ትንቢተ ሕዝቅኤል 19
19
1አንተም በእስራኤል አለቆች ላይ ይህን ሙሾ አሙሽ፥ እንዲህም በል፦ 2እናትህ ምን ነበረች? አንበሳ ነበረች፥ በአንበሶች መካከል ተጋደመች፥ በደቦል አንበሶች መካከል ግልገሎችዋን አሳደገች። 3ከግልገሎችዋም አንዱን አወጣች እርሱም ደቦል አንበሳ ሆነ፥ ንጥቂያንም ተማረ፥ ሰዎችንም በላ። 4አሕዛብም ወሬውን ሰሙ እርሱም በጕድጓዳቸው ተያዘ፥ በሰንሰለትም አድርገው ወደ ግብጽ ምድር ወሰዱት። 5እርስዋም እንደ ደከመችና ተስፋዋ እንደ ጠፋ ባየች ጊዜ፥ ከግልገሎችዋ ሌላን ወስዳ ደቦል አንበሳ አደረገችው። 6እርሱም በአንበሶች መካከል ተመላለሰ ደቦል አንበሳም ሆነ፥ ንጥቂያም ተማረ፥ ሰዎችንም በላ። 7ግንቦቻቸውንም አወቀ፥ ከተሞቻቸውንም አፈረሰ፥ ከግሣቱም ድምፅ የተነሣ ምድሪቱና ሞላዋ ጠፋች። 8አሕዛብም በዙሪያው ከየአገሩ ሁሉ ተሰበሰቡበት፥ መረባቸውንም በእርሱ ላይ ዘረጉ በጕድጓዳቸውም ተያዘ። 9በሰንሰለትም አድርገው በቀፎ ውስጥ አኖሩት ወደ ባቢሎንም ንጉሥ አመጡት፥ ድምፁም በእስራኤል ተራሮች ላይ ከዚያ ወዲያ እንዳይሰማ ወደ አምባ አገቡት።
10እናትህ በመልክህ በውኃ አጠገብ እንደ ተተከለች እንደ ወይን ግንድ ነበረች፥ ከውኃም ብዛት የተነሣ የምታፈራና የምትሰፋ ሆነች። 11ለእርስዋም ብርቱዎች በትሮች ነበሩአት እነርሱም ለነገሥታት በትሮች ነበሩ። ቁመታቸውም በዛፎች ቅርንጫፎች መካከል ረዘመ፥ በጫፎቻቸውም ብዛትና በርዝመታቸው ታዩ። 12ነገር ግን በመዓት ተነቀለች ወደ መሬትም ተጣለች የምሥራቅም ነፋስ ፍሬዋን አደረቀ፥ ብርቱዎች በትሮችዋም ተሰበሩና ደረቁ፥ እሳትም በላቻቸው። 13አሁንም በምድረ በዳ፥ በደረቅና በተጠማች መሬት ተተከለች። 14ከጫፎችዋም በትሮች እሳት ወጣች ፍሬዋንም በላች፥ የነገሥታትም በትር ይሆን ዘንድ የበረታ በትር የለባትም። ይህ ሙሾ ነው፥ ለልቅሶም ይሆናል።
Currently Selected:
ትንቢተ ሕዝቅኤል 19: አማ54
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ