የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ኦሪት ዘዳግም 12

12
1በምድር ላይ በምትኖሩበት ዘመን ሁሉ የአባቶቻችሁ አምላክ እግዚአብሔር ለመውረስ በሰጣችሁ አገር፥ የምትጠብቁአትና የምታደርጉአት ሥርዓትና ፍርድ እነዚህ ናቸው። 2እናንተ የምትወርሱአቸው አሕዛብ አማልክቶቻቸውን ያመለኩባቸውን በረጅም ተራሮች በኮረብቶችም ላይ ከለምለምም ዛፍ በታች ያለውን ስፍራ ሁሉ ፈጽማችሁ አጥፉአቸው፤ 3መሠዊያቸውንም አፍርሱ፥ ሐውልቶቻቸውንም ሰባብሩ፥ የማምለኪያ ዐፀዶቻቸውንም በእሳት አቃጥሉ፥ የአማልክቶቻቸውንም የተቀረጹ ምስሎች አንከታክቱ፤ ከዚያም ስፍራ ስማቸውን አጥፉ። 4ለአምላካችሁ ለእግዚአብሔር እንዲህ ያለ ሥራ አትሥሩ። 5ነገር ግን አምላካችሁ እግዚአብሔር ከነገዶቻችሁ ሁሉ ስሙን በዚያ ያኖር ዘንድ ወደዚያ ወደ መረጠው ስፍራ ትመጣላችሁ፥ ማደሪያውንም ትሻላችሁ። 6ወደዚያም የሚቃጠለውን መሥዋዕታችሁን፥ ሌላ መሥዋዕታችሁንም፥ አሥራታችሁንም፥ በእጃችሁም ያነሣችሁትን ቍርባን፥ ስእለታችሁንም፥ በፈቃዳችሁ የምታቀርቡትን፥ የላማችሁንና የበጋችሁንም በኵራት ውሰዱ። 7በዚያም በአምላካችሁ በእግዚአብሔር ፊት ብሉ፥ እጃችሁንም በምትዘረጉበት፥ አምላክህ እግዚአብሔር በባረከህ ነገር ሁሉ፥ እናንተና ቤተሰባችሁ ደስ ይበላችሁ። 8ሰው ሁሉ በፊቱ መልካም መስሎ የታየውን፥ እኛ በዚህ ዛሬ የምናደርገውን ሁሉ አታደርጉም፤ 9አምላካችሁ እግዚአብሔር ወደሚሰጣችሁ ዕረፍትና ርስት እስከ ዛሬ ድረስ አልገባችሁምና። 10ዮርዳኖስን ግን በተሻገራችሁ ጊዜ፥ አምላካችሁም እግዚአብሔር በሚያወርሳችሁ ምድር በተቀመጣችሁ ጊዜ፥ ያለ ፍርሃትም እንድትኖሩ ከከበቡአችሁ ጠላቶች ሁሉ ዕረፍት በሰጣችሁ ጊዜ፥ 11በዚያን ጊዜ አምላካችሁ እግዚአብሔር ስሙ ይጠራበት ዘንድ ወደዚያ ወደ መረጠው ስፍራ፥ እኔ የማዝዛችሁን ሁሉ፥ የሚቃጠለውን መሥዋዕታችሁን፥ ሌላ መሥዋዕታችሁንም፥ አሥራታችሁንም፥ በእጃችሁ ያነሣችሁትንም ቍርባን፥ ለእግዚአብሔርም ተስላችሁ የመረጣችሁትን ስእለታችሁን ሁሉ ውሰዱ። 12እናንተም፥ ወንዶች ልጆቻችሁና ሴቶች ልጆቻችሁም፥ ባሪያዎቻችሁም፥ ገረዶቻችሁም፥ ከእናንተ ጋር ክፍልና ርስት ስለሌለው በደጆቻችሁ ውስጥ የተቀመጠው ሌዋዊም በአምላካችሁ በእግዚአብሔር ፊት ደስ ይበላችሁ። 13የሚቃጠለውን መሥዋዕትህን በሚታይህ ስፍራ ሁሉ እንዳታቀርብ ተጠንቀቅ። 14ነገር ግን እግዚአብሔር ከነገዶችህ ከአንዱ ዘንድ በመረጠው ስፍራ በዚያ የሚቃጠለውን መሥዋዕትህን አቅርብ፥ በዚያም የማዝዝህን ሁሉ አድርግ። 15ነገር ግን አምላክህ እግዚአብሔር እንደ ሰጠህ በረከት፥ ሰውነትህ እንደ ፈቀደ፥ በደጆችህ ሁሉ ውስጥ አርደህ ብላ፤ ንጹሕ ሰው ንጹሕም ያልሆነ ሰው እንደ ሚዳቍና እንደ ዋላ ያለውን ይብላው። 16ደሙን ግን እንደ ውኃ በምድር ላይ አፍስሰው እንጂ አትብላው። 17የእህልህን የወይን ጠጅህን የዘይትህንም አሥራት፥ የላምህንና የበግህንም በኵራት፥ የተሳልኸውንም ስእለት ሁሉ፥ በፈቃድህም ያቀረብኸውን፥ በእጅህም ያነሣኸውን ቍርባን በደጆችህ ውስጥ መብላት አትችልም። 18ነገር ግን አንተ፥ ወንዶችና ሴቶች ልጆችህም፥ ባሪያዎችህና ገረዶችህም፥ በአገርህም ደጅ ያለው ሌዋዊ አምላክህ እግዚአብሔር በመረጠው ስፍራ በአምላክህ በእግዚአብሔር ፊት ብሉት፤ እጅህንም በምትዘረጋበት ነገር ሁሉ በአምላክህ በእግዚአብሔር ፊት ደስ ይበልህ። 19በምድርህ ላይ በምትኖርበት ዘመን ሁሉ ሌዋዊውን ቸል እንዳትል ተጠንቀቅ። 20አምላክህ እግዚአብሔር እንደ ነገረህ አገርህን ባሰፋ ጊዜ፥ ሰውነትህም ሥጋ መብላት ስለ ወደደች፦ ሥጋ ልብላ ስትል፥ እንደ ሰውነትህ ፈቃድ ሥጋን ብላ። 21አምላክህ እግዚአብሔር በዚያ ስሙን ያኖር ዘንድ የመረጠው ስፍራ ከአንተ ሩቅ ቢሆንም፥ እግዚአብሔር ከሰጠህ ከላምና ከበግ መንጋህ እንዳዘዝሁህ እረድ፥ እንደ ሰውነትህም ፈቃድ ሁሉ በአገርህ ደጅ ውስጥ ብላ። 22ሚዳቍና ዋላ እንደሚበሉ እንዲሁ ብላው፤ ንጹሕ ሰው ንጹሕም ያልሆነ ይብላው። 23ነገር ግን ደሙ ነፍሱ ነውና፥ ነፍሱንም ከሥጋው ጋር መብላት አይገባህምና ደሙን እንዳትበላ ተጠንቀቅ። 24በምድር ላይ እንደ ውኃ አፍስሰው እንጂ አትብላው። 25በእግዚአብሔር ፊት መልካም የሆነውን ነገር ስታደርግ ለአንተ ከአንተም በኋላ ለልጆችህ መልካም እንዲሆንላችሁ፥ አትብላው። 26ነገር ግን የተቀደሰውን ነገርህን ስእለትህንም ይዘህ እግዚአብሔር ወደ መረጠው ስፍራ ሂድ። 27የሚቃጠለውንም መሥዋዕትህን፥ ሥጋውንና ደሙን፥ በአምላክህ በእግዚአብሔር መሠዊያ ላይ አቅርብ፤ የመሥዋዕትህም ደም በአምላክህ በእግዚአብሔር መሠዊያ ላይ ይፍሰስ፥ ሥጋውንም ብላው። 28በአምላክህ በእግዚአብሔር ፊት መልካምና ቅን የሆነውን ነገር ስታደርግ ለአንተ ከአንተም በኋላ ለልጆችህ ለዘላለም መልካም ይሆንላችሁ ዘንድ እኔ የማዝዝህን እነዚህን ቃሎች ሁሉ ሰምተህ ጠብቅ። 29አምላክህ እግዚአብሔር ትወርሳቸው ዘንድ የምትሄድባቸውን አሕዛብን በፊትህ ባጠፋ ጊዜ፥ አንተም በወረስሃቸው ጊዜ፥ 30በምድራቸውም በተቀመጥህ ጊዜ፥ ከፊትህ ከጠፉ በኋላ እነርሱን ለመከተል እንዳትጠመድ፦ እነዚህስ አሕዛብ አማልክቶቻቸውን ያመለኩት እንዴት ነው? እንዲሁ ደግሞ እኔ አደርጋለሁ ብለህ ስለ አማልክቶቻቸው እንዳትጠይቅ ተጠንቀቅ። 31እግዚአብሔር የሚጠላውን ርኵሰት ሁሉ እነርሱ ለአማልክቶቻቸው አድርገዋልና፥ ወንዶችና ሴቶች ልጆቻቸውን ደግሞ ለአማልክቶቻቸው በእሳት ያቃጥሉአቸዋልና አንተ ለአምላክህ ለእግዚአብሔር እንዲሁ አታድርግ። 32እኔ የማዝዝህን ነገር ሁሉ ታደርገው ዘንድ ጠብቅ፤ ምንም በእርሱ ላይ አትጨምር፥ ከእርሱም ምንም አታጕድል።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ