የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ትንቢተ ሕዝቅኤል 17

17
1የእግዚአብሔር ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፦ 2የሰው ልጅ ሆይ፥ በእንቈቅልሽ አጫውት ለእስራኤልም ቤት ምሳሌ ንገር፥ እንዲህም በል፦ 3ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ታላቅ ክንፍ ረጅምም ማርገብገቢያ ያለው ላባም የተሞላ፥ መልከ ዝንጕርጕር ታላቅ ንስር ወደ ሊባኖስ መጣ፥ የዝግባንም ጫፍ ወሰደ። 4ቀንበጡንም ቀነጠበ ወደ ከነዓንም ምድር ወሰደው በነጋዶችም ከተማ አኖረው። 5ከምድርም ዘር ወሰደ በፍሬያማ እርሻ ተከለው በብዙም ውኃ አጠገብ እንደ አኻያ ዛፍ አኖረው። 6በበቀለም ጊዜ ቁመቱ ያጠረ አረጉም ወደ እርሱ የሚመለስ ሥሩም በበታቹ የነበረ ሰፊ ወይን ሆነ፥ እንዲሁ ወይን ሆነ አረግም ሰደደ ቀንበጥም አወጣ።
7ታላቅ ክንፍና ብዙ ላባም ያለው ሌላ ታላቅ ንስር ነበረ፥ እነሆም፥ ያጠጣው ዘንድ ይህ ወይን ሥሩን ወደ እርሱ አዘነበለ አረጉንም ከተተከለበት ከመደቡ ወደ እርሱ ሰደደ። 8አረግም ያወጣ ፍሬም ያፈራ የከበረም ወይን ይሆን ዘንድ በመልካም መሬት ውስጥ በብዙም ውኃ አጠገብ ተተክሎ ነበር። 9እንዲህም በል፦ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ በውኑ ይከናወንለት ይሆንን? ይደርቅስ ዘንድ፥ አዲስ የበቀለውስ ቅጠሉ ይጠወልግ ዘንድ ሥሩን አይነቅለውምን? ፍሬውንስ አይለቅመውምን? ሥሩም የተነቀለው በብርቱ ክንድና በብዙ ሕዝብ አይደለም። 10ተተክሎስ፥ እነሆ፥ ይከናወንለት ይሆንን? የምሥራቅ ነፋስ ባገኘው ጊዜ ፈጽሞ አይደርቅምን? በተተከለበት መደብ ላይ ይደርቃል።
11የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፦ 12ለዓመፀኛ ቤት፦ ይህ ትርጓሜ ምን እንደ ሆነ አታውቁምን? በላቸው። እንዲህም ብለህ ንገራቸው፦ እነሆ፥ የባቢሎን ንጉሥ ወደ ኢየሩሳሌም መጣ፥ ንጉሥዋንና መኳንንቶችዋንም ማረከ፥ ወደ እርሱም ወደ ባቢሎን ወሰዳቸው። 13ከመንግሥትም ዘር ወስዶ ቃል ኪዳን ከእርሱ ጋር አደረገ፥ አማለውም፥ የምድሪቱንም ኃያላን ወሰደ፥ 14ይኸውም ቃል ኪዳኑን በመጠበቅ እንድትጸና እንጂ መንግሥቱ እንድትዋረድና ከፍ እንዳትል ነው። 15እርሱ ግን በእርሱ ላይ ሸፈተ ፈረሶችንና ብዙንም ሕዝብ ይሰጡት ዘንድ መልእክተኞችን ወደ ግብጽ ላከ። በውኑ ይከናወንለት ይሆንን? ይህንስ ያደረገ ያመልጣልን? ቃል ኪዳንንስ አፍርሶ ያመልጣልን? 16እኔ ሕያው ነኝና ያነገሠውና መሐላውን የናቀበቱ፥ ቃል ኪዳኑንም ያፈረሰበቱ ንጉሥ በሚኖርበት ስፍራ ከእርሱ ጋር በባቢሎን መካከል በእርግጥ ይሞታል፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። 17ብዙዎችን ነፍሳት ለማስወገድ አፈርን በደለደሉ ምሽግም በሠሩ ጊዜ፥ ፈርዖን ከብዙ ሠራዊቱና ከታላቁ ጉባኤው ጋር በሰልፍ አይረዳውም። 18ቃል ኪዳኑንም በማፍረስ መሐላውን ንቆአል፥ እነሆም፥ እጅን ሰጠ፥ ይህንም ሁሉ አድርጎአል፥ ስለዚህ አያመልጥም። 19ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እኔ ሕያው ነኝና የናቀውን መሐላዬን ያፈረሰውንም ቃል ኪዳኔን በራሱ ላይ አመጣለሁ። 20መረቤንም በእርሱ ላይ እዘረጋለሁ በወጥመድም ይያዛል፥ ወደ ባቢሎንም አመጣዋለሁ በእኔም ላይ ስላደረገው ዓመፅ በዚያ ከእርሱ ጋር እፋረዳለሁ። 21ጭፍሮቹም ሁሉ በሰይፍ ይወድቃሉ፥ የቀሩትም ሁሉ ወደ እየነፋሳቱ ይበተናሉ፥ እኔም እግዚአብሔር እንደ ተናገርሁ ታውቃላችሁ።
22ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ከረጅሙ ዝግባ ጫፍ ላይ ቀንበጥን ወስጄ አኖረዋለሁ፥ ከጫፎቹ አንዱን ቀንበጥ እቀነጥበዋለሁ፥ በረጅምና በታላቅ ተራራም ላይ እተክለዋለሁ። 23ከፍ ባለው በእስራኤል ተራራ ላይ እተክለዋለሁ፥ ቅርንጫፎችም ያወጣል ፍሬም ያፈራል የከበረም ዝግባ ይሆናል፥ በበታቹም ወፎች ሁሉ ያርፋሉ፥ በቅርንጫፎቹም ጥላ በክንፍ የሚበርር ሁሉ ይጠጋል። 24የዱር ዛፎች ሁሉ ረጅሙን ዛፍ ዝቅ ያደረግሁ፥ አጭሩንም ዛፍ ከፍ ያደረግሁ፥ የለመለመውንም ዛፍ ያደረቅሁ፥ የደረቀውንም ዛፍ ያለመለምሁ እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ፥ እኔ እግዚአብሔር ተናግሬአለሁ እኔም አድርጌአለሁ።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ