ትንቢተ ሕዝቅኤል 9
9
1እርሱም፦ እያንዳንዳቸው የሚያጠፋ መሣሪያን በእጃቸው ይዘው ከተማይቱን የሚቀሥፉ ይቅረቡ ብሎ በታላቅ ድምፅ በጆሮዬ ጮኸ። 2እነሆም፥ እያንዳንዳቸው አጥፊውን መሣሪያ በእጃቸው ይዘው ስድስት ሰዎች ወደ ሰሜን ከሚመለከተው ከላይኛው በር መንገድ መጡ፥ በመካከላቸውም የበፍታ ልብስ የለበሰ የጸሐፊም ቀለም ቀንድ በወገቡ የያዘ አንድ ሰው ነበረ። እነርሱም ገብተው በናሱ መሠዊያ አጠገብ ቆሙ።
3የእስራኤልም አምላክ ክብር በበላዩ ከነበረበት ኪሩብ ተነሥቶ ወደ ቤቱ መድረክ ሄዶ ነበር፥ በፍታ የለበሰውን የጸሐፊውንም ቀለም ቀንድ በወገቡ የያዘውን ሰው ጠራ። 4እግዚአብሔርም፦ በከተማይቱ በኢየሩሳሌም መካከል እለፍ፥ በመካከልዋም ስለ ተሠራው ርኵሰት ሁሉ በሚያለቅሱና በሚተክዙ ሰዎች ግምባር ላይ ምልክት ጻፍ አለው። 5እኔም እየሰማሁ ለሌሎቹ፦ እርሱን ተከትላችሁ በከተማይቱ መካከል እለፉ ግደሉም፥ ዓይናችሁ አይራራ አትዘኑም፥ 6ሽማግሌውንና ጐበዙን ቈንጆይቱንም ሕፃናቶቹንና ሴቶቹን ፈጽማችሁ ግደሉ፥ ነገር ግን ምልክቱ ወዳለበት ሰው ሁሉ አትቅረቡ፥ በመቅደሴም ጀምሩ አላቸው። በቤቱም አንጻር ባሉ ሽማግሌዎች ጀመሩ። 7እርሱም፦ ቤቱን አርክሱ፥ በተገደሉትም ሰዎች አደባባዮችን ሙሉ ውጡ አላቸው። እነርሱም ወጥተው በከተማይቱ ገደሉ። 8ሲገድሉም እኔ ብቻዬን ቀርቼ ሳለሁ በግምባሬ ተደፍቼ፦ ጌታ እግዚአብሔር ሆይ፥ ወዮ! መዓትህን በኢየሩሳሌም ላይ ስታፈስስ የእስራኤልን ቅሬታ ሁሉ ታጠፋለህን? ብዬ ጮኽሁ።
9እርሱም፦ የእስራኤልና የይሁዳ ቤት ኃጢአት እጅግ በዝቶአል ምድሪቱም ደም፥ ከተማይቱም ዓመፅን ተሞልታለች፥ እነርሱም፦ እግዚአብሔር ምድሪቱን ትቶአታል እግዚአብሔርም አያይም ብለዋል። 10እኔም ደግሞ በዓይኔ አልራራም አላዝንምም፥ መንገዳቸውንም በራሳቸው ላይ እመልሳለሁ አለኝ። 11እነሆም፥ በፍታ የለበሰው የቀለም ቀንድም በወገቡ የያዘው ሰው፦ ያዘዝኸኝን አድርጌአለሁ ብሎ በቃሉ መለሰ።
Currently Selected:
ትንቢተ ሕዝቅኤል 9: አማ54
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ