የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ትንቢተ ሕዝቅኤል 36:1-12

ትንቢተ ሕዝቅኤል 36:1-12 አማ54

አንተም፥ የሰው ልጅ ሆይ፥ ለእስራኤል ተራሮች ትንቢት ተናግረህ፦ የእስራኤል ተራሮች ሆይ፥ የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ በል። ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ጠላት በእናንተ ላይ፦ እሰይ፥ የጥንት ከፍታዎች ለእኛ ርስት ሆነዋል ብሎአልና ስለዚህ ትንቢት ተናገር እንዲህም በል፦ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ለቀሩት አሕዛብ ርስት ትሆኑ ዘንድ በዙሪያችሁ ያሉ ባድማ አድርገዋችኋልና፥ ውጠዋችሁማልና፥ እናንተም የተናጋሪዎች ከንፈር መተረቻና የሕዝብ ማላገጫ ሆናችኋልና ስለዚህ፥ እናንተ የእስራኤል ተራሮች ሆይ፥ የጌታን የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ። ጌታ እግዚአብሔር ለተራሮችና ለኮረብቶች፥ ለፈሳሾችና ለሸለቆች ለምድረ በዳዎች ባዶ ለሆኑትም በዙሪያ ላሉት ለቀሩት አሕዛብ ምርኮና መሳቂያ ለሆኑት ከተሞች እንዲህ ይላል፥ ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ያሳድዱአትና ይበዘብዙአት ዘንድ በልባቸው ሁሉ ደስታና በነፍሳቸው ንቀት ምድሬን ርስት አድርገው ለራሳቸው በሰጡ በቀሩት አሕዛብና በኤዶምያስ ሁሉ ላይ በቅንዓቴ እሳት ተናግሬአለሁ፥ ስለዚህ ስለ እስራኤል ምድር ትንቢት ተናገር፥ ለተራሮችና ለኮረብቶችም ለፈሳሾችና ለሸለቆችም እንዲህ በል፦ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እነሆ፥ የአሕዛብን ስድብ ስለ ተሸከማችሁ በቅንዓቴና በመዓቴ ተናግሬአለሁ፥ ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ በዙሪያችሁ ያሉ አሕዛብ ስድባቸውን በእርግጥ ይሸከማሉ ብዬ ምያለሁ። የእስራኤል ተራሮች ሆይ፥ እናንተ ግን ቅርንጫፎቻችሁን ታቈጠቍጣላችሁ፥ ይመጡም ዘንድ ቀርበዋልና ለሕዝቤ ለእስራኤል ፍሬአቸሁን ትሰጣላችሁ። እነሆ፥ እኔ ለእናንተ ነኝና፥ ወደ እናንተም እመለከታለሁ፥ እናንተም ትታረሳላችሁ ይዘራባችሁማል፥ እኔም የእስራኤልን ቤት ሰዎች ሁሉ ሁሉንም አበዛባችኋለሁ፥ በከተሞችም ሰዎች ይኖሩባቸዋል ባድማዎቹም ስፍራዎች ይሠራሉ፥ ሰውንና እንስሳውንም አበዛባችኋለሁ፥ እነርሱም ይበዛሉ ያፈሩማል፥ እንደ ጥንታችሁም ሰዎችን አኖርባችኋለሁ፥ ቀድሞም ካደረግሁላችሁ ይልቅ መልካም አደርግላችኋለሁ፥ እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቃላችሁ። ሰዎችንም፥ ሕዝቤን እስራኤልን፥ በእናንተ ላይ አስሄዳቸዋለሁ፥ እነርሱም ይወርሱሻል ርስትም ትሆኛቸዋለሽ፥ ከእንግዲህም ወዲያ ልጅ አልባ አታደርጊአቸውም።