የሐዋርያት ሥራ 9:32-43

የሐዋርያት ሥራ 9:32-43 አማ54

ጴጥሮስም በየስፍራው ሁሉ ሲዞር በልዳ ወደሚኖሩ ቅዱሳን ደግሞ ወረደ። በዚያም ከስምንት ዓመት ጀምሮ በአልጋ ላይ ተኝቶ የነበረውን ኤንያ የሚሉትን አንድ ሰው አገኘ፤ እርሱም ሽባ ነበረ። ጴጥሮስም፦ “ኤንያ ሆይ፥ ኢየሱስ ክርስቶስ ይፈውስሃል፤ ተነሣ ለራስህም አንጥፍ” አለው። ወዲያውም ተነሣ። በልዳና በሰሮናም የሚኖሩ ሁሉ እርሱን አይተው ወደ ጌታ ዘወር አሉ። በኢዮጴም ጣቢታ የሚሉአት አንዲት ደቀ መዝሙር ነበረች፥ ትርጓሜውም ዶርቃ ማለት ነው፤ እርስዋም መልካም ነገር የሞላባት ምጽዋትም የምታደርግ ነበረች። በዚያም ወራት ታመመችና ሞተች፤ አጥበውም በሰገነት አኖሩአት። ልዳም ለኢዮጴ ቅርብ ናትና ደቀ መዛሙርት ጴጥሮስ በዚያ እንዳለ ሰምተው፥ ወደ እነርሱ ከመምጣት እንዳይዘገይ እየለመኑ ሁለት ሰዎች ወደ እርሱ ላኩ። ጴጥሮስም ተነሥቶ ከእነርሱ ጋር መጣ፤ በደረሰም ጊዜ በሰገነት አወጡት መበለቶችም ሁሉ እያለቀሱ ዶርቃ ከእነርሱ ጋር ሳለች ያደረገቻቸውን ቀሚሶችንና ልብሶችን ሁሉ እያሳዩት በፊቱ ቆሙ። ጴጥሮስም ሁሉን ወደ ውጭ አስወጥቶ ተንበርክኮም ጸለየ፥ ወደ ሬሳውም ዘወር ብሎ፦ “ጣቢታ ሆይ፥ ተነሺ” አላት። እርስዋም ዓይኖችዋን ከፈተች ጴጥሮስንም ባየች ጊዜ ተቀመጠች። እጁንም ለእርስዋ ሰጥቶ አስነሣት፤ ቅዱሳንንና መበለቶችንም ጠራ ሕያውም ሆና በፊታቸው አቆማት። ይህም በኢዮጴ ሁሉ የታወቀ ሆነ፥ ብዙ ሰዎችም በጌታ አመኑ። በኢዮጴም ስምዖን ከሚሉት ከአንድ ቍርበት ፋቂ ጋር አያሌ ቀን ኖረ።