ሁለተኛ መጽሐፈ ነገሥት 20
20
የንጉሥ ሕዝቅያስ ታሞ መዳን
(2ዜ.መ. 32፥24-26፤ ኢሳ. 38፥1-8፤21-22)
1በዚያም ወራት ሕዝቅያስ እስከ ሞት ድረስ ታመመ። ነቢዩም የአሞጽ ልጅ ኢሳይያስ ወደ እርሱ መጥቶ “እግዚአብሔር እንዲህ ይላል ‘ትሞታለህ እንጂ በሕይወት አትኖርምና ቤትህን አስተካክል፤’” አለው። 2ፊቱንም ወደ ግድግዳው መልሶ እንዲህ ሲል ወደ እግዚአብሔር ጸለየ 3“አቤቱ፥ በፊትህ በእውነትና በፍጹም ልብ እንደ ሄድሁ፥ ደስ የሚያሰኝህንም እንዳደረግሁ ታስብ ዘንድ እለምንሃለሁ።” ሕዝቅያስም እጅግ አድርጎ አለቀሰ። 4ኢሳይያስም ወደ መካከለኛው ከተማ አደባባይ ሳይደርስ የእግዚአብሔር ቃል እንዲህ ሲል መጣለት 5“ተመልሰህ የሕዝቤን አለቃ ሕዝቅያስን እንዲህ በለው ‘የአባትህ የዳዊት አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፥ ጸሎትህን ሰምቻለሁ፤ እንባህንም አይቻለሁ፤ እነሆ፥ እፈውስሃለሁ፤ በሦስተኛውም ቀን ወደ እግዚአብሔር ቤት ትወጣለህ። 6በዕድሜህም ላይ ዐሥራ አምስት ዓመት እጨምራለሁ፤ አንተንና ይህችን ከተማ ከአሦር ንጉሥ እጅ እታደጋለሁ፤ ስለ እኔም ስለ ባሪያዬም ስለ ዳዊት ይህችን ከተማ እጋርዳታለሁ።’” 7ኢሳይስም “የበለስ ጥፍጥፍ አምጡልኝ፤” አለ፤ አምጥተውም በእባጩ ላይ አደርጉለት፤ እርሱም ተፈወሰ።
8ሕዝቅያስም ኢሳይያስን “እግዚአብሔር እንዲፈውሰኝ፥ እኔስ በሦስተኛው ቀን ወደ እግዚአብሔር ቤት እንድወጣ ምልክቱ ምንድን ነው?” አለው። 9ኢሳይያስም “እግዚአብሔር የተናገረውን ነገር እንዲፈጽመው ከእግዚአብሔር ዘንድ ምልክቱ ይህ ይሆንልሃል፤ ጥላው ዐሥር ደረጃ ወደ ፊት ይሄድ ዘንድ ወይም ዐሥር ደረጃ ወደ ኋላ ይመለስ ዘንድ ትወድዳለህን?” አለ። 10ሕዝቅያስም “ጥላው ዐሥር ደረጃ ቢጨምር ቀላል ነገር ነው፤ እንዲህ አይሁን፤ ነገር ግን ጥላው ዐሥር ደረጃ ወደ ኋላ ይመለስ፤” አለው። 11ነቢዩ ኢሳይያስም ወደ እግዚአብሔር ጮኸ፤ ጥላውንም በአካዝ የጥላ ስፍራ ሰዓት ላይ በወረደበት መንገድ ዐሥር ደረጃ ወደ ኋላ መለሰው።
ከባቢሎን የመጡ መልእክተኞች
(ኢሳ. 39፥1-8)
12በዚያም ወራት የባቢሎን ንጉሥ የባልዳን ልጅ መሮዳክ ባልዳን ሕዝቅያስ እንደ ታመመ ሰምቶ ነበርና ደብዳቤና እጅ መንሻ ወደ ሕዝቅያስ ላከ። 13ሕዝቅያስም ደስ አለው፤ ግምጃ ቤቱንም ሁሉ፥ ብሩንና ወርቁንም፥ ቅመሙንና የከበረውንም ዘይት፥ መሣሪያም ያለበትን ቤት በቤተ መዛግብቱም የተገኘውን ሁሉ አሳያቸው፤ በቤቱና በግዛቱ ሁሉ ካለው ሕዝቅያስ ያላሳያቸው የለም። 14ነቢዩ ኢሳይያስም ወደ ንጉሡ ወደ ሕዝቅያስ መጥቶ “እነዚህ ሰዎች ምን አሉ? ከወዴትስ መጡልህ?” አለው። ሕዝቅያስም “ከሩቅ አገር ከባቢሎን መጡ፤” አለው። 15እርሱም “በቤትህ ያዩት ምንድር ነው?” አለው፤ ሕዝቅያስም “በቤቴ ያለውን ሁሉ አይተዋል፤ በቤተ መዛግብቴ ካለው ያላሳየኋቸው የለም፤” አለው።
16ኢሳይያስም ሕዝቅያስን “የእግዚአብሔርን ቃል ስማ። 17‘እነሆ፥ በቤትህ ያለው ሁሉ፥ አባቶችህም እስከ ዛሬ ድረስ ያከማቹት ሁሉ ወደ ባቢሎን የሚፈልስበት ወራት ይመጣል፤ ምንም አይቀርም፤’ ይላል እግዚአብሔር። 18ከአንተም ከሚወጡት ከምትወልዳቸው ልጆችህ ማርከው ይወስዳሉ፤ በባቢሎንም ንጉሥ ቤት ውስጥ ጃንደረቦች ይሆናሉ፤” አለው። 19ሕዝቅያስም ኢሳይያስን “የተናገርኸው የእግዚአብሔር ቃል መልካም ነው፤” አለው። ደግሞም “በዘመኔ ሰላምና እውነት የሆነ እንደ ሆነ መልካም አይደለምን?” አለ።
የንጉሥ ሕዝቅያስ ዘመነ መንግሥት ፍጻሜ
(2ዜ.መ. 32፥32-33)
20የቀረውም የሕዝቅያስ ነገር፥ ጭከናውም ሁሉ፥ ኵሬውንና መስኖውንም እንደ ሠራ፥ ውሃውንም ወደ ከተማይቱ እንዳመጣ፥ በይሁዳ ነገሥታት ታሪክ መጽሐፍ የተጻፈ አይደለምን? 21ሕዝቅያስም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፤ ልጁም ምናሴ በእርሱ ፋንታ ነገሠ።
Currently Selected:
ሁለተኛ መጽሐፈ ነገሥት 20: አማ54
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ
![None](/_next/image?url=https%3A%2F%2Fimageproxy.youversionapi.com%2F58%2Fhttps%3A%2F%2Fweb-assets.youversion.com%2Fapp-icons%2Fam.png&w=128&q=75)
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ