ኦሪት ዘጸአት 8
8
2) ጓጉንቸር
1እግዚአብሔርም ሙሴን ተናገረው፤ “ወደ ፈርዖን ግባ፤ እንዲህም በለው፤ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፥ ‘ያገለግለኝ ዘንድ ሕዝቤን ልቀቅ። 2ለመልቀቅ እንቢ ብትል ግን እነሆ እኔ አገርህን ሁሉ በጓጕንቸሮች እመታለሁ፤ 3ወንዙም ጓጕንቸሮችን ያፈላል፤ ወጥተውም ወደ ቤትህ፥ ወደ መኝታ ቤትህ፥ ወደ አልጋህም፥ ወደ ባሪያዎችህም ቤት፥ በሕዝብህም ላይ፥ ወደ ምድጆችህም፥ ወደ ቡሃቃዎችህም ይገባሉ፤ 4ጓጕንቸሮችም በአንተ በሕዝብህም በባሪያዎችም ሁሉ ላይ ይወጣሉ።’” 5እግዚአብሔርም ሙሴን አለው፤ “አሮንን፥ ‘በትርህን ይዘህ በወንዞቹና በመስኖቹ በውኃ ማከማቻዎቹም ላይ እጅህን ዘርጋ፤ በግብፅም አገር ላይ ጓጕንቸሮችን አውጣ፤ በለው።” 6አሮንም በግብፅ ውኆች ላይ እጁን ዘረጋ፤ ጓጕንቸሮቹም ወጡ፤ የግብፅንም አገር ሸፈኑ። 7ጠንቍዮችም በአስማታቸው እንዲሁ አደረጉ፤ በግብፅም አገር ላይ ጓጕንቸሮችን አወጡ።
8ፈርዖንም ሙሴንና አሮንን ጠርቶ “ጓጕንቸሮቹን ከእኔ ከሕዝቤም እንዲያርቅ ወደ እግዚአብሔር ጸልዩልኝ፤ ለእግዚአብሔርም ይሠዋ ዘንድ ሕዝቡን እለቅቃለሁ፤” አላቸው። 9ሙሴም ፈርዖንን፥ “ጓጕንቸሮቹ ከአንተም ከቤቶችህም እንዲጠፋ፥ በወንዙም ብቻ እንዲቀሩ፥ ለአንተ ለባሪያዎችህም ለሕዝብህም መቼ እንድጸልይ አስታውቀኝ፤” አለው። 10እርሱም “ነገ” አለ። ሙሴም “አምላካችንን እግዚአብሔርን የሚመስል እንደሌለ ታውቅ ዘንድ እንደ ቃልህ ይሁን። 11ጓጕንቸሮቹም ከአንተ፥ ከቤቶችህም፥ ከባርያዎችህም፥ ከሕዝብህም ይሄዳሉ፤ በወንዙም ብቻ ይቀራሉ” አለ። 12ሙሴና አሮንም ከፈርዖን ዘንድ ወጡ። ሙሴም በፈርዖን ላይ ስላመጣቸው ጓጕንቸሮች ወደ እግዚአብሔር ጮኸ። 13እግዚአብሔርም ሙሴ እንዳለ አደረገ፤ ጓጕንቸሮቹም ከቤት ከወጀድም ከሜዳም ሞቱ። 14እንደ ክምርም አድርገው ሰበሰቡአቸው፤ ምድርም ገማች። 15ፈርዖንም ጸጥታ እንደሆነ ባየ ጊዜ ልቡን አደነደነ፤ እግዚአብሔርም እንደተናገረ አልሰማቸውም።
3) ቅማል
16እግዚአብሔርም ሙሴን አለው፤ “አሮንን፦ ‘በትርህን ዘርጋ፤ በግብፅም አገር ሁሉ ቅማል እንዲሆን የምድሩን ትቢያ ምታ፤’ በለው።” 17እንዲሁም አደረጉ፤ አሮንም እጁን ዘረጋ፤ በበትሩም የምድሩን ትቢያ መታው፤ በሰውና በእንስሳም ላይ ቅማል ሆነ፤ በግብፅ አገር ሁሉ የምድር ትቢያ ሁሉ ቅማል ሆነ። 18ጠንቍዮችም በአስማታቸው ያወጡ ዘንድ እንዲሁ አደረጉ፤ ነገር ግን አልቻሉም፤ ቅማሉም በሰውና በእንስሳ ላይ ነበረ። 19ጠንቍዮችም ፈርዖንን፥ “ይህስ የእግዚአብሔር ጣት ነው” አሉት፤ የፈርዖን ልብ ግን ጸና፤ እግዚአብሔርም እንደ ተናገረ አልሰማቸውም።
4) ተናካሽ ዝንብ
20እግዚአብሔርም ሙሴን አለው፤ “ማልደህ ተነሣ፤ በፈርዖንም ፊት ቁም፤ እነሆ እርሱ ወደ ውኃ ይወርዳል፤ እንዲህም በለው፤ ‘እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ 21እንዲያገለግለኝ ሕዝቤን ልቀቅ። ሕዝቤንም ባትለቅቅ፥ እነሆ በአንተ፥ በባሪያዎችህም፥ በሕዝብህም፥ በቤቶችህም ላይ የዝንብ መንጎች እሰድዳለሁ፤ የግብፃውያን ቤቶች የሚኖሩባትም ምድር ሁሉ በዝንብ መንጎች ይሞላሉ። 22በዚያን ቀን በምድር መካከል እኔ እግዚአብሔር እንደሆንሁ ታውቅ ዘንድ፥ በዚያ የዝንብ መንጋ እንዳይሆን ሕዝቤ የሚቀመጥባትን የጌሤምን ምድር እለያለሁ። 23በሕዝቤና በሕዝብህ መካከል እለያለሁ፤ ይህም ተአምራት ነገ ይሆናል።’” 24እግዚአብሔርም እንዲሁ አደረገ፤ በፈርዖንም ቤት፥ በባሪያዎቹም ቤቶች ውስጥ ብዙ የዝንብ መንጋ መጣ፤ በግብፅም አገር ሁሉ ላይ ከዝንቡ መንጋ የተነሣ ምድር ጠፋች።
25ፈርዖንም ሙሴንና አሮንን ጠርቶ፥ “ሂዱ፤ በአገሩ ውስጥ ለአምላካችሁ ሠዉ፤” አላቸው። 26ሙሴም፦ “ለእግዚአብሔር ለአምላካችን የግብፃውያንን ርኩሰት እንሰዋለንና እንዲህ ይደረግ ዘንድ አይገባም፤ እነሆ እኛ የግብፃውያንን ርኵሰት በፊታቸው ብንሠዋ አይወግሩንምን? 27እኛስ ለእግዚአብሔር ለአምላካችን እንሠዋ ዘንድ እንደሚያዝዘን የሦስት ቀን መንገድ ወደ ምድረ በዳ እንሄዳለን፤” አለ። 28ፈርዖንም፥ “ለእግዚአብሔር ለአምላካችሁ በምድረ በዳ ትሠዉ ዘንድ እለቅቃችኋለሁ፤ ነገር ግን ርቃችሁ አትሂዱ፤ ጸልዩልኝ፤” አለ። 29ሙሴም፥ “እነሆ ከአንተ ዘንድ እወጣለሁ፤ የዝንቡም መንጎች ከፈርዖን፥ ከባሪያዎቹም፥ ከሕዝቡም ነገ እንዲሄዱ ወደ እግዚአብሔር እጸልያለሁ፤ ነገር ግን ለእግዚአብሔር ይሠዋ ዘንድ ሕዝቡን እንዳይለቅቅ ፈርዖን እንደገና አያታልለን” አለ። 30ሙሴም ከፈርዖን ዘንድ ወጣ፤ ወደ እግዚአብሔርም ጸለየ። 31እግዚአብሔርም ሙሴ እንዳለ አደረገ፤ የዝንቡንም መንጎች ከፈርዖን ከባሪያዎቹም ከህዝቡም አስነሣ፤ አንድ ስንኳ አልቀረም። 32ፈርዖንም በዚህ ጊዜ ደግሞ ልቡን አደነደነ፤ ሕዝቡንም አልለቀቀም።
Currently Selected:
ኦሪት ዘጸአት 8: አማ54
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ