የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ኦሪት ዘጸአት 29

29
1እኔንም በክህነት እንዲያገለግሉኝ ትቀድሳቸው ዘንድ የምታደርግባቸው ነገር ይህ ነው፤ ነውር የሌለባቸውን አንድ ወይፈንና ሁለት አውራ በጎች ትወስዳለህ። 2ቂጣ እንጀራ፥ በዘይትም የተለወሰ የቂጣ እንጎቻ፥ በዘይትም የተቀባ ስስ ቂጣ ከመልካም ስንዴ ታደርጋለህ። 3በአንድ ሌማትም ታደርጋቸዋለህ፤ ከወይፈኑና ከሁለቱ አውራ በጎች ጋር በሌማቱ ታቀርባቸዋለህ። 4አሮንና ልጆቹንም ወደ መገናኛው ድንኳን ታቀርባቸዋለህ፥ በውኃም ታጥባቸዋለህ። 5ልብሶችን ወስደህ ለአሮን ሸሚዝና የኤፉድ ቀሚስ ኤፉድም የደረት ኪስም ታለብሰዋለህ፥ በብልሃትም በተጠለፈ ቍድ ታስታጥቀዋለህ፤ 6መጠምጠሚያውንም በራሱ ላይ ታደርጋለህ፥ የተቀደሰውንም አክሊል በመጠምጠሚያው ላይ ታኖራለህ። 7የቅብዓትንም ዘይት ወስደህ በራሱ ላይ ታፈስሰዋለህ፥ ትቀባውማለህ። 8ልጆቹንም ታቀርባቸዋለህ፥ ሸሚዞቹንም ታለብሳቸዋለህ። 9አሮንንና ልጆቹንም በመታጠቂያ ታስታጥቃቸዋለህ፥ ቆብንም ታለብሳቸዋለህ፤ ለዘላለም ሥርዓትም ክህነት ይሆንላቸዋል፤ እንዲሁም አሮንንና ልጆቹን ትክናቸዋለህ። 10ወይፈኑንም ወደ መገናኛው ድንኳን በር ፊት ታቀርበዋለህ፤ አሮንና ልጆቹም እጆቻቸውን በወይፈኑ ራስ ላይ ይጭናሉ። 11ወይፈኑንም በመገናኛው ድንኳን በር አጠገብ በእግዚአብሔር ፊት ታርደዋለህ። 12ከወይፈኑም ደም ወስደህ በመሠዊያው ቀንዶች ላይ በጣትህ ትረጨዋለህ፤ ደሙንም ሁሉ ከመሠዊያው በታች ታፈስሰዋለህ። 13የሆድ ዕቃውንም የሚሸፍነውን ስብ ሁሉ በጉልበቱም ላይ ያለውን መረብ ሁለቱንም ኵላሊቶች በላያቸውም ያለውን ስብ ወስደህ በመሠዊያው ላይ ታቃጥላለህ። 14የወይፈኑን ሥጋ ግን፥ ቁርበቱንም፥ ፈርሱንም ከሰፈር ውጭ በእሳት ታቃጥለዋለህ፤ የኃጢአት መሥዋዕት ነው። 15አንደኛውንም አውራ በግ ትወስደዋለህ፤ አሮንና ልጆቹም በአውራው በግ ራስ ላይ እጆቻቸውን ይጭናሉ። 16አውራውንም በግ ታርደዋለህ፥ ደሙንም ወስደህ በመሠዊያው ላይ በዙሪያው ትረጨዋለህ። 17የአውራውንም በግ በየብልቱ ትቆርጠዋለህ፥ የሆድ ዕቃውንና እግሮቹንም ታጥባለህ፥ ከብልቱና ከራሱም ጋር ታኖረዋለህ። 18አውራውንም በግ በሞላው በመሠዊያው ላይ ታቃጥላለህ፤ ለእግዚአብሔር የሚቃጠል መሥዋዕት ነው፤ ጣፋጭ ሽቱ ነው። ለእግዚአብሔር የቀረበ የእሳት ቍርባን ነው። 19ሁለተኛውንም አውራ በግ ትወስደዋለህ፤ አሮንና ልጆቹም እጆቻቸውን በአውራው በግ ራስ ላይ ይጭናሉ። 20አውራውንም በግ ታርደዋለህ፥ ደሙንም ትወስዳለህ፥ የአሮንንም የቀኝ ጆሮ ጫፍ፥ የልጆቹንም የቀኝ ጆሮአቸውን ጫፍ፥ የቀኝ እጃቸውንና የቀኝ እግራቸውን አውራ ጣት ታስነካለህ፤ ደሙንም በመሠዊያው ላይ በዙሪያው ትረጨዋለህ። 21በመሠዊያውም ላይ ካለው ደም ከቅብዓት ዘይትም ወስደህ በአሮንና በልብሱ ላይ፥ ከእርሱም ጋር ባሉት በልጆቹና በልብሶቻቸው ላይ ትረጨዋለህ፤ እርሱም ልብሶቹም፥ ከእርሱም ጋር ልጆቹ ልብሶቻቸውም ይቀደሳሉ። 22ደግሞም የሚካኑበት አውራ በግ ነውና የበጉን ስብ፥ ላቱንም፥ የሆድ ዕቃውንም የሚሸፍነውን ስብ፥ በጉበቱም ላይ ያለውን መረብ፥ ሁለቱንም ኵላሊቶች በላያቸውም ያለውን ስብ፥ የቀኙንም ወርች ትወስዳለህ። 23አንድ እንጀራ፥ አንድም የዘይት እንጀራ፥ አንድም ስስ ቂጣ በእግዚአብሔር ፊት በሌማት ካለው ቂጣ እንጀራ ትወስዳለህ፤ 24ሁሉንም በአሮን እጆችና በልጆቹ እጆች ታኖረዋለህ፤ ለሚወዘወዝ ቍርባን በእግዚአብሔር ፊት ትወዘውዘዋለህ። 25ከእጃቸውም ትቀበለዋለህ፥ በመሠዊያውም ላይ ከሚቃጠል መሥዋዕት ጋር በእግዚአብሔር ፊት ጣፋጭ ሽቱ እንዲሆን ታቃጥለዋለህ፤ እርሱ ለእግዚአብሔር የእሳት ቍርባን ነው። 26ለአሮንም ክህነት የታረደውን በግ ፍርምባ ወስደህ ለሚወዘወዝ ቍርባን በእግዚአብሔር ፊት ትወዘውዘዋለህ፤ እርሱም የአንተ ወግ ይሆናል። 27ከሚካኑበትም አውራ በግ የተወሰደ ለአሮንና ለልጆቹ ወግ የሚሆን ለመሥዋዕት የተወዘወዘውን ፍርምባና የተነሣውን ወርች ትቀድሳለህ። 28ያውም የማንሣት ቍርባን ነውና ከእስራኤል ልጆች ዘንድ ለዘላለም የአሮንና የልጆቹ ወግ ይሁን፤ የእስራኤል ልጆች የሚያቀርቡት የደኅንነት መሥዋዕታቸው የማንሣት ቍርባን ይሆናል፤ ለእግዚአብሔር የማንሣት ቍርባን ይሆናል። 29የተቀደሰውም የአሮን ልብስ ይቀቡበትና ይካኑበት ዘንድ ከእርሱ በኋላ ለልጆቹ ይሁን። 30ከልጆቹም በእርሱ ፈንታ ካህን የሚሆነው በመቅደስ ለማገልገል ወደ መገናኛው ድንኳን ሲገባ ሰባት ቀን ይልበሰው። 31የሚካንበትንም አውራ በግ ወስደህ ሥጋውን በተቀደሰ ስፍራ ትቀቅለዋለህ። 32አሮንና ልጆቹም የአውራውን በግ ሥጋ በሌማትም ያለውን እንጀራ በመገናኛው ድንኳን በር ይበሉታል። 33የተካኑና የተቀደሱ ይሆኑ ዘንድ ማስተስረያ የሆነውን ነገር ይብሉት፤ ሌላ ሰው ግን አይብላው፤ የተቀደሰ ነውና። 34የተካኑበትም ሥጋ ወይም እንጀራ ተርፎ ቢያድር፥ የቀረውን በእሳት ታቃጥለዋለህ፤ የተቀደሰ ነውና አይበላም። 35እንዳዘዝሁህም ሁሉ በአሮንና በልጆቹ እንዲህ አድርግ፤ ሰባት ቀን ትክናቸዋለህ። 36ዕለት ዕለትም ስለ ማስተስረይ ለኃጢአት መሥዋዕት ወይፈኑን ታቀርባለህ፤ ማስተስረያም ባደረግህ ጊዜ መሠዊያውን ታነጻዋለህ፤ ቅዱስም ይሆን ዘንድ ትቀባዋለህ። 37ሰባት ቀን ለመሠዊያው ማስተስረያ ታደርጋለህ፥ ትቀድሰውማለህ፤ መሠዊያውም ቅድስተ ቅዱሳን ይሆናል፤ መሠዊያውንም የሚነካ ሁሉ ቅዱስ ይሆናል። 38በመሠዊያውም ላይ የምታቀርበው ይህ ነው፤ በቀን በቀን ዘወትር ሁለት የዓመት ጠቦቶች ታቀርባለህ። 39አንዱን ጠቦት በማለዳ ቍርባን አድርገህ ታቀርበዋለህ፤ ሁለተኛውንም ጠቦት በማታ ቍርባን አድርገህ ታቀርበዋለህ። 40ከአንዱ ጠቦትም ጋር የኢን መስፈሪያ አራተኛ እጅ በሆነ ተወቅጦ በተጠለለ ዘይት የተለወሰ የኢፍ መስፈሪያ አሥረኛ እጅ መልካም ዱቄት፥ ደግሞ ለመጠጥ ቍርባን የኢን መስፈሪያ አራተኛ እጅ የወይን ጠጅ ታቀርባለህ። 41ሁለተኛውንም ጠቦት በማታ ታቀርበዋለህ፥ እንደ ማለዳውም የእህልና የመጠጥ ቍርባን ታደርግበታለህ፤ ለእግዚአብሔር ጣፋጭ ሽቱ እንዲሆን የእሳት ቍርባን ይሆናል። 42ለአንተ እናገር ዘንድ ከእናንተ ጋር በምገናኝበት በመገናኛው ድንኳን ደጃፍ፥ በእግዚአብሔር ፊት ይህ ዘወትር ለልጅ ልጃችሁ የሚቃጠል መሥዋዕት ይሆናል። 43ከእስራኤልም ልጆች ጋር በዚያ እገናኛለሁ፤ ድንኳኑም በክብሬ ይቀደሳል። 44የመገናኛውንም ድንኳን መሠዊያውንም እቀድሳለሁ፤ በክህነትም ያገለግሉኝ ዘንድ አሮንንና ልጆቹን እቀድሳለሁ። 45በእስራኤልም ልጆች መካከል እኖራለሁ፥ አምላክም እሆናቸዋለሁ። 46በመካከላቸውም እኖር ዘንድ ከግብፅ ምድር ያወጣኋቸው አምላካቸው እግዚአብሔር እኔ እንደ ሆንሁ ያውቃሉ፤ እኔ አምላካቸው እግዚአብሔር ነኝ።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ