ሁለተኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 3
3
1በሳኦል ቤትና በዳዊት ቤት መካከል ብዙ ዘመን ጦርነት ሆነ፥ የዳዊት ቤት እየበረታ፥ የሳኦል ቤት ግን እየደከመ የሚሄድ ሆነ።
2ለዳዊትም ወንድ ልጆች በኬብሮን ተወለዱለት፥ በኩሩም ከኢይዝራኤላዊቱ ከአኪናሆም የተወለደው አምኖን ነበረ። 3ሁለተኛውም የቀርሜሎሳዊው የናባል ሚስት ከነበረች ከአቢግያ የተወለደው ዶሎሕያ ነበረ። ሦስተኛውም ከጌሹር ንጉሥ ከተልማይ ልጅ ከመዓካ የተወለደው አቤሴሎም ነበረ። 4አራተኛውም የአጊት ልጅ አዶንያስ፥ አምስተኛውም የአቢጣል ልጅ ሰፋጥያስ ነበረ። 5ስድስተኛውም የዳዊት ልጅ ሚስት የዔግላ ልጅ ይትረኃም ነበረ። እነዚህም ለዳዊት በኬብሮን ተወለዱለት።
6በሳኦል ቤትና በዳዊት ቤት መካከል ጦርነት ሆኖ ሳለ አበኔር በሳኦል ቤት ይበረታ ነበር። 7ለሳኦልም የኢዮሄል ልጅ ሪጽፋ የተባለች ቁባት ነበረችው፥ ኢያቡስቴም አበኔርን፦ ወደ አባቴ ቁባት ለምን ገባህ? አለው። 8አበኔርም በኢያቡስቴ ቃል እጅግ ተቆጥቶ እንዲህ አለ፦ እኔ ለአባትህ ለሳኦል ቤት ለወንድሞቹም ለዘመዶቹም ቸርነት አድርጌአለሁ፥ አንተንም ለዳዊት እጅ አሳልፌ አልሰጠሁም፥ አንተም ዛሬ ከዚህች ሴት ጋር ስለ ሠራሁት ኃጢአት ትከስሰኛለህ፥ በውኑ እኔ የውሻ ራስ ነኝን? 9መንግሥትን ከሳኦል ቤት ያወጣ ዘንድ የዳዊትንም ዙፋን በእስራኤልና በይሁዳ ከዳን ጀምሮ እስከ ቤርሳቤህ ድረው ከፍ ያደርግ ዘንድ 10እግዚአብሔር ለዳዊት እንደ ማለለት እንዲሁ ከእርሱ ጋር ባላደርግ እግዚአብሔር በአበኔር ይህን ያድርግበት ይህንም ይጨምርበት። 11ኢያቡስቴም አበኔርን ይፈራው ነበርና አንዳች ይመልስለት ዘንድ አልቻለም።
12አበኔርም ለዳዊት፦ ምድሪቱ ለማን ናት? ከእኔ ጋር ቃል ኪዳን አድርግ፥ እጄም ከአንተ ጋር ትሆናለች፥ እስራኤልንም ሁሉ ወደ አንተ እመልሰዋለሁ ብለው ይነግሩት ዘንድ መልእክተኞች ሰደደለት። 13ዳዊትም፦ ይሁን፥ ከአንተ ጋር ቃል ኪዳን አደርጋለሁ፥ ነገር ግን አንድ ነገር ከአንተ እሻለሁ፥ ፊቴን ለማየት በመጣህ ጊዜ፥ የሳኦልን ልጅ ሜልኮልን ካላመጣህልኝ ፊቴን አታይም አለ። 14ዳዊትም ወደ ሳኦል ልጅ ወደ ኢያቡስቴ፦ በመቶ ፍልስጥኤማውያን ሸለፈት ያጨኋትን ሚስቴን ሜልኮልን ስጠኝ ብሎ መልእክተኞችን ሰደደ። 15ኢያቡስቴም ልኮ ከሌሳ ልጅ ከባልዋ ከፈልጢኤል ወሰዳት። 16ባልዋም እያለቀሰ ከእርስዋ ጋር ሄደ፥ እስከ ብራቂም ድረስ ተከተላት። አበኔርም፦ ሂድ፥ ተመለስ አለው፥ እርሱም ተመለሰ።
17አበኔርም ለእስራኤል ሽማግሌዎች፦ አስቀድሞ ዳዊት በእናንተ ላይ ንጉሥ ይሆን ዘንድ ፈልጋችሁ ነበር። 18እግዚአብሔርም ስለ ዳዊት፦ በባሪያዬ በዳዊት እጅ ሕዝቤን እስራኤልን ከፍልስጥኤማውያን እጅና ከጠላቶቻቸው ሁሉ እጅ አድናለሁ ብሎ ተናግሮአልና እንግዲህ አሁን አድርጉ ብሎ ነገራቸው። 19አበኔርም ደግሞ በብንያም ወገን ጆሮ ተናገረ፥ አበኔርም ደግሞ በእስራኤልና በብንያም ቤት ሁሉ መልካም የነበረውን ለዳዊት ሊነግረው ወደ ኬብሮን ሄደ። 20አበኔርም ከሀያ ሰዎች ጋር ወደ ዳዊት ወደ ኬብሮን መጣ። ዳዊትም ለአበኔርና ከእርሱ ጋር ለነበሩት ሰዎች ግብዣ አደረገላቸው። 21አበኔርም ዳዊትን፦ ተነሥቼ ልሂድ፥ ከአንተ ጋርም ቃል ኪዳን እንዲያደርጉ፥ ነፍስህም እንደ ወደደች ሁሉን እንድትገዛ እስራኤልን ሁሉ ለጌታዬ ለንጉሥ ልሰብስብ አለው። ዳዊትም አበኔርን አሰናበተው፥ በደኅናም ሄደ። 22በዚያን ጊዜም የዳዊት ባሪያዎችና ኢዮአብ ከዘምቻ ታላቅ ምርኮ ይዘው መጡ። አበኔር ግን ዳዊት አሰናብቶት በደኅና ሄዶ ነበር እንጂ በኬብሮን አልነበረም። 23ኢዮአብና ከእርሱም ጋር የነበረ ጭፍራ ሁሉ በመጡ ጊዜ፦ የኔር ልጅ አበኔር ወደ ንጉሥ መጣ፥ አሰናበተውም በደኅናውም ሄደ ብለው ሰዎች ለኢዮአብ ነገሩት። 24ኢዮአብም ወደ ንጉሥ ገብቶ፦ ምን አደረግህ? እነሆ፥ አበኔር መጥቶልህ ነበር፥ በደኅና እንዲሄድ ስለ ምን አሰናበትኸው? 25የኔር ልጅ አበኔር ያታልልህ ዘንድ፥ መውጫህንና መግቢያህንም ያውቅ ዘንድ፥ የምታደርገውንም ነገር ሁሉ ያስተውል ዘንድ እንደ መጣ አታውቅምን? አለው። 26ኢዮአብም ከዳዊት በወጣ ጊዜ መልእክተኞችን ከአበኔር በኋላ ላከ፥ ከሴይርም ጕድጓድም መለሱት። ዳዊት ግን ይህን አላወቀም።
27አበኔርም ወደ ኬብሮን በተመለሰ ጊዜ ኢዮአብ በበር ውስጥ በቆይታ ይናገረው ዘንድ ወደ አጠገቡ ወሰደው፥ በዚያም ለወንድሙ ለአሣሄል ደም ተበቅሎ ሆዱን መታው፥ ሞተም። 28በኋላም ይህ ነገር እንደ ተደረገ በሰማ ጊዜ፦ ከኔር ልጅ ከአበኔር ደም በእግዚአብሔር ዘንድ ለዘላለም እኔ ንጽሕ ነኝ፥ መንግሥቴም ንጽሕ ነው፥ 29በኢዮአብ ራስ ላይና በአባቱ ቤት ሁሉ ላይ ይምጣበት፥ በኢዮአብም ቤት ፈሳሽ ነገር ያለበት ወይም ለምጻም ወይም አንካሳ ወይም በሰይፍ የሚወድቅ ወይም እንጀራ የሌለው ሰው አይታጣ አለ። 30ኢዮአብና ወንድሙ አቢሳም በሰልፍ በገባዖን ወንድማቸውን አሣሄልን ገድሎ ነበርና አበኔርን ገደሉት።
31ዳዊትም ኢዮአብንና ከእርሱ ጋር የነበሩትን ሕዝብ ሁሉ፦ ልብሳችሁን ቅደዱ፥ ማቅም ልበሱ፥ በአበኔርም ፊት አልቅሱ አላቸው። ንጉሡም ዳዊት ከቃሬዛው በኋላ ሄደ። 32አበኔርንም በኬብሮን ቀበሩት፥ ንጉሡም ድምፁን ከፍ አድርጎ በአበኔር መቃብር አጠገብ አለቀሰ፥ ሕዝቡም ሁሉ አለቀሱ። ንጉሡም ለአበኔር፦ 33አበኔር ሰነፍ እንደሚሞት ይሞታልን? 34እጅህ አልታሰረም፥ እግርህም በሰንሰለት አልተያዘም፥ ሰው በዓመፀኞች ፊት እንደሚወድቅ አንተ እንዲሁ ወደቅህ ብሎ የልቅሶ ቅኔ ተቀኘለት። ሕዝቡም ሁሉ ዋይታ አብዝተው አለቀሱ። 35ሕዝቡም ሁሉ ገና ሳይመሽ ዳዊትን እንጀራ ይበላ ዘንድ ሊጋብዙት መጡ፥ ዳዊት ግን፦ ፀሐይ ሳትጠልቅ እንጀራ ወይም ሌላ ነገር ብቀምስ እግዚአብሔር ይህን ያድርግብኝ፥ ይህንም ይጨምርብኝ ብሎ፥ ማለ። 36ሕዝቡም ሁሉ ይህን ተመለከቱ፥ ደስ አሰኛቸውም፥ በሕዝቡም ሁሉ ፊት ንጉሥ ያደረገው ሁሉ ደስ አሰኛቸው።
37በዚያም ቀን ሕዝቡ ሁሉ እስራኤልም ሁሉ የኔር ልጅ የአበኔር ሞት ከንጉሡ ዘንድ እንዳልሆነ አወቁ። 38ንጉሡም ባሪያዎቹን፦ ዛሬ በእስራኤል ዘንድ መኮንንና ታላቅ ሰው እንደ ወደቀ አታውቁምን? 39እኔም ዛሬ ምንም ለመንገሥ የተቀባሁ ብሆን ደካማ ነኝ፥ እነዚህም ሰዎች የጽሩያም ልጆች በርትተውብኛል፥ እግዚአብሔር ክፋት በሠራ ላይ እንደ ክፋቱ ይመልስበት አላቸው።
Currently Selected:
ሁለተኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 3: አማ54
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ