የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ሁለተኛ መጽሐፈ ነገሥት 24

24
1በእርሱም ዘመን የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነዖር ወጣ፤ ኢዮአቄምም ሦስት ዓመት ተገዛለት፤ ከዚያም በኋላ ዘወር አለና ዐመፀበት። 2እግዚአብሔርም የከለዳውያንንና የሶርያውያንን የሞዓባውያንንም የአሞንንም ልጆች አደጋ ጣዮች ሰደደበት፤ በባሪያዎቹ በነቢያት እንደ ተናገረው እንደ እግዚአብሔር ቃል ያጠፉት ዘንድ በይሁዳ ላይ ሰደዳቸው። 3-4ምናሴ ስላደረገው ኀጢአት ሁሉ ስላፈሰሰውም ንጹሕ ደም፥ ኢየሩሳሌምንም በንጹሕ ደም ስለሞላ ከፊቱ ያስወግዳቸው ዘንድ ይህ ነገር በእግዚአብሔር ትእዛዝ በይሁዳ ላይ ሆነ፤ እግዚአብሔርም ይራራ ዘንድ አልወደደም።
5የቀረውም የኢዮአቄም ነገር፥ የሠራውም ሥራ ሁሉ፥ በይሁዳ ነገሥታት ታሪክ መጽሐፍ የተጻፈ አይደለምን? 6ኢዮአቄምም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፤ ልጁም ዮአኪን፤ በእርሱ ፋንታ ነገሠ። 7የባቢሎንም ንጉሥ ለግብጽ ንጉሥ የነበረውን ሁሉ ከግብጽ ወንዝ ጀምሮ እስከ ኤፍራጥስ ወንዝ ድረስ ወስዶ ነበርና የግብጽ ንጉሥ ከዚያ ወዲያ ከአገሩ አልወጣም።
ዮአኪን በይሁዳ እንደ ነገሠና እንደ ተማረከ
(2ዜ.መ. 36፥9-10)
8ዮአኪን መንገሥ በጀመረ ጊዜ የዐሥራ ስምንት ዓመት ጐልማሳ ነበረ፤ በኢየሩሳሌምም ሦስት ወር ነገሠ፤ እናቱም ኔስታ ትባል ነበር፤ እርስዋም የኢየሩሳሌም ሰው የኤልናታን ልጅ ነበረች። 9አባቱም እንዳደረገ ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት ክፉ አደረገ።
10በዚያም ወራት የባቢሎን ንጉሥ የናቡከደነዖር ባሪያዎች ወደ ኢየሩሳሌም ወጡ፤ ከተማይቱም ተከበበች። 11ባሪያዎቹም በከበቡአት ጊዜ የባቢሎን ንጉሥ ናብከደነዖር ወደ ከተማይቱ ወጣ። 12የይሁዳም ንጉሥ ዮአኪንና እናቱ፥ ባርያዎቹም፥ አለቆቹም፥ ጃንደረቦቹም ወደ ባቢሎን ንጉሥ ወጡ፤ የባቢሎንም ንጉሥ በነገሠ በስምንተኛው ዓመት ያዘው። 13የእግዚአብሔርንም ቤት ቤተ መዛግብት ሁሉ የንጉሡንም ቤተ መዛግብት ከዚያ አወጣ፤ እግዚአብሔርም እንደ ተናገረው የእስራኤል ንጉሥ ሰሎሞን በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ የሠራውን የወርቁን ዕቃ ሁሉ ሰባበረ። 14ኢየሩሳሌምንም ሁሉ፥ አለቆቹንም ሁሉ፥ ጽኑዓን ኀያላኑንም ሁሉ፥ ጠራቢዎቹንም ሁሉ፥ ብረት ሠራተኞቹን ሁሉ ዐሥር ሺህ ምርኮኞች አፈለሰ፤ ከድሆች ከአገሩ ሕዝብ በቀር ማንም አልቀረም። 15ዮአኪንንም ወደ ባቢሎን አፈለሰ፤ የንጉሡንም እናት፥ የንጉሡንም ሚስቶች፥ ጃንደረቦቹንም፥ የአገሩንም ታላላቆች ከኢየሩሳሌም ወደ ባቢሎን ማረከ። 16የባቢሎንም ንጉሥ ብርቱዎቹንና ሰልፍ የሚችሉትን ሁሉ፥ ኀያላኑን ሁሉ ሰባት ሺህ ያህል፥ ጠራቢዎችና ብረት ሠራተኞችም አንድ ሺህ፥ ወደ ባቢሎን ማረከ። 17የባቢሎንም ንጉሥ የዮአኪንን አጎት ማታንያን በእርሱ ፋንታ አነገሠ፤ ስሙንም ሴዴቅያስ ብሎ ለወጠው።
ሴዴቅያስ በይሁዳ እንደ ነገሠ
(2ዜ.መ. 36፥11-12ኤር. 52፥1-3)
18ሴዴቅያስ መንገሥ በጀመረ ጊዜ የሃያ አንድ ዓመት ጐልማሳ ነበረ፤ በኢየሩሳሌምም ዐሥራ አንድ ዓመት ነገሠ፤ እናቱም አሚጣል የተባለች የልብና ሰው የኤርምያስ ልጅ ነበረች። 19ኢዮአቄምም እንዳደረገ ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት ክፉ አደረገ። 20ከፊቱ አውጥቶ እስኪጥላቸው ድረስ ይህ ነገር በእግዚአብሔር ቍጣ በኢየሩሳሌምና በይሁዳ ላይ ሆኖአልና፤ ሴዴቅያስም በባቢሎን ንጉሥ ላይ ዐመፀ።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ