የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ትንቢተ አሞጽ 4

4
1በሰማርያ ተራራ የምትኖሩ፥ ድሆችንም የምትበድሉ፥ ችጋረኞችንም የምታሰጨንቁ፥ ጌቶቻቸውንም፦ አምጡ እንጠጣ የምትሉ እናንተ የባሳን ላሞች ሆይ፥ ይህን ቃል ስሙ። 2ጌታ እግዚአብሔር፦ እናንተን በሰልፍ ዕቃ፥ ቅሬታችሁንም በመቃጥን የሚወስዱበት ቀን፥ እነሆ፥ በላያችሁ ይመጣል ብሎ በቅዱስነቱ ምሎአል። 3እያንዳንዳችሁ በየፊታችሁ በተነደለ ስፍራ ትወጣላችሁ፥ በሬማንም ትጣላላችሁ፥ ይላል እግዚአብሔር።
4የእስራኤል ልጆች ሆይ፥ ይህን ወድዳችኋልና ወደ ቤቴል ኑና ኃጢአትን ሥሩ፥ ወደ ጌልገላ ኑና ኃጢአትን አብዙ፥ በየማለዳውም መሥዋዕታችሁን፥ በየሦስተኛውም ቀን አሥራታችሁን አቅርቡ፥ 5እርሾ ካለበትም የምስጋናውን መሥዋዕት አቅርቡ፥ በፈቃዳችሁም የምታቀርቡትን አውጁና አውሩ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።
6በከተማችሁ ሁሉ ጥርስን ማጥራት፥ በስፍራችሁም ሁሉ እንጀራን ማጣት ሰጠኋችሁ፥ እናንተ ግን ወደ እኔ አልተመለሳችሁም፥ ይላል እግዚአብሔር። 7መከር ሳይደርስ ገና ከሦስት ወር በፊት ዝናብ ከለከልኋችሁ፥ በአንድም ከተማ ላይ አዘነብሁ፥ በሌላውም ከተማ ላይ እንዳይዘንብ አደረግሁ፥ በአንድ ወገን ዘነበ፥ ያልዘነበበትም ወገን ደረቀ። 8የሁለት ወይም የሦስት ከተሞች ሰዎች ወደ አንዲት ከተማ ውኃ ይጠጡ ዘንድ ሄዱ፥ ነገር ግን አልረኩም፥ እናንተ ግን ወደ እኔ አልተመለሳችሁም፥ ይላል እግዚአብሔር። 9በዋግና በአረማሞ መታኋችሁ፥ የአታክልቶቻችሁንም ብዛት ወይኖቻችሁንም በለሶቻችሁንም ወይራዎቻችሁንም ተምች በልቶአል፥ እናንተ ግን ወደ እኔ አልተመለሳችሁም፥ ይላል እግዚአብሔር። 10በግብጽ እንደ ነበረው ቸነፈርን ሰደድሁባችሁ፥ ጐበዛዝቶቻችሁን በሰይፍ ገደልሁ፥ ፈረሶቻችሁንም አስማረክሁ፥ የሰፈራችሁንም ግማት ወደ አፍንጫችሁ አወጣሁ፥ እናንተ ግን ወደ እኔ አልተመለሳችሁም፥ ይላል እግዚአብሔር። 11ሰዶምንና ገሞራን እግዚአብሔር እንደ ገለበጣቸው፥ እንዲሁ ገለበጥኋችሁ፥ እናንተም ከእሳት ውስጥ እንደ ተነጠቀ ትንታግ ሆናችሁ፥ ነገር ግን ወደ እኔ አልተመለሳችሁም፥ ይላል እግዚአብሔር።
12ስለዚህ፥ እስራኤል ሆይ፥ እንደዚህ አደርግብሃለሁ፥ እስራኤልም ሆይ፥ እንደዚህ ስለማደርግብህ አምላክህን ለመገናኘት ተዘጋጅ። 13እነሆ፥ ተራሮችን የሠራ፥ ነፋስንም የፈጠረ፥ የልቡንም አሳብ ለሰው የሚነግር፥ ንጋትን ጨለማ የሚያደርግ፥ በምድርም ከፍታዎች ላይ የሚረግጥ፥ ስሙ የሠራዊት አምላክ እግዚአብሔር ነው።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ