የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ሕዝቅኤል 36:1-12

ሕዝቅኤል 36:1-12 NASV

“የሰው ልጅ ሆይ፤ ለእስራኤል ተራሮች ትንቢት ተናገር፤ እንዲህም በል፤ ‘የእስራኤል ተራሮች ሆይ፤ የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ። ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ጠላት ስለ አንቺ፣ “ዕሠይ! እነዚያ የጥንት ተራሮች የእኛ ርስት ሆነዋል ብሏል።” ’ ስለዚህ ትንቢት ተናገር፤ እንዲህም በል፤ ‘ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ከየአቅጣጫው ከብበው በመውጋት ስላጠቋችሁ፣ ለቀሩት ሕዝቦች ሁሉ ርስት ሆናችሁ፤ ለሕዝብም መሣቂያና መሣለቂያ ሆናችሁ። ስለዚህ የእስራኤል ተራሮች ሆይ፤ የጌታ እግዚአብሔርን ቃል ስሙ፤ ጌታ እግዚአብሔር ለተራሮችና ለኰረብቶች፣ ለሸለቆዎችና ለውሃ መውረጃዎች፣ ለፈራረሱ ባድማዎችና፣ በሌሎቹ በዙሪያችሁ ባሉት ሕዝቦች ተዘርፈውና መዘባበቻ ሆነው መና ለቀሩት ከተሞች እንዲህ ይላል፤ ልዑል እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ በሚቃጠል ቅናቴ በቀሩት ሕዝቦች ሁሉና በኤዶም ሁሉ ላይ ተናግሬአለሁ፤ ከልብ በመነጨ ደስታና በንቀት ተሞልተው የግጦሽ መሬቴን ይዘው ይበዘብዙት ዘንድ የራሳቸው ርስት አድርገውታልና።’ ስለዚህ የእስራኤልን ምድር የሚመለከት ትንቢት ተናገር፤ ለተራሮች፣ ለኰረብቶች፣ ለሸለቆዎችና ለውሃ መውረጃዎች እንዲህ በል፤ ‘ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “በሕዝቦች ዘለፋ ስለ ተሠቃያችሁ ቍጣ በተሞላ ቅናቴ እናገራለሁ።” ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “እጄን አንሥቼ እምላለሁ፤ በዙሪያችሁ ያሉ ሕዝቦች ዘለፋ ይወርድባቸዋል።” “ ‘የእስራኤል ተራሮች ሆይ፣ እናንተ ግን፤ ለሕዝቤ ለእስራኤል ቅርንጫፍ ታወጣላችሁ፤ ፍሬም ታፈራላችሁ፤ በቅርቡ ወደ አገራቸው ይመለሳሉና። ስለ እናንተ ይገድደኛል፤ በበጎነትም እመለከታችኋለሁ፤ ትታረሳላችሁ፤ ዘርም ይዘራባችኋል። መላው የእስራኤል ቤት እንኳ ሳትቀሩ፣ የሰዎችን ቍጥር በእናንተ ላይ አበዛለሁ። ከተሞች የሰው መኖሪያ ይሆናሉ፤ የፈረሱት እንደ ገና ይሠራሉ። በእናንተ ላይ የሰዎችንና የእንስሳትን ቍጥር እጨምራለሁ፤ ፍሬያማ ይሆናሉ፤ ቍጥራቸውም ይበዛል። እንዳለፈው ጊዜ ሁሉ ሰዎች በውስጣችሁ እንዲኖሩ አደርጋለሁ፤ ካለፈው የበለጠ አበለጽጋችኋለሁ፤ ከዚያም እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቃላችሁ። ሰዎችን፣ ሕዝቤን እስራኤልን በእናንተ ላይ እንዲመላለሱ አደርጋለሁ፤ ይወርሷችኋል፤ እናንተም ርስታቸው ትሆናላችሁ፤ ከእንግዲህ ወዲህ ልጅ አልባ አታደርጓቸውም።