የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ወደ ቆላስይስ ሰዎች 3:12-25

ወደ ቆላስይስ ሰዎች 3:12-25 አማ54

እንግዲህ እንደ እግዚአብሔር ምርጦች ቅዱሳን ሆናችሁ የተወደዳችሁም ሆናችሁ፥ ምሕረትን፥ ርኅራኄን፥ ቸርነትን፥ ትህትናን፥ የዋህነትን፥ ትዕግሥትን ልበሱ፤ እርስ በርሳችሁ ትዕግሥትን አድርጉ፥ ማንም በባልንጀራው ላይ የሚነቅፈው ነገር ካለው፥ ይቅር ተባባሉ፤ ክርስቶስ ይቅር እንዳላችሁ እናንተ ደግሞ እንዲሁ አድርጉ፤ በእነዚህም ሁሉ ላይ የፍጻሜ ማሰሪያ የሆነውን ፍቅርን ልበሱት። በአንድ አካልም የተጠራችሁለት ደግሞ የክርስቶስ ሰላም በልባችሁ ይግዛ፤ የምታመሰግኑም ሁኑ። የእግዚአብሔር ቃል በሙላት ይኑርባችሁ፤ በጥበብ ሁሉ እርስ በርሳችሁ አስተምሩና ገሥጹ፤ በመዝሙርና በዝማሬ በመንፈሳዊም ቅኔ በጸጋው በልባችሁ ለእግዚአብሔር ዘምሩ፤ እግዚአብሔር አብን በእርሱ እያመሰገናችሁ፥ በቃል ቢሆን ወይም በሥራ የምታደርጉትን ሁሉ በጌታ በኢየሱስ ስም አድርጉት። ሚስቶች ሆይ፥ በጌታ እንደሚገባ ለባሎቻችሁ ተገዙ። ባሎች ሆይ፥ ሚስቶቻችሁን ውደዱ መራራም አትሁኑባቸው። ልጆች ሆይ፥ ይህ ለጌታ ደስ የሚያሰኝ ነውና በሁሉ ለወላጆቻችሁ ታዘዙ። አባቶች ሆይ፥ ልባቸው እንዳይዝል ልጆቻችሁን አታበሳጩአቸው። ባሪያዎች ሆይ፥ በቅን ልብ ጌታን እየፈራችሁ እንጂ፥ ለሰው ደስ እንደምታሰኙ ለታይታ የምትገዙ ሳትሆኑ፥ በሥጋ ጌቶቻችሁ ለሆኑ በሁሉ ታዘዙ። ለሰው ሳይሆን ለጌታ እንደምታደርጉ፥ የምታደርጉትን ሁሉ በትጋት አድርጉት፥ ከጌታ የርስትን ብድራት እንድትቀበሉ ታውቃላችሁና፤ የምታገለግሉት ጌታ ክርስቶስ ነውና። የሚበድልም የበደለውን በብድራት ይቀበላል፥ ለሰው ፊትም አድልዎ የለም።