የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ሁለተኛ መጽሐፈ ነገሥት 25

25
የኢየሩሳሌም ቤጠላት እጅ መውደቅ
(2ዜ.መ. 3፥13-17ኤር. 52፥3-11)
1ሴዴቅያስም በነገሠ በዘጠነኛው ዓመት በዐሥረኛው ወር ከወሩም በዐሥረኛው ቀን የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆርና ሠራዊቱ ሁሉ ወደ ኢየሩሳሌም መጥተው ከበቡአት፤ በዙሪያዋም ዕርድ ሠሩባት። 2ከተማይቱም እስከ ንጉሡ እስከ ሴዴቅያስ እስከ ዐሥራ አንደኛው ዓመት ድረስ ተከብባ ነበር። 3በአራተኛውም ወር በዘጠነኛው ቀን በከተማይቱ ራብ ጸንቶ ነበርና ለአገሩ ሰዎች እንጀራ ታጣ። 4ከተማይቱም ተሰበረች፤ ሰልፈኞችም ሁሉ በሁለት ቅጥር መካከል ባለው በር ወደ ንጉሡ አትክልት በሚወስደው መንገድ በሌሊት ሸሹ፤ ከለዳውያንም በከተማይቱ ዙሪያ ነበሩ፤ በዓረባም መንገድ ሄዱ። 5የከለዳውያንም ሠራዊት ንጉሡን ተከታተሉ፤ በኢያሪኮም ሜዳ ያዙት፤ ሠራዊቱም ሁሉ ከእርሱ ተለይተው ተበትነው ነበር። 6ንጉሡንም ይዘው የባቢሎን ንጉሥ ወዳለበት ወደ ሪብላ አመጡት፤ ፍርድም ፈረዱበት። 7የሴዴቅያስንም ልጆች በፊቱ ገደሉአቸው፤ የሴዴቅያስንም ዐይኖች አወጡ፤ በሰንሰለትም አሰሩት፤ ወደ ባቢሎንም ወሰዱት።
የኢየሩሳሌም ቤተመቅደስ እንደ ፈረሰ
(ኤር. 52፥12-33)
8በባቢሎንም ንጉሥ በናቡከደነፆር በዐሥራ ዘጠነኛው ዓመት በአምስተኛው ወር ከወሩም በሰባተኛው ቀን የባቢሎን ንጉሥ ባሪያ የዘበኞቹ አለቃ ናቡዘረዳን ወደ ኢየሩሳሌም መጣ። 9የእግዚአብሔርንም ቤትና የንጉሡን ቤት አቃጠለ፤ የኢየሩሳሌምንም ቤቶች ሁሉ፥ ታላላቆቹን ቤቶች ሁሉ፥ በእሳት አቃጠለ። 10ከዘበኞቹም አለቃ ጋር የነበረው የከለዳውያን ሠራዊት ሁሉ የኢየሩሳሌምን ቅጥር ዙሪያዋን አፈረሱ። 11የዘበኞቹም አለቃ ናቡዘረዳን በከተማይቱ ውስጥ የቀረውን ሕዝብ፥ ሸሽተውም ወደ ባቢሎን ንጉሥ የተጠጉትን፥ የቀሩትንም ሕዝብ አፈለሰ። 12የዘበኞቹም አለቃ ከአገሩ ድሆች ወይን ተካዮችና አራሾች እንዲሆኑ አስቀረ።
13ከለዳውያንም በእግዚአብሔር ቤት ውስጥ የነበሩትን የናስ ዐምዶች፥ በእግዚአብሔርም ቤት የነበሩትን መቀመጫዎችና የናስ ኵሬ ሰባበሩ፤ ናሱንም ወደ ባቢሎን ወሰዱ። 14ምንቸቶቹንና መጫሪያዎቹንም መኰስተሪያዎቹንና ጭልፋዎቹንም የሚያገለግሉበትንም የናስ ዕቃ ሁሉ ወሰዱ። 15የዘበኞቹም አለቃ ማንደጃዎቹንና መቀመጫዎቹን፥ የወርቁን ዕቃ ሁሉ በወርቅ፥ የብሩንም በብር አድርጎ ወሰደ። 16ሰሎሞንም ለእግዚአብሄር ቤት የሠራቸውን ሁለቱን ዐምዶች አንዱንም ኵሬ መቀመጫዎቹንም ወሰደ፤ ለእነዚህ ዕቃዎች ሁሉ ናስ ሚዛን አልነበረውም። 17የአንዱም ዐምድ ቁመት ዐሥራ ስምንት ክንድ ነበረ፤ የናስም ጕልላት ነበረበት፤ የጕልላቱም ርዝመት ሦስት ክንድ ነበረ፤ በጕልላቱም ላይ በዙሪያው የናስ መርበብና ሮማኖች ነበሩ፤ እንዲሁም ደግሞ በሁለተኛው ዐምድ ላይ መርበብ ነበረበት።
የይሁዳ ሕዝብ ተማርኮ ወደባቢሎን እንደ ተወሰደ
(ኤር. 52፥24-27)
18የዘበኞቹም አለቃ ታላቁን ካህን ሠራያን፥ ሁለተኛውንም ካህን ሶፎንያስን፥ ሦስቱንም በረኞች ወሰደ። 19ከከተማይቱም በሰልፈኞች ላይ ተሹመው ከነበሩት አንዱን ጃንደረባ፥ በከተማይቱም የተገኙትን በንጉሡ ፊት የሚቆሙትን አምስቱን ሰዎች፥ የአገሩንም ሕዝብ የሚያሰልፍ የሠራዊቱን አለቃ ጸሐፊ፥ በከተማይቱም ከተገኙት ከአገሩ ሕዝብ ስድሳ ሰዎች ወሰደ። 20የዘበኞቹም አለቃ ናቡዘረዳን ወስዶ የባቢሎን ንጉሥ ወዳለበት ወደ ሪብላ አመጣቸው። 21የባቢሎንም ንጉሥ መታቸው፤ በሐማትም ምድር ባለችው በሪብላ ገደላቸው። እንዲሁ ይሁዳ ከአገሩ ተማረከ።
ጎዶልያስ የይሁዳ ገዢ እንደ ሆነ
(ኤር. 40፥7-941፥1-3)
22የባቢሎንም ንጉሥ ናቡከደነፆር በይሁዳ ምድር በቀረው ሕዝብ ላይ የሳፋንን ልጅ የአኪቃምን ልጅ ጎዶልያስን አለቃ አደረገው። 23የጭፍሮቹም አለቆች ሁሉ፥ የናታንያ ልጅ እስማኤል፥ የቃሬያም ልጅ ዮሐናን፥ የነጦፋዊውም የተንሑሜት ልጅ ሠራያ፥ የማዕካታዊውም ልጅ ያእዛንያ፥ ሰዎቻቸውም የባቢሎን ንጉሥ ጎዶልያስን እንደ ሾመ በሰሙ ጊዜ ወደ ጎዶልያስ ወደ ምጽጳ መጡ። 24ጎዶልያስም “ከከለዳውያን ሎሌዎች የተነሣ አትፍሩ፤ በአገሩ ተቀመጡ፤ ለባቢሎንም ንጉሥ ተገዙ፤ መልካምም ይሆንላችኋል፤” ብሎ ለእነርሱና ለሰዎቻቸው ማለላቸው። 25በሰባተኛው ወር ግን የመንግሥት ዘር የነበረ የኤሊሳማ ልጅ የናታንያ ልጅ እስማኤል ከእርሱም ጋር ዐሥር ሰዎች መጥተው ጎዶልያስንና ከእርሱ ጋር በምጽጳ የነበሩትን አይሁድንና ከለዳውያንን እስኪሞቱ ድረስ መቱአቸው። 26ከለዳውያንንም ፈርተው ነበርና ከታናሹ ጀምሮ እስከ ታላቁ ድረስ ሕዝቡ ሁሉ የጭፍሮቹም አለቆች ተነሥተው ወደ ግብጽ መጡ።
ዮአኪን ከእስራት እንደ ተፈታ
(ኤር. 52፥31-34)
27እንዲህም ሆነ፤ የይሁዳ ንጉሥ ዮአኪን በተማከረከ በሠላሳ ሰባተኛው ዓመት በዐሥራ ሁለተኛው ወር ከወሩም በሃያ ሰባተኛው ቀን የባቢሎን ንጉሥ ዮርማሮዴቅ በነገሠ በአንደኛው ዓመት የይሁዳ ንጉሥ ዮአኪንን ከወህኒ አወጣው፤ 28በፍቅርም ተናገረው፤ ዙፋኑንም ከእርሱ ጋር በባቢሎን ከነበሩት ነገሥታት ዙፋን በላይ አደረገለት። 29በወህኒም ውስጥ ለብሶት የነበረውን ልብስ ለወጠለት፤ ዮአኪንም በሕይወቱ ዘመን ሁሉ በፊቱ ሁልጊዜ እንጀራ ይበላ ነበር። 30ንጉሡም በሕይወቱ ዘመን ሁሉ የዘወትር ቀለብ ዕለት ዕለት ይሰጠው ነበር።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ