ኦሪት ዘጸአት 34
34
1እግዚአብሔርም ሙሴን አለው፦ ሁለት የድንጋይ ጽላቶች እንደ ፊተኞች አድርገህ ጥረብ፤ በሰበርኻቸው በፊተኞቹ ጽላቶች የነበሩትን ቃሎች እጽፍባቸዋለሁ። 2ነገም የተዘጋጀህ ሁን፥ በማለዳም ወደ ሲና ተራራ ወጥተህ በዚያ በተራራው ራስ ላይ በፊቴ ቁም። 3ከአንተም ጋር ማንም ሰው አይውጣ፥ በተራራውም ሁሉ ማንም አይታይ፤ መንጎችና ከብቶችም በዚያ ተራራ ፊት አይሰማሩ። 4ሙሴም እንደ ፊተኞቹ አድርጐ ሁለት የድንጋይ ጽላቶች ጠረበ፤ በነጋውም ማልዶ እግዚአብሔር እንዳዘዘው ወደ ሲና ተራራ ወጣ፥ ሁለቱንም የድንጋይ ጽላቶች በእጁ ወሰደ፥ 5እግዚአብሔርም በደመናው ውስጥ ወረደ፥ በዚያም ከእርሱ ጋር ቆመ፥ የእግዚአብሔርንም ስም አወጀ። 6እግዚአብሔርም በፊቱ አልፎ፦ እግዚአብሔር፥ እግዚአብሔር መሐሪ፥ ሞገስ ያለው፥ ታጋሽም፥ ባለ ብዙ ቸርነትና እውነት፥ 7እስከ ሺህ ትውልድም ቸርነትን የሚጠብቅ፥ አበሳንና መተላለፍን ኃጢአትንም ይቅር የሚል፥ በደለኛውንም ከቶ የማያነጻ፥ የአባቶችንም ኃጢአት በልጆች እስከ ሦስትና እስከ አራት ትውልድም በልጅ ልጆች የሚያመጣ አምላክ ነው ሲል አወጀ። 8ሙሴም ፈጥኖ ወደ መሬት ተጐነበሰና ሰገደ፦ 9አቤቱ በፊትህስ ሞገስን አግኝቼ እንደ ሆነ፥ ይህ አንገተ ደንዳና ሕዝብ ነውና ጌታዬ በመካከላችን ይሂድ፤ ጠማማነታችንንና ኃጢአታችንንም ይቅር በለን፥ ለርስትህም ተቀበለን አለ። 10እርሱም አለው፦ እነሆ እኔ ቃል ኪዳን አደርጋለሁ፤ በምድር ሁሉ፥ በአሕዛብም ሁሉ ዘንድ እንደ እርሱ ያለ ከቶ ያልተደረገውን ተአምራት በሕዝብህ ሁሉ ፊት አደርጋለሁ፤ እኔም በአንተ ዘንድ የምሠራው ነገር የሚያስፈራ ነውና አንተ ያለህበት ይህ ሕዝብ ሁሉ የእግዚአብሔርን ሥራ ያያል። 11በዚህ ቀን የማዝዝህን ነገር ጠብቅ፤ እነሆ እኔ አሞራዊውን ከነዓናዊውንም ኬጢያዊውንም ፌርዛዊውንም ኤዊያዊውንም ኢያቡሳዊውንም በፊትህ አወጣለሁ። 12በመካከልህ ወጥመድ እንዳይሆኑብህ አንተ በምትሄድባት ምድር ከሚኖሩ ሰዎች ጋር ቃል ኪዳን እንዳታደርግ ተጠንቀቅ፤ 13ነገር ግን መሠዊያዎቻቸውን ታፈርሳላችሁ፥ ሐውልቶቻቸውንም ትሠብራላችሁ፥ የማምለኪያ ዓፀዶቻቸውንም ትቈርጣላችሁ፤ 14ስሙ ቀናተኛ የሆነ እግዚአብሔር ቅንዓት ያለው አምላክ ነውና ለሌላ አምላክ አትስገድ። 15በዚያች ምድር ከሚኖሩ ሰዎች ጋር ቃል ኪዳን እንዳታደርግ፥ እነርሱ አምላኮቻቸውን ተከትለው ባመነዘሩና በሠዉላቸው ጊዜ እንዳይጠሩህ፥ ከመሥዋዕታቸውም እንዳትበላ፥ 16ሴት ልጆቻቸውንም ከወንድ ልጆችህ ጋር እንዳታጋባ፥ ልጆቻቸውም አምላኮቻቸውን ተከትለው ሲያመነዝሩ ከአምላኮቻቸው በኋላ ሄደው አመንዝረውም ልጆችህን እንዳያስቱ ተጠንቀቅ። 17ቀልጠው የተሠሩትን የአማልክት ምስሎች ለአንተ አታድርግ። 18የቂጣውን በዓል ትጠብቀዋለህ። በአቢብ ወር ከግብፅ ወጥተሃልና በታዘዘው ዘመን በአቢብ ወር እንዳዘዝሁህ ሰባት ቀን ቂጣ እንጀራ ብላ። 19ማኅፀንንም የሚከፍት ሁሉ የእኔ ነው፤ የከብትህም ተባት በኵር ሁሉ፥ በሬም ቢሆን በግም ቢሆን፥ የእኔ ነው። 20የአህያውንም በኵር በጠቦት ትዋጀዋለህ፤ ባትዋጀውም አንገቱን ትሰብረዋለህ። የልጆችህንም በኵር ሁሉ ትዋጃለህ። በፊቴም አንድ ሰው ባዶ እጁን አይታይ። 21ስድስት ቀን ትሠራለህ፥ በሰባተኛውም ቀን ታርፋለህ፤ በምታርስበትና በምታጭድበት ዘመን ታርፋለህ። 22የሰባቱንም ሱባዔ በዓል ታደርጋለህ፥ እርሱም የስንዴ መከር በኵራት ነው፤ በዓመቱም ፍጻሜ የመክተቻ በዓል ታደርጋለህ። 23በአንተ ዘንድ ያለው ወንድ ሁሉ በእስራኤል አምላክ በጌታ በእግዚአብሔር ፊት በዓመት ሦስት ጊዜ ይታይ። 24አሕዛብን ከፊትህ አወጣለሁ፥ አገርህንም አሰፋለሁ፤ በአምላክህም በእግዚአብሔር ፊት ለመታየት በዓመት ሦስት ጊዜ ስትወጣ ማንም ምድርህን አይመኝም። 25የመሥዋዕቴን ደም ከቦካ እንጀራ ጋር አትሠዋ፤ የፋሲካውም በዓል መሥዋዕት እስከ ነገ አይደር። የተመረጠውን የምድርህን ፍሬ በኵራት ወደ አምላክህ ወደ እግዚአብሔር ቤት ታገባለህ። 26ጠቦቱን በእናቱ ወተት አትቀቅልም። 27እግዚአብሔርም ሙሴን፦ በእነዚህ ቃሎች መጠን ከአንተና ከእስራኤል ጋር ቃል ኪዳን አድርጌአለሁና እነዚህን ቃሎች ጻፍ አለው። 28በዚያም አርባ ቀንና አርባ ሌሊት ከእግዚአብሔር ጋር ነበረ፤ እንጀራም አልበላም፥ ውኃም አልጠጣም። በጽላቶቹም አሥሩን የቃል ኪዳን ቃሎች ጻፈ። 29እንዲህም ሆነ፤ ሙሴ ከሲና ተራራ በወረደ ጊዜ ሁለቱ የምስክር ጽላቶች በሙሴ እጅ ነበሩ፤ ሙሴም ከተራራው በወረደ ጊዜ እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ስለ ተነጋገረ የፊቱ ቁርበት እንዳንጸባረቀ አላወቀም ነበር። 30አሮንና የእስራኤል ልጆች ሁሉ ሙሴን ባዩ ጊዜ፥ እነሆ የፊቱ ቁርበት አንጸባረቀ፤ ወደ እርሱም ይቀርቡ ዘንድ ፈሩ። 31ሙሴም ጠራቸው፤ አሮንም የማኅበሩን አለቆች ሁሉ ወደ እርሱ ተመለሱ፤ ሙሴም ተናገራቸው። 32ከዚያም በኋላ የእስራኤል ልጆች ሁሉ ቀረቡ፤ እግዚአብሔርም በሲና ተራራ የተናገረውን ነገር ሁሉ አዘዛቸው። 33ሙሴም ለእነርሱ ተናግሮ ከጨረሰ በኋላ በፊቱ መሸፈኛ አደረገ። 34ሙሴም ከእርሱ ጋር ሲነጋገር ወደ እግዚአብሔር በገባ ጊዜ እስኪ ወጣ ድረስ መሸፈኛውን ከፊቱ አነሣ፤ በወጣም ጊዜ ለእስራኤል ልጆች የታዘዘውን ነገር ነገረ። 35የእስራኤልም ልጆች የሙሴን ፊት ቁርበት እንዳንጸባረቀ ያዩ ነበር፤ እርሱም ከእርሱ ጋር ሊነጋገር እስኪገባ ድረስ እንደ ገና በፊቱ መሸፈኛ ያደርግ ነበር።
Currently Selected:
ኦሪት ዘጸአት 34: አማ54
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ