ በሚሉአት ምንጭ መንገድ መጣ በአዜብ ምድር ተቀምጦ ነበርና። 63ይስሐቅም በመሸ ጊዜ በልቡ እያሰላሰለ ወደ ሜዳ ወጥቶ ነበር ዓይኖቹንም፥ አቀና እነሆም ግመሎች ሲመጡ አየ 64ርብቃም ዓይኖችዋን አቀናች ይስሐቅንም አየች ከግመልም ወረድች። 65ሎሌውንም፦ ሊገናኘን በሜዳ የሚመጣ ይህ ሰው ማን ነው? አለችው። 66ሎሌውም፦ እርሱ ጌታዬ ነው አላት እርስዋም መሸፈኛ ወስዳ ተከናነበች። ሎሌውም ያደረገውን ነገር ሁሉ ለይስሐቅ ነገረው። 67ይስሐቅም ወደ እናቱ ወደ ሣራ ድንኳን አገባት ርብቃንም ወሰዳት ሚስትም ሆነችው ወደዳትም ይስሐቅም ከእናቱ ሞት ተጽናና።
Currently Selected:
ኦሪት ዘፍጥረት 24: አማ54
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ