ትንቢተ ሕዝቅኤል 48
48
1የነገዶችም ስም ይህ ነው። በሔትሎን መንገድ አጠገብ ወደ ሐማት መግቢያ በደማስቆም ድንበር ባለው በሐጸርዔናን በሐማትም አጠገብ በሰሜን በኩል ካለው ከሰሜን ድንበር ይጀምራል። ወርዳቸውም ከምሥራቅ ጀምሮ እስከ ምዕራብ ድረስ ይሆናል። ለዳን አንድ የዕጣ ክፍል ይሆናል። 2ከዳን ድንበር ቀጥሎ ከምሥራቅ ጀምሮ እስከ ምዕራብ ድረስ ለአሴር አንድ የዕጣ ክፍል ይሆናል። 3ከአሴርም ድንበር ቀጥሎ ከምሥራቅ ጀምሮ እስከ ምዕራብ ድረስ ለንፍታሌም አንድ የዕጣ ክፍል ይሆናል። 4ከንፍታሌም ድንበር ቀጥሎ ከምሥራቅ ጀምሮ እስከ ምዕራብ ድረስ ለምናሴ አንድ የዕጣ ክፍል ይሆናል። 5ከምናሴም ድንበር ቀጥሎ ከምሥራቅ ጀምሮ እስከ ምዕራብ ድረስ ለኤፍሬም አንድ የዕጣ ክፍል ይሆናል። 6ከኤፍሬምም ድንበር ቀጥሎ ከምሥራቅ ጀምሮ እስከ ምዕራብ ድረስ ለሮቤል አንድ የዕጣ ክፍል ይሆናል። 7ከሮቤልም ድንበር ቀጥሎ ከምሥራቅ ጀምሮ እስከ ምዕራብ ድረስ ለይሁዳ አንድ የዕጣ ክፍል ይሆናል።
8ከይሁዳም ድንበር ቀጥሎ ከምሥራቅ ጀምሮ እስከ ምዕራብ ድረስ ለመባ የሆነ የዕጣ ክፍል ይሆናል፥ ወርዱ ሀያ አምስት ሺህ ክንድ ይሆናል ርዝመቱም ከምሥራቅ ጀምሮ እስከ ምዕራብ ድረስ ከዕጣ ክፍሎች እንደ አንዱ ይሆናል፥ መቅደሱም በመካከሉ ይሆናል። 9ለእግዚአብሔር የምታቀርቡት መባ ርዝመቱ ሃያ አምስት ሺህ ወርዱም ሃያ ሺህ ክንድ ይሆናል። 10ለእነዚህም ለካህናቱ የተቀደሰ መባ ይሆናል፥ በሰሜን በኩል ርዝመቱ ሀያ አምስት ሺህ፥ በምዕራብም በኩል ወርዱ አሥር ሺህ፥ በምሥራቅም በኩል ወርዱ አሥር ሺህ፥ በደቡብም በኩል ርዝመቱ ሃያ አምስት ሺህ ክንድ ይሆናል። የእግዚአብሔርም መቅደስ በመካከሉ ይሆናል። 11የእስራኤልም ልጆች በሳቱ ጊዜ፥ ሌዋውያን እንደ ሳቱ ላልሳቱት ሥርዓቴን ለጠበቁት ከሳዶቅ ልጆች ወገን ለተቀደሱት ካህናት ይሆናል። 12ከምድርም መባ የተለየ መባ ይሆንላቸዋል፥ ከሁሉም ይልቅ የተቀደሰ ይሆናል፥ በሌዋውያን ድንበር አጠገብ ይሆናል።
13በካህናቱም ድንበር አንጻር ርዝመቱ ሀያ አምስት ሺህ ወርዱም አሥር ሺህ የሆነ ዕጣ ለሌዋውያን ይሆናል፥ ርዝመቱ ሁሉ ሀያ አምስት ሺህ ወርዱም ሀያ ሺህ ክንድ ይሆናል። 14ለእግዚአብሔርም የተቀደሰ ነውና ከእርሱ ምንም አይሸጡም አይለውጡምም፥ የምድሩም በኵራት አይፋለስም።
15በሀያ አምስቱም ሺህ አንጻር አምስት ሺህ ወርድ ያለው የቀረ ስፍራ ለከተማይቱ ለጋራ ጉዳይዋ፥ ለመኖሪያ ለማሰማርያም ይሆናል፥ ከተማይቱም በመካከሉ ትሆናለች። 16ልክዋም ይህ ነው፥ በሰሜን በኩል አራት ሺህ አምስት መቶ፥ በደቡብም በኩል አራት ሺህ አምስት መቶ፥ በምሥራቅም በኩል አራት ሺህ አምስት መቶ፥ በምዕራብም በኩል አራት ሺህ አምስት መቶ ክንድ ይሆናል። 17ለከተማይቱም ማሰማርያ ይኖራታል፥ በሰሜን በኩል ሁለት መቶ አምሳ፥ በደቡብም በኩል ሁለት መቶ አምሳ፥ በምሥራቅም በኩል ሁለት መቶ አምሳ፥ በምዕራብም በኩል ሁለት መቶ አምሳ ክንድ ይሆናል። 18በተቀደሰው መባ አንጻር የተረፈው ርዝመቱ ወደ ምሥራቅ አሥር ሺህ ወደ ምዕራብም አሥር ሺህ ክንድ ይሆናል። በተቀደሰው መባ አንጻር ይሆናል። ፍሬውም ከተማይቱን ለሚያገለግሉ ለመብል ይሆናል። 19ከእስራኤል ነገድ ሁሉ ከተማይቱን የሚያገለግሉ ያርሱታል። 20መባው ሁሉ ርዝመቱ ሀያ አምስት ሺህ ወርዱም ሀያ አምስት ሺህ ክንድ ይሆናል፥ የተቀደሰውን መባ ከከተማይቱ ይዞታ ጋር አራት ማዕዘን አድርጋችሁ ትሰጣላችሁ።
21በተቀደሰው መባና በከተማይቱ ይዞታ በዚህና በዚያ ወገን የቀረው ለአለቃው ይሆናል፥ በመባው በሃያ አምስቱ ሺህ ፊት ወደ ምሥራቁ ድንበር፥ በምዕራብም በኩል በሀያ አምስቱ ሺህ ፊት ወደ ምዕራቡ ድንበር፥ እንደ ዕጣ ክፍል ሁሉ መጠን፥ ለአለቃው ይሆናል፥ የተቀደሰውም መባና ቤተ መቅደሱ በመካከሉ ይሆናል። 22የሌዋውያንም ርስት የከተማይቱም ይዞታ ለአለቃው በሆነው መካከል ይሆናል፥ በይሁዳ ድንበርና በብንያም ድንበር መካከል የአለቃ ዕጣ ክፍል ይሆናል።
23ለቀሩትም ነገዶች እንዲህ ይሆናል፥ ከምሥራቅ ጀምሮ እስከ ምዕራብ ድረስ ለብንያም አንድ የዕጣ ክፍል ይሆናል። 24ከብንያምም ድንበር ቀጥሎ ከምሥራቅ ጀምሮ እስከ ምዕራብ ድረስ ለስምዖን አንድ የዕጣ ክፍል ይሆናል። 25ከስምዖንም ድንበር ቀጥሎ ከምሥራቅ ጀምሮ እስከ ምዕራብ ድረስ ለይሳኮር አንድ የዕጣ ክፍል ይሆናል። 26ከይሳኮርም ድንበር ቀጥሎ ከምሥራቅ ጀምሮ እስከ ምዕራብ ድረስ ለዛብሎን አንድ የዕጣ ክፍል ይሆናል። 27ከዛብሎንም ድንበር ቀጥሎ ከምሥራቅ ጀምሮ እስከ ምዕራብ ድረስ ለጋድ አንድ የዕጣ ክፍል ይሆናል። 28ከጋድም ድንበር ቀጥሎ በደቡብ በኩል ድንበሩ ከታማር ጀምሮ እስከ ሜሪባ ቃዴስ ውኃ እስከ ግብጽ ወንዝ እስከ ታላቁ ባሕር ድረስ ይሆናል። 29ርስት አድርጋችሁ ለእስራኤል ነገዶች በዕጣ የምታካፍሉአት ምድር ይህች ናት፥ የእያንዳንዱም ዕጣ እንደዚህ ነው፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።
30የከተማይቱም መውጫዎች እነዚህ ናቸው። በሰሜን ወገን ልኩ አራት ሺህ አምስት መቶ ክንድ ነው። 31የከተማይቱ በሮች እንደ እስራኤል ነገዶች ስም ይሆናሉ፥ በሰሜን በኩል አንዱ የሮቤል በር አንዱም የይሁዳ በር አንዱም የሌዊ በር፥ ሦስት በሮች ይሆናሉ። 32በምሥራቁም ወገን አራት ሺህ አምስት መቶ ክንድ፥ ሦስትም በሮች አሉ፥ አንዱ የዮሴፍ በር አንዱም የብንያም በር አንዱም የዳን በር ነው። 33በደቡብም ወገን ልኩ አራት ሺህ አምስት መቶ ክንድ፥ ሦስትም በሮች አሉ፥ አንዱ የስምዖን በር አንዱም የይሳኮር በር አንዱም የዛብሎን በር ነው። 34በምዕራቡም ወገን ልኩ አራት ሺህ አምስት መቶ ክንድ፥ ሦስትም በሮች አሉ፥ አንድ የጋድ በር አንዱም የአሴር በር አንዱም የንፍታሌም በር ነው። 35ዙሪያዋም አሥራ ስምንት ሺህ ክንድ ይሆናል፥ ከዚያም ቀን ጀምሮ የከተማይቱ ስም፦ እግዚአብሔር በዚያ አለ ተብሎ ይጠራል።
Currently Selected:
ትንቢተ ሕዝቅኤል 48: አማ54
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ