ኦሪት ዘፍጥረት 17
17
1አብራምም የዘጠና ዘጠኝ ዓመት ሰው በሆን ጊዜ እግዚአብሔር ለአብራም ተገለጠለትና፥ እነሆ ኤልሻዳይ ነኝ በፊቴ ተመላለስ፥ ፍጽምም ሁን፤ 2ቃል ኪዳኔንም በእኔና በአንተ መካከል አደርጋለሁ፥ እጅግም አበዛሃለሁ አለው። 3አብራምም በግምባሩ ወደቀ፤ እግዚአብሔርም እንዲህ ብሎ ተናገረው፥ 4እነሆ፥ ቃል ኪዳኔ ከአንተ ጋር ነው ለብዙ አሕዛብም አባት ትሆናለህ። 5ከዛሬም ጀምሮ እንግዲህ ስምህ አብራም ተብሎ አይጠራ፥ ነገር ግን ስምህ አብርሃም ይሆናል፤ ለብዙ አሕዛብ አባት አድርጌሃለሁና። 6እጅግም አበዛሃለሁ፥ ሕዝብም አደርግሃለሁም ነገሥታትም ከአንተ ይወጣሉ። 7ቃል ኪዳኔንም በእኔና በአንተ መካከል ከአንተም በኍላ ከዘርህ ጋር በትውልዳቸው ለዘላለም ኪፋን አቆማለሁ፥ ለአንተና ለአንተ በኍላ ለዘርህ አምላክ እሆን ዘንድ። 8በእንግድነት የምትኖርባትን ምድር የከነዓ ምድር ሁሉ ለዘላለም ግዛት ይሆንህ ዘንድ ለአንተና ከአንተ በኍላ ለዘርህ እሰጣለሁ፤ አምላክም እሆናቸዋለሁ።
9እግዚአብሔርም አብርሃምን አለው፥ አንተ ደግሞ ቃል ኪዳኔን ትጠብቅለህ፥ አንተ ከአንተም በኍላ ዘርህ በትውልዳቸው። 10በእኔና በአንተ መካከለ ከአንተም በኍላ በዘርህ መካከል የምትጠብቁት ቃል ኪዳኔን ይህ ነው ከእናንተ ወንድ ሁሉ ይገረዝ። 11የቍልፈታችሁንም ሥጋ ትገረዛላችሁ፤ በእኔና በእናንተ መካከል ላለውም ቃል ኪዳን ምልክት ይሆንል። 12የስምንት ቀን ልጅ ይገረዝ፤ በቤት የተወለደ ወይም ከዘራችሁ ያይደለ በብርም ከእንግዳ ሰው የተገዛ፥ ወንድ ሁሉ በትውልዳችሁ ይገርዝ። 13በቤትህ የተወለደ በብርህም የተገዛ ፈጽሞ ይገረዝ። 14ቃል ኪዳኔም በሥጋችሁ የዘላለም ቃል ኪዳን ይሆናል። የቍልፈቱን ሥጋ ያልተገረዘ ቆላፍ ሰው ሁሉ ያች ነፍስ ከወገንዋ ተለይታ ትጥፋ ቃል ኪዳኔን አፍርሳለችና።
15እግዚአብሔርም አብርሃምን አለው፥ የሚስትህን የሦራን ስም ሦራ ብለህ አትጥራ፥ ስምዋ ሣራ ይሆናል እንጂ። 16እባርካታለሁ፥ ደግሞም ከእርስዋ ልጅ እሰጥሃለሁ እባርካትማለሁ፥ የአሕዛብም እናት ትሆናለች፤ የአሕዛብ ነገሥታት ከእርስዋ ይወጣሉ። 17አብርሃምም በግምባሩ ወደቀ፥ ሳቀም፥ በልቡም አለ፥ የመቶ ዓመት ሰው በውኑ ልጅ ይወልዳልን? ዘጠና ዓመት የሆናትም ሣራ ትወልዳለችን? 18አብርሃምም እግዚአብሔርን፥ እስማኤል በፊትህ ቢኖር በወደድሁ ነበር አለው። 19እግዚአብሔርም አለ፥ በእውነት ሚስትህ ሣራ ወንድ ልጅን ትወልድልሃለች፥ ስሙንም ይስሐቅ ብልህ ትጠራዋለህ፤ ከእርሱ በኍላ ለዘሩ የዘላለም ቃል ኪዳን እንዲሆን ቃል ኪዳኔን ከእርሱ ጋር አቆማለሁ። 20ስለ እስማኤልም ሰምቼሃለሁ፤ እነሆ ባርኬዋለሁ፥ ፍሬያምም አደርገዋለሁ፥ እጅግም አበዛዋለሁ፤ አሥራ ሁለት አለቆችንም ይወልዳል፥ ታላቅ ሕዝብም እንዲሆን አደርገዋለሁ። 21ቃለ ኪዳኔን ግን በሚመጣው ዓመት በዚሁ ጊዜ ሣራ ከምትወልድልህ ከይስሐቅ ጋር አቆማለሁ።
22ንግግሩንም ከእርሱ ጋር በፈጸም ጊዜ እግዚአብሔር ከአብርሃም ተለይቶ ወጣ። 23አብርሃምም ልጁን እስማኤልን፥ በቤቱም የተወለዱትን ሁሉ በብሩም የገዛቸውን ሁሉ ከአብርሃም ቤተሰብ ወንዶቹን ሁሉ ወሰደ የቍልፈታቸውንም ሥጋ እግዚአብሔ እንዳለው በዚያው ቀን ገረዘ። 24አብርሃምም የቍልፈቱን ሥጋ በተገረዘ ጊዜ የዘጠና ዘጠኝ ዓመት ሰው ነበረ፤ 25ልጅ እስማኤልም የቍልፈቱን ሥጋ በተገረዘ ጊዜ የአሥራ ሦስት ዓመት ልጅ ነበረ። 26በዚያው ቀን አብርሃም ተገረዘ ልጁ እስማኤልም። 27በቤት የተወለዱትና በብር ከእንግዶች የተገዙት የቤቱ ሰዎች ሁሉ ከእርሱ ጋር ተገረዙ።
Currently Selected:
ኦሪት ዘፍጥረት 17: አማ54
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ