ኦሪት ዘዳግም 23:1-11

ኦሪት ዘዳግም 23:1-11 አማ54

ቍላው የተቀጠቀጠ ብልቱም የተቈረጠ ወደ እግዚአብሔር ጉባኤ አይግባ። ዲቃላ ወደ እግዚአብሔር ጉባኤ አይግባ፤ እስከ አሥር ትውልድ ድረስ ወደ እግዚአብሔር ጉባኤ አይግባ። ከግብፅ በወጣችሁ ጊዜ እንጀራና ውኃ ይዘው በመንገድ ላይ አልተቀበሉአችሁምና፥ በመስጴጦምያ ካለው ከፋቱራ የቢዖርን ልጅ በለዓምን ዋጋ ሰጥተው ይረግምህ ዘንድ አምጥተውብሃልና አሞራዊና ሞዓባዊ ወደ እግዚአብሔር ጉባኤ አይግባ፤ እስከ አሥር ትውልድ ድረስ ለዘላለም ወደ እግዚአብሔር ጉባኤ አይግባ። ነገር ግን አምላክህ እግዚአብሔር በለዓምን ይሰማ ዘንድ አልወደደም፤ አምላክህም እግዚአብሔር ወድዶሃልና እርግማኑን በረከት አደረገልህ። በዘመንህ ሁሉ ለዘላለም ሰላምና ልማት ለእነርሱ አትሻ። ኤዶማዊ ወንድምህ ነውና አትጸየፈው፤ ግብፃዊውንም በአገሩ ስደተኛ ነበርህና አትጸየፈው። ከእነርሱም በሦስተኛው ትውልድ የሚወለዱ ልጆች ወደ እግዚአብሔር ጉባኤ ይግቡ። ጠላቶችህን ልትወጋ በወጣህ ጊዜ ከክፉ ነገር ሁሉ ሰውነትህን ጠብቅ። በእናንተ መካከል ሌሊት በሚሆነው ርኩሰት የረከስ ሰው ቢኖር፥ ከሰፈር ወደ ውጭ ይውጣ፥ ወደ ሰፈርም አይግባ። በመሸም ጊዜ በውኃ ይታጠብ፤ ፀሐይም በገባ ጊዜ ወደ ሰፈር ይመለስ።