የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ወደ ቆላስይስ ሰዎች 2

2
1ስለ እናንተና በሎዶቅያ ስላሉት ፊቴንም በሥጋ ስላላዩት ሁሉ እንዴት ያለ ትልቅ መጋደል እንዳለኝ ልታውቁ እወዳለሁና፤ 2ልባቸው እንዲጸናና፥ በፍቅርም ተባብረው በማስተዋል ወደሚገኝበት ወደ መረዳት ባለ ጠግነት ሁሉ እንዲደርሱ የእግዚአብሔርንም ምሥጢር እርሱንም ክርስቶስን እንዲያውቁ እጋደላለሁ፤ 3የተሰወረ የጥበብና የእውቀት መዝገብ ሁሉ በእርሱ ነውና። 4ማንም በሚያባብል ቃል እንዳያስታችሁ ይህን እላለሁ። 5በሥጋ ምንም እንኳ ብርቅ፥ በመንፈስ ከእናንተ ጋር ነኝና፥ ሥርዓታችሁንም በክርስቶስም ያለውን የእምነታችሁን ጽናት እያየሁ ደስ ይለኛል።
6እንግዲህ ጌታን ክርስቶስ ኢየሱስን እንደ ተቀበላችሁት በእርሱ ተመላለሱ፤ 7ሥር ሰዳችሁ በእርሱ ታነጹ፥ እንደ ተማራችሁም በሃይማኖት ጽኑ፥ ምስጋናም ይብዛላችሁ። 8እንደ ክርስቶስ ትምህርት ሳይሆን፥ እንደ ሰው ወግና እንደ ዓለማዊ እንደ መጀመሪያ ትምህርት ባለ በፍልስፍና በከንቱም መታለል ማንም እንዳይማርካችሁ ተጠበቁ። 9በእርሱ የመለኮት ሙላት ሁሉ በሰውነት ተገልጦ ይኖራልና፤ 10ለአለቅነትና ለሥልጣንም ሁሉ ራስ በሆነ በእርሱ ሆናችሁ ተሞልታችኋል። 11የሥጋንም ሰውነት በመገፈፍ፥ በክርስቶስ መገረዝ፥ በእጅ ባልተደረገ መገረዝ በእርሱ ሆናችሁ ደግሞ ተገረዛችሁ፤ 12በጥምቀትም ከእርሱ ጋር ተቀብራችሁ፥ በጥምቀት ደግሞ፥ ከሙታን ባስነሣው በእግዚአብሔር አሠራር በማመናችሁ፥ ከእርሱ ጋር ተነሣችሁ። 13እናንተም በበደላችሁና ሥጋችሁን ባለመገረዝ ሙታን በሆናችሁ ጊዜ፥ ከእርሱ ጋር ሕይወትን ሰጣችሁ፤ በደላችሁን ሁሉ ይቅር አላችሁ፤ 14በእኛ ላይ የነበረውን የሚቃወመንንም በትእዛዛት የተጻፈውን የዕዳ ጽሕፈት ደመሰሰው፤ እርሱንም በመስቀል ጠርቆ ከመንገድ አስወግዶታል፤ 15አለቅነትንና ሥልጣናትን ገፎ፥ ድል በመንሣት በእርሱ እያዞራቸው በግልጥ አሳያቸው።
16እንግዲህ በመብል ወይም በመጠጥ ወይም ስለ በዓል ወይም ስለ ወር መባቻ ወይም ስለ ሰንበት ማንም አይፍረድባችሁ፤ 17እነዚህ ሊመጡ ያሉት ነገሮች ጥላ ናቸውና፥ አካሉ ግን የክርስቶስ ነው። 18ትሕትናንና የመላእክትን አምልኮ እየወደደ፥ ባላየውም ያለ ፈቃድ እየገባ፥ በሥጋዊም አእምሮ በከንቱ እየታበየ ማንም አይፍረድባችሁ፤ 19እንደዚህ ያለ ሰው ራስ ወደሚሆነው አይጠጋም፥ ከእርሱም አካል ሁሉ በጅማትና በማሰሪያ ምግብን እየተቀበለ እየተጋጠመም፥ እግዚአብሔር በሚሰጠው ማደግ ያድጋል።
20-21ከዓለማዊ ከመጀመሪያ ትምህርት ርቃችሁ ከክርስቶስ ጋር ከሞታችሁ፥ 22እንደ ሰው ሥርዓትና ትምህርት፦ አትያዝ፥ አትቅመስ፥ አትንካ ለሚሉት ትእዛዛት በዓለም እንደምትኖሩ ስለ ምን ትገዛላችሁ? እነዚህ ሁሉ በመደረግ ሊጠፉ ተወስነዋልና። 23ይህ እንደ ገዛ ፈቃድህ በማምለክና በትሕትና ሥጋንም በመጨቆን ጥበብ ያለው ይመስላል፥ ነገር ግን ሥጋ ያለ ልክ እንዳይጠግብ ለመከልከል ምንም አይጠቅምም።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ