መጽሐፈ አስቴር 8
8
1በዚያም ቀን ንጉሡ አርጤክስስ የአይሁድን ጠላት የሐማን ቤት ለንግሥቲቱ ለአስቴር ሰጠ። አስቴርም ለእርስዋ ምን እንደ ሆነ ነግራው ነበርና መርዶክዮስ ወደ ንጉሡ ፊት ገባ። 2ንጉሡም ከሐማ ያወለቀውን ቀለበቱን አወጣ፥ ለመርዶክዮስም ሰጠው። አስቴርም በሐማ ቤት ላይ መርዶክዮስን ሾመች።
3አስቴርም እንደ ገና በንጉሡ ፊት ተናገረች፥ በእግሩም ላይ ወድቃ እያለቀሰች የአጋጋዊውን የሐማን ክፋትና በአይሁድ ላይ የተተነኰለውን ተንኰል ይሽር ዘንድ ለመነችው። 4ንጉሡም የወርቁን ዘንግ ለአስቴር ዘረጋላት፥ አስቴርም ተነሥታ በንጉሡ ፊት ቆመችና፦ 5ንጉሡን ደስ ቢያሰኘው፥ በፊቱም ሞገስ አግኝቼ እንደሆነ፥ ይህም ነገር በፊቱ ቅን ቢሆን፥ እኔም በእርሱ ዘንድ ተወድጄ እንደ ሆነ፥ አጋጋዊው የሐመዳቱ ልጅ ሐማ በንጉሡ አገር ሁሉ ያሉትን አይሁድ ለማጥፋት የጻፈው ተንኰል ይገለበጥ ዘንድ ይጻፍ። 6እኔ በሕዝቤ ላይ የሚወርደውን ክፉ ነገር አይ ዘንድ እንዴት እችላለሁ? ወይስ የዘመዶቼን ጥፋት አይ ዘንድ እንዴት እችላለሁ? አለች። 7ንጉሡም አርጤክስስ ንግሥቲቱን አስቴርንና አይሁዳዊውን መርዶክዮስን፦ እነሆ የሐማን ቤት ለአስቴር ሰጥቻለሁ፥ እርሱም እጆቹን በአይሁድ ላይ ስለ ዘረጋ በግንድ ላይ ተሰቀለ። 8በንጉሡ ስም የተጻፈና በንጉሡ ቀለበት የታተመ አይገለበጥምና እናንተ ደግሞ ደስ የሚያሰኛችሁን በንጉሡ ስም ስለ አይሁድ ጻፉ፥ በንጉሡም ቀለበት አትሙ አላቸው።
9በዚያን ጊዜም ኒሳን በተባለው በመጀመሪያው ወር ከወሩም በሀያ ሦስተኛው ቀን የንጉሡ ጸሐፊዎች ተጠሩ፥ መርዶክዮስም ስለ አይሁድ እንዳዘዘው ሁሉ ከህንድ ጀምሮ እስከ ኢትዮጵያ ድረስ በመቶ ሀያ ሰባቱ አገሮች ላሉ ሹማምትና አለቆች አዛውንትም ለእያንዳንዱም አገር እንደ ጽሕፈቱ ለእያንዳንዱም ሕዝብ እንደ ቋንቋው ለአይሁድም እንደ ጽሕፈታቸውና እንደ ቋንቋቸው ተጻፈ። 10በንጉሡም በአርጤክስስ ስም አስጻፈው፥ በንጉሡም ቀለበት አሳተመው፥ ደብዳቤውንም በንጉሡ ፈረስ ቤት በተወለዱት፥ ለንጉሡም አገልግሎት በተለዩ በፈጣን ፈረሶች በተቀመጡ መልእክተኞች እጅ ሰደደው። 11በዚያም ደብዳቤ በከተሞቹ ሁሉ የሚኖሩት አይሁድ እንዲሰበሰቡ፥ ለሕይወታቸውም እንዲቆሙ፥ በጥል የሚነሡባቸውን የሕዝቡንና የአገሩን ሠራዊት ሁሉ ከሕፃናቶቻቸውና ከሴቶቻቸው ጋር እንዲያጠፉና እንዲገድሉ እንዲደመስሱም፥ ምርኮአቸውንም እንዲዘርፉ ንጉሡ ፈቀደላቸው። 12ይህም አዳር በሚባለው በአሥራ ሁለተኛው ወር በአሥራ ሦስተኛው ቀን በንጉሡ በአርጤክስስ አገሮች ሁሉ በአንድ ቀን እንዲሆን ነው።
13አይሁድም ጠላቶቻቸውን እንዲበቀሉ በዚያ ቀን ይዘጋጁ ዘንድ የደብዳቤው ቅጅ በየአገሩ ላሉ አሕዛብ ሁሉ ታወጀ። 14ለንጉሡ አገልግሎት በተለዩ በፈጣን ፈረሶች የተቀመጡት መልእክተኞች በንጉሡ ትእዛዝ ተርበትብተውና ቸኵለው ወጡ፥ አዋጁም በሱሳ ግንብ ተነገረ።
15መርዶክዮስም በሰማያዊና በነጭ ሐር የተሠራውን የንጉሡን የክብር ልብስ ለብሶ ታላቅም የወርቅ አክሊል ደፍቶ ከጥሩ በፍታና ከሐምራዊ ግምጃ የተሠራ መጐናጸፊያ ተጐናጽፎ ከንጉሡ ፊት ወጣ፥ የሱሳም ከተማ ደስ አላት፥ እልልም አለች። 16ለአይሁድም ብርሃንና ደስታ ተድላና ክብርም ሆነ። 17የንጉሡም ትእዛዝና አዋጅ በደረሰበት አገርና ከተማ ሁሉ ለአይሁድ ደስታና ተድላ፥ የግብዣም ቀን መልካምም ቀን ሆነ። አይሁድንም መፍራት ስለ ወደቀባቸው ከምድር አሕዛብ ብዙ ሰዎች አይሁድ ሆኑ።
Currently Selected:
መጽሐፈ አስቴር 8: አማ54
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ