ሁለተኛ መጽሐፈ ነገሥት 13
13
ኢዮአካዝ በእስራኤል ላይ እንደ ነገሠ
1በይሁዳ ንጉሥ በአካዝያስ ልጅ በኢዮአስ በሃያ ሦስተኛው ዓመት የኢዩ ልጅ ኢዮአካዝ በእስራኤል ላይ በሰማርያ ነገሠ፤ ዐሥራ ሰባትም ዓመት ነገሠ። 2በእግዚአብሔርም ፊት ክፉ ነገር አደረገ፤ እስራኤልንም ያሳተውን የናባጥን ልጅ የኢዮርብዓምን ኀጢአት ተከተለ፤ ከእርስዋም አልራቀም። 3የእግዚአብሔርም ቍጣ በእስራኤል ላይ ነደደ፤ በዘመኑም ሁሉ በሶርያው ንጉሥ በአዛሄል እጅ፥ በአዛሄልም ልጅ በቤንሀዳድ እጅ አሳልፎ ይሰጣቸው ነበር። 4ኢዮአካዝም እግዚአብሔርን ለመነ፤ እግዚአብሔርም የሶርያ ንጉሥ እስራኤልን ያስጨነቀበትን ጭንቀት አይቶአልና ሰማው። 5እግዚአብሔርም ለእስራኤል ታዳጊ ሰጠ፤ ከሶርያውያንም እጅ ዳኑ፤ የእስራኤልም ልጆች እንደ ቀድሞው ጊዜ በድንኳናቸው ተቀመጡ። 6ነገር ግን በእርስዋ ሄዱ እንጂ እስራኤልን ካሳተው ከኢዮርብዓም ቤት ኀጢአት አልራቁም፤ ደግሞም የማምለኪያ ዐፀድ በሰማርያ ቆሞ ቀረ። 7ለኢዮአካዝም ከአምሳ ፈረሰኞች፥ ከዐሥርም ሠረገሎች፥ ከዐሥር ሺህም እግረኞች በቀር ሕዝብ አልቀረለትም፤ የሶርያ ንጉሥ አጥፍቶአቸዋልና፤ በአውድማም እንዳለ ዕብቅ አድቅቆአቸዋልና። 8የቀረውም የኢዮአካዝ ነገር፥ ያደረገውም ሁሉ፥ ጭከናውም፥ በእስራኤል ነገሥታት ታሪክ መጽሐፍ የተጻፈ አይደለምን? 9ኢዮአካዝም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፤ በሰማርያም ቀበሩት፤ ልጁም ዮአስ በፋንታው ነገሠ።
ዮአስ በእስራኤል እንደ ነገሠ
10በይሁዳ ንጉሥ በኢዮአስ በሠላሳ ሰባተኛው ዓመት የኢዮአካዝ ልጅ ዮአስ በእስራኤል ላይ በሰማርያ ነገሠ፤ ዐሥራ ስድስትም ዓመት ነገሠ። 11በእግዚአብሔር ፊት ክፋ ነገር አደረገ፤ እስራኤልን በሳተው በናባጥ ልጅ በኢዮርብዓም ኀጢአት ሁሉ ሄደ እንጂ ከእርስዋ አልራቀም። 12የቀረውም የዮአስ ነገር ያደረገውም ሁሉ፥ ከይሁዳም ከአሜስያስ ጋር የተዋጋበት ጭከና፥ በእስራኤል ነገሥታት ታሪክ መጽሐፍ የተጻፈ አይደለምን? 13ዮአስም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፤ ኢዮርብዓምም በዙፋኑ ላይ ተቀመጠ፤ ዮአስም በሰማርያ ከእስራኤል ነገሥታት ጋር ተቀበረ።
የኤልሳዕ መሞት
14ኤልሳዕም በሚሞትበት በሽታ ታመመ፤ የእስራኤልም ንጉሥ ዮአስ ወደ እርሱ ወርዶ በፊቱ አለቀሰና “አባቴ ሆይ! አባቴ ሆይ! የእስራኤል ሠረገላና ፈረሰኞች፤” አለ። 15ኤልሳዕም “ቀስትና ፍላጻዎች ውሰድ፤” አለው፤ ቀስቱንና ፍላጻዎችንም ወሰደ። 16የእስራኤልንም ንጉሥ “እጅህን በቀስቱ ላይ ጫን፤” አለው። እጁንም ጫነበት፤ ኤልሳዕም እጁን በንጉሡ እጅ ላይ ጭኖ 17“የምሥራቁን መስኮት ክፈት፤” አለ፤ ከፈተውም። ኤልሳዕም “ወርውር!” አለ፤ ወረወረውም። እርሱም “የእግዚአብሔር መድኃኒት ፍላጻ ነው፤ በሶርያ ላይ የመድኃኒት ፍላጻ ነው፤ እስክታጠፋቸው ድረስ ሶርያውያንን በአፌቅ ትመታለህ፤” አለ። 18ደግሞም “ፍላጻዎቹን ውሰድ፤” አለው፤ ወሰዳቸውም። የእስራኤልንም ንጉሥ “ምድሩን ምታው፤” አለው። ሦስት ጊዜም መትቶ ቆመ። 19የእግዚአብሔርም ሰው ተቆጥቶ “አምስት ወይም ስድስት ጊዜ መትተኸው ቢሆን ኖሮ ሶርያን እስክታጠፋው ድረስ በመታኸው ነበር፤ አሁን ግን ሦስት ጊዜ ብቻ ሶርያን ትመታለህ፤” አለ።
20ኤልሳዕም ሞተ፤ ቀበሩትም። ከሞዓብም አደጋ ጣዮች በየዓመቱ ወደ አገሩ ይገቡ ነበር። 21ሰዎችም አንድ ሰው ሲቀብሩ አደጋ ጣዮችን አዩ፤ ሬሳውንም በኤልሳዕ መቃብር ውስጥ ጣሉት፤ የኤልሳዕንም አጥንት በነካ ጊዜ ሰውዮው ድኖ በእግሩ ቆመ።
በእስራኤልና በሶርያ መካከል የተደረገ ጦርነት
22የሶርያ ንጉሥ አዛሄል በኢዮአካዝ ዘመን ሁሉ እስራኤልን አስጨነቀ፤ 23እግዚአብሔር ግን ራራላቸው፤ ማራቸውም፤ ከአብርሃምና ከይስሐቅ ከያዕቆብም ጋር ስላደረገውም ቃል ኪዳን እነርሱን ተመለከተ፤ ሊያጠፋቸውም አልወደደም፤ ፈጽሞም ከፊቱ አልጣላቸውም። 24የሶርያም ንጉሥ አዛሄል ሞተ፤ ልጁም ቤንሀዳድ በፋንታው ነገሠ። 25አዛሄልም ከአባቱ ከኢዮአካዝ እጅ በሰልፍ የወሰዳቸውን ከተሞች የኢዮአካዝ ልጅ ዮአስ ከአዛሄል ልጅ ከቤንሀዳድ እጅ ወሰደ። ዮአስም ሦስት ጊዜ መታው፤ የእስራኤልንም ከተሞች መለሰ።
Currently Selected:
ሁለተኛ መጽሐፈ ነገሥት 13: አማ54
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ