ሁለተኛ መጽሐፈ ነገሥት 19

19
ንጉሥ ሕዝቅያስ የነቢዩ የኢሳይያስን ምክር እንደ ጠየቀ
(ኢሳ. 37፥1-7)
1ንጉሡም ሕዝቅያስ ይህን በሰማ ጊዜ ልብሱን ቀደደ፤ ማቅም ለበሰ፤ ወደ እግዚአብሔርም ቤት ገባ። 2የቤቱንም አዛዥ ኤልያቄምን ጸሐፊውንም ሳምናስን የካህናቱንም ሽማግሌዎች ማቅ ለብሰው ወደ ነቢዩ ወደ አሞጽ ልጅ ወደ ኢሳይያስ ይሄዱ ዘንድ ላካቸው። 3እነርሱም “ሕዝቅያስ እንዲህ ይላል ‘ይህ ቀን የመከራና የተግሣጽ የዘለፋም ቀን ነው፤ ልጆች የሚወለዱበት ጊዜ ደርሶአል፤ ለመውለድም ኀይል የለም። 4ምናልባት በሕያው አምላክ ላይ ይገዳደር ዘንድ ጌታው የአሦር ንጉሥ የላከውን የራፋስቂስን ቃል ሁሉ አምላክህ እግዚአብሔር ይሰማ እንደ ሆነ፥ አምላክህ እግዚአብሔርም ስለ ሰማው ቃል ይገሥጸው እንደ ሆነ፥ ስለዚህ ለቀረው ቅሬታ ጸልይ’” አሉት። 5እንዲሁ የንጉሡ የሕዝቅያስ ባሪያዎች ወደ ኢሳያስ መጡ። 6ኢሳያስም “ለጌታችሁ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል ‘የአሦር ንጉሥ ባሪያዎች ስለ ሰደቡኝ፥ ስለ ሰማኸው ቃል አትፍራ። 7እነሆ፥ በላዩ መንፈስን እሰድዳለሁ፤ ወሬንም ይሰማል፤ ወደ ምድሩም ይመለሳል፤ በምድሩም በሰይፍ እንዲወድቅ አደርገዋለሁ፤’ በሉት፤” አላቸው።
ሰናክሬም የላከው ማስፈራሪያ
(ኢሳ. 37፥8-20)
8የአሦርም ንጉሥ ከለኪሶ እንደ ራቀ ሰምቶ ነበርና ራፋስቂስ ተመልሶ በልብና ሲዋጋ አገኘው። 9እርሱም “የኢትዮጵያ ንጉሥ ቲርሐቅ ሊወጋህ መጥቶአል፤” የሚል ወሬ በሰማ ጊዜ ደግሞ ወደ ሕዝቅያስ መልእክተኞችን እንዲህ ሲል ላከ፤ 10“ለይሁዳ ንጉሥ ለሕዝቅያስ እንዲህ ብላችሁ ንገሩት ‘ኢየሩሳሌም በአሦር ንጉሥ እጅ አትሰጥም፤’ ብሎ የምትታመንበት አምላክህ አያታልልህ። 11እነሆ፥ የአሦር ነገሥታት በምድር ሁሉ ላይ ያደረጉትን፥ እንዴትስ እንዳጠፋአቸው ሰምተሃል፤ አንተስ ትድናለህን? 12አባቶቼ ያጠፉአቸውን፥ ጎዛንን፥ ካራንን፥ ራፊስን፥ በተላሳር የነበሩትንም የዔድንን ልጆች፥ የአሕዛብ አማልክት አዳኑአቸውን? 13የሐማት ንጉሥ፥ የአርፋድ ንጉሥ፥ የሴፈርዋይም ከተማ ንጉሥ፥ የሄናና የዒዋ ንጉሥ ወዴት አሉ?”
የሕዝቅያስ ጸሎት
(ኢሳ. 37፥14-20)
14ሕዝቅያስም ደብዳቤውን ከመልእክተኞች እጅ ተቀብሎ አነበበው፤ ሕዝቅያስም ወደ እግዚአብሔር ቤት ወጥቶ በእግዚአብሔር ፊት ዘረጋው። 15ሕዝቅያስም ወደ እግዚአብሔር እንዲህ ብሎ ጸለየ “በኪሩቤል ላይ የምትቀመጥ የእስራኤል አምላክ አቤቱ፥ አንተ ብቻህን የምድር ነገሥታት ሁሉ አምላክ ነህ፤ ሰማይንና ምድርን ፈጥረሃል። 16አቤቱ፥ ጆሮህን አዘንብልና ስማ፤ አቤቱ፥ ዐይንህን ክፈትና እይ፤ በሕያው አምላክ ላይ ይገዳደር ዘንድ የላከውን የሰናክሬምን ቃል ስማ። 17አቤቱ፥ በእውነት የአሦር ነገሥታት አሕዛብንና ምድራቸውን አፍርሰዋል፤ 18አማልክቶቻቸውንም በእሳት ላይ ጥለዋል፤ የእንጨትና የድንጋይ የሰው እጅ ሥራ ነበሩ እንጂ አማልክት አልነበሩምና፤ ስለዚህ አጥፍተዋቸዋል። 19እንግዲህም አምላካችን አቤቱ፥ የምድር መንግሥታት ሁሉ አንተ ብቻ እግዚአብሔር አምላክ እንደ ሆንህ ያውቁ ዘንድ ከእጁ እንድታድነን እለምንሃለሁ።”
ኢሳይያስ ወደ ንጉሡ የላከው መልእክት
(ኢሳ. 37፥21-38)
20የአሞጽም ልጅ ኢሳይያስ እንዲህ ብሎ ወደ ሕዝቅያስ ላከ “የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል ‘ስለ አሦር ንጉሥ ስለ ሰናክሬም ወደ እኔ የለመንኽውን ሰምቻለሁ። 21እግዚአብሔር በእርሱ ላይ የተናገረው ቃል ይህ ነው “ድንግሊቱ የጽዮን ልጅ ቀላል አድርጋሃለች፤ በንቀትም ስቃብሃለች፤ የኢየሩሳሌም ልጅ በላይህ ራስዋን ነቅንቃብሃለች።” 22የተገዳደርኸው፥ የሰደብኸውስ ማንን ነው? ቃልህንስ ከፍ ከፍ ያደረግኸው ዐይንህንም ወደ ላይ ያነሣኸው በማን ላይ ነው? በእስራኤል ቅዱስ ላይ ነው! 23አንተስ “በሠረገላዬ ብዛት ወደ ተራሮች ከፍታ፥ ወደ ሊባኖስ ጥግ ላይ ወጥቻለሁ፤ ረጃጅሞቹንም ዝግባዎች የተመረጡትንም ጥዶች እቈርጣለሁ፤ ወደ አገሩም ዳርቻና ወደ ቀርሜሎስ ዱር እገባለሁ። 24ቈፈርሁም፤ እንግዳውንም ውሃ ጠጣሁ፤ የተገደበውንም ውሃ ሁሉ በእግሬ ጫማ አደርቃለሁ፤” ብለህ በመልእክተኞችህ እጅ በእግዚአብሔር ላይ ተገዳደርህ።
25“‘እኔ ጥንቱን እንደ ሠራሁት፥ ቀድሞውንም እንዳደረግሁት አልሰማህምን? አሁንም የተመሸጉትን ከተሞች የፍርስራሽ ክምር እስኪሆኑ ድረስ እንድታፈርስ አደረግሁህ። 26ስለዚህም የሚኖሩባቸው ሰዎች እጃቸው ዝሎአል፤ ደንግጠውም ታውከዋል፤ እንደ ምድረ በዳ ሣር፥ እንደ ለምለምም ቡቃያ፥ በሰገነትም ላይ እንዳለ ሣር፥ ሳይሸት ዋግ እንደ መታውም እህል ሆነዋል። 27እኔ ግን መቀመጫህንና መውጫህንም መግቢያህንም፥ በእኔም ላይ የተቈጠኸውን ቍጣ አውቄአለሁ። 28ቍጣህና ትዕቢትህ ወደ ጆሮዬ ደርሶአልና ስለዚህ ስናጋዬን በአፍንጫህ፥ ልጓሜንም በከንፈርህ አደርጋለሁ፤ በመጣህበትም መንገድ እመልስሃለሁ።
29“‘ይህም ምልክት ይሆንሃል፤ በዚህ ዓመት የገቦውን፥ በሁለተኛውም ዓመት ከገቦው የበቀለውን ትበላላችሁ፤ በሦስተኛውም ዓመት ትዘራላችሁ፤ ታጭዱማላችሁ፤ ወይንንም ትተክላላችሁ፤ ፍሬውንም ትበላላችሁ። 30ያመለጠው የይሁዳ ቤት ቅሬታ ሥሩን ወደ ታች ይሰድዳል፤ ወደ ላይም ያፈራል። 31ከኢየሩሳሌም ቅሬታ ከጽዮንም ተራራ ያመለጡት ይወጣሉና፤ የሠራዊት ጌታ የእግዚአብሔር ቅንዓት ይህን ያደርጋል። 32ስለዚህም እግዚአብሔር ስለ አሦር ንጉሥ እንዲህ ይላል “ወደዚች ከተማ አይመጣም፤ ፍላጻንም አይወረውርባትም፤ በጋሻም አይመጣባትም፤ የአፈርንም ድልድል አይደለድልባትም። 33በመጣበት መንገድ በዚያው ይመለሳል፤ ወደዚህችም ከተማ አይመጣም” ይላል እግዚአብሔር። 34ስለ እኔም፥ ስለ ባሪያዬም ስለ ዳዊት ይህችን ከተማ አድናት ዘንድ እጋርዳታለሁ።’”
35በዚያችም ሌሊት የእግዚአብሔር መልአክ ወጣ፤ ከአሦራውያንም ሰፈር መቶ ሰማንያ አምስት ሺህ ገደለ፤ ማለዳም በተነሡ ጊዜ፥ እነሆ፥ ሁሉ በድኖች ነበሩ። 36የአሦርም ንጉሥ ሰናክሬም ተነሥቶ ሄደ፤ ተመልሶም በነነዌ ተቀመጠ። 37በአምላኩም በናሳራክ ቤት ሲሰግድ ልጆቹ አድራሜሌክና ሳራሳር በሰይፍ ገደሉት፤ ወደ አራራትም አገር ኰበለሉ። ልጁም አስራዶን በእርሱ ፋንታ ነገሠ።

ማድመቅ

ያጋሩ

ኮፒ

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ