ሁለተኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 11
11
1እንዲህም ሆነ፥ በዓመቱ መለወጫ ነገሥታት ወደ ሰልፍ በሚወጡበት ጊዜ፥ ዳዊት ኢዮአብን ከእርሱም ጋር ባሪያዎቹን እስራኤልንም ሁሉ ሰደደ። የአሞንም ልጆች አገር አጠፉ፥ ረባትንም ከበቡ፥ ዳዊት ግን በኢየሩሳሌም ቀርቶ ነበር።
2እንዲህም ሆነ፥ ወደ ማታ ጊዜ ዳዊት ከምንጣፉ ተነሣ፥ በንጉሥም ቤት በሰገነት ላይ ተመላለሰ፥ በሰገነቱ ሳለ አንዲት ሴት ስትታጠብ አየ፥ ሴቲቱም መልከ መልካም ነበረች። 3ዳዊትም ልኮ ስለ ሴቲቱ ጠየቀ፥ አንድ ሰውም፦ ይህች የኤልያብ ልጅ የኬጢያዊው የኦርዮ ሚስት ቤርሳቤህ አይደለችምን? አለ። 4ዳዊትም መልእክተኞች ልኮ አስመጣት፥ ወደ እርሱም ገባች፥ ከርኩሰትዋም ነጽታ ነበርና ከእርስዋ ጋር ተኛ፥ ወደ ቤትዋም ተመለሰች። 5ሴቲቱም አረገዘች፥ ወደ ዳዊትም፦ አርግዤአለሁ ብላ ላከችበት።
6ዳዊትም ወደ ኢዮአብ፦ ኬጢያዊውን አርዮን ስደድልኝ ብሎ ላከ። ኢዮአብም ኦርዮን ወደ ዳዊት ሰደደው። 7ኦርዮም ወደ እርሱ በመጣ ጊዜ ዳዊት የኢዮአብንና የሕዝቡን ደኅንነት፥ ሰልፉም እንዴት እንደ ሆነ ጠየቀው። 8ዳዊትም ኦርዮን፦ ወደ ቤትህ ሂድ፥ እግርህንም ታጠብ አለው። ኦርዮም ከንጉሡ ቤት ሲወጣ ማለፊያ የንጉሥ መብል ተከትሎት ሄደ። 9ኦርዮ ግን ከጌታው ባሪያዎች ሁሉ ጋር በንጉሥ ቤት ደጅ ተኛ፥ ወደ ቤቱም አልወረደም። 10ኦርዮ ወደ ቤቱ አልሄደም ብለው ለዳዊት ነገሩት፥ ዳዊትም ኦርዮን፦ አንተ ከመንገድ የመጣህ አይደለምን? ስለ ምን ወደ ቤትህ አልወረድህም? አለው። 11ኦርዮም ዳዊትን፦ ታቦቱና እስራኤል ይሁዳም በጎጆ ተቀምጠዋል፥ ጌታዬ ኢዮአብና የጌታዬም ባሪያዎች በሰፊ ሜዳ ሰፍረዋል እኔ ልበላና ልጠጣ ወይስ ከሚስቴ ጋር ልተኛ ወደ ቤቴ እሄዳላሁን? በሕይወትህና በሕያው ነፍስህ እምላለሁ! ይህን ነገር አላደርገውም አለው። 12ዳዊትም ኦርዮን፦ ዛሬ ደግሞ በዚህ ተቀመጥ፥ ነገም አሰናብትሃለሁ አለው። ኦርዮም በዚያ ቀንና በነጋው በኢየሩሳሌም ተቀመጠ። 13ዳዊትም ጠራው፦ በፊቱም በላና ጠጣ፥ አሰከረውም፥ ነገር ግን በመሸ ጊዜ ወጥቶ ከጌታው ባሪያዎች ጋር በምንጣፉ ላይ ተኛ፥ ወደ ቤቱም አልወረደም።
14በነጋም ጊዜ ዳዊት ለኢዮአብ ደብዳቤ ጻፈ፥ በኦርዮም እጅ ላከው። 15በደብዳቤውም፦ ኦርዮን ጽኑ ሰልፍ ባለበት በፊተኛው ስፍራ አቁሙት፥ ተመትቶም ይሞት ዘንድ ከኋላው ሽሹ ብሎ ጻፈ። 16ኢዮአብም ከተማይቱን በከበበ ጊዜ ጀግኖች እንዳሉበት በሚያውቀው ስፍራ ኦርዮን አቆመው። 17የከተማይቱም ሰዎች ወጥተው ከኢዮአብ ጋር ተዋጉ፥ ከዳዊትም ባሪያዎች ከሕዝቡ አንዳንዱ ወደቁ፥ ኬጢያዊው ኦርዮም ደግሞ ሞተ። 18ኢዮአብም ልኮ በሰልፍ የሆነውን ሁሉ ለዳዊት ነገረው። 19ለመልእክተኛውም እንዲህ ብሎ አዘዘው፦ የሰልፉን ነገር ሁሉ ለንጉሡ ነግረህ በፈጸምህ ጊዜ፥ 20ስትዋጉ ወደ ከተማይቱ ለምን ቀረባችሁ? ከቅጥሩ በላይ ፍላጻ እንዲወረወር አታውቁምን? 21የሩቤሼትን ልጅ አቤሜሌክን ማን ገደለው? ከቅጥር ላይ የወፍጮ መጅ ጥላ በቴቤስ ላይ የገደለችው አንዲት ሴት አይደለችምን? ስለ ምን ወደ ቅጥሩ እንደዚህ ቀርባችሁ? ብሎ ንጉሡ ሲቆጣ ብታይ፥ አንተ፦ ባሪያህ ኬጢያዊው ኦርዮ ደግሞ ሞተ በለው።
22መልእክተኛውም ተነሥቶ ሄደ፥ ኢዮአብም ያዘዘውን ሁሉ ለዳዊት ነገረው። 23መልእክተኛውም ዳዊትን፦ ሰዎቹ በረቱብን፥ ወደ ሜዳም ወጡብን፥ እኛም ወደቅንባቸው፥ እስከ ከተማይቱም በር ድረስ ተከተልናቸው። 24ፍላጻ የሚወረውሩም በቅጥሩ ላይ ሆነው በባሪያዎችህ ላይ ወረወሩ፥ ከንጉሡም ባሪያዎች አንዳንድ ሞቱ፥ ባሪያህም ኬጢያዊው ኦርዮ ደግሞ ሞተ አለው። 25ዳዊትም መልእክተኛውን፦ ሰይፍ አንድ ጊዜ ይህን አንድ ጊዜም ያን ያጠፋልና ይህ ነገር በዓይንህ አይክፋ፥ ከተማይቱን የሚወጉትን አበርታ፥ አፍርሳትም ብለህ ለኢዮአብ ንገረው፥ አንተም አጽናው አለው። 26የኦርዮም ሚስት ባልዋ ኦርዮ እንደሞተ በሰማች ጊዜ ለባልዋ አለቀሰች። 27የልቅሶዋም ወራት ሲፈጸም ዳዊት ልኮ ወደ ቤቱ አስመጣት፥ ሚስትም ሆነችው፥ ወንድ ልጅም ወለደችለት ነገር ግን ዳዊት ያደረገው ነገር ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ሆነ።
Currently Selected:
ሁለተኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 11: አማ54
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ