የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ትንቢተ አሞጽ 3

3
1የእስራኤል ልጆች ሆይ፥ እግዚአብሔር በእናንተ፥ ከግብጽ ምድር ባወጣሁት ወገን ሁሉ ላይ የተናገረውን ይህን ቃል ስሙ፥ 2እንዲህም ብሎአል፦ እኔ ከምድር ወገን ሁሉ እናንተን ብቻችሁን አውቄአችኋለሁ፥ ስለዚህ ስለ ኃጢአታችሁ ሁሉ እበቀላችኋለሁ። 3በውኑ ሁለት ሰዎች ሳይስማሙ በአንድነት ይሄዳሉን? 4ወይስ አንበሳ የሚነጥቀው ነገር ሳያገኝ በጫካ ውስጥ ያገሣልን? ወይስ የአንበሳ ደቦል አንዳች ሳይዝ በመደቡ ሆኖ ይጮኻልን? 5ወይስ ወፍ፥ አጥማጅ ከሌለው፥ በምድር ላይ በወጥመድ ይያዛልን? ወይስ ወስፈንጠር አንዳች ሳይዝ ከምድር ይፈነጠራልን? 6ወይስ በከተማ ውስጥ መለከት ሲነፋ ሕዝቡ አይፈራምን? ወይስ ክፉ ነገር በከተማ ላይ የመጣ እንደ ሆነ ያደረገው እግዚአብሔር አይደለምን? 7በእውነት ጌታ እግዚአብሔር ምሥጢሩን ለባሪያዎቹ ለነቢያት ካልነገረ በቀር ምንም አያደርግም። 8አንበሳው አገሣ፥ የማይፈራ ማን ነው? ጌታ እግዚአብሔር ተናገረ፥ ትንቢት የማይናገር ማን ነው?
9በአዛጦን አዳራሾችና በግብጽ ምድር አዳራሾች አውሩና፦ በሰማርያ ተራሮች ላይ ተሰብሰቡ፥ በውስጥዋም የሆነውን ታላቁን ውካታ፥ በመካከልዋም ያለውን ግፍ ተመልከቱ በሉ። 10ግፍንና ቅሚያን በአዳራሾቻቸው የሚያከማቹት ቅን ነገርን ያደርጉ ዘንድ አያውቁም፥ ይላል እግዚአብሔር። 11ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ በምድሪቱ ዙሪያ ጠላት ይመጣል፥ ብርታትሽንም ከአንቺ ያወርዳል፥ አዳራሾችሽንም ይበዘበዛሉ። 12እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እረኛ ከአንበሳ አፍ ሁለት እግርን ወይም የጆሮን ጫፍ እንደሚያድን፥ እንዲሁ በሰማርያ በአልጋ ማዕዘን፥ በደማስቆም በምንጣፍ ላይ የተቀመጡት የእስራኤል ልጆች ይድናሉ።
13ስሙ፥ በያዕቆብም ቤት ላይ መስክሩ፥ ይላል የሠራዊት አምላክ ጌታ እግዚአብሔር። 14እስራኤልን ስለ ኃጢአቱ በምበቀልበት ቀን የቤቴልን መሠዊያዎች ደግሞ እበቀላለሁ፥ የመሠዊያው ቀንዶች ይሰበራሉ፥ ወደ ምድርም ይወድቃሉ። 15የክረምቱንና የበጋውን ቤት እመታለሁ፥ በዝሆንም ጥርስ የተለበጡት ቤቶች ይጠፋሉ፥ ታላላቆችም ቤቶች ይፈርሳሉ፥ ይላል እግዚአብሔር።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ