የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

2 ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 11:16-33

2 ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 11:16-33 አማ54

እንደ ገና እላለሁ፦ ለማንም ሰው ሞኝ የሆንሁ አይምሰለው፤ ያለዚያ ግን እኔ ደግሞ ጥቂት እመካ ዘንድ እንደ ሞኝ እንኳ ሆኜ ተቀበሉኝ። እንደዚህ ታምኜ ስመካ የምናገረው፥ በሞኝነት እንጂ ጌታ እንዳዘዘኝ አልናገርም። ብዙዎች በዓለማዊ ነገር ስለሚመኩ እኔ ደግሞ እመካለሁ። ልባሞች ስለምትሆኑ በደስታ ሞኞችን ትታገሣላችሁና፤ ማንም ባሪያዎች ቢያደርጋችሁ፥ ማንም ቢበላችሁ፥ ማንም ቢቀማችሁ፥ ማንም ቢኮራባችሁ፥ ማንም ፊታችሁን በጥፊ ቢመታችሁ ትታገሣላችሁና። ደካሞች መስለን እንደ ነበርን በውርደት እላለሁ። ነገር ግን በሞኝነት እላለሁ፤ ማንም በሚደፍርበት እኔ ደግሞ እደፍርበታለሁ። ዕብራውያን ናቸውን? እኔ ደግሞ ነኝ። የእስራኤል ወገን ናቸውን? እኔ ደግሞ ነኝ። የአብርሃም ዘር ናቸውን? እኔ ደግሞ ነኝ። የክርስቶስ አገልጋዮች ናቸውን? እንደ እብድ ሰው እላለሁ፤ እኔ እበልጣለሁ፤ በድካም አብዝቼ፥ በመገረፍ አብዝቼ፥ በመታሰር አትርፌ፥ በመሞት ብዙ ጊዜ ሆንሁ። አይሁድ አንድ ሲጎድል አርባ ግርፋት አምስት ጊዜ ገረፉኝ። ሦስት ጊዜ በበትር ተመታሁ፤ አንድ ጊዜ በድንጋይ ተወገርሁ፤ መርከቤ ሦስት ጊዜ ተሰበረ፤ ሌሊትና ቀን በባሕር ውስጥ ኖርሁ። ብዙ ጊዜ በመንገድ ሄድሁ፤ በወንዝ ፍርሃት፥ በወንበዴዎች ፍርሃት፥ በወገኔ በኩል ፍርሃት፥ በአሕዛብ በኩል ፍርሃት፥ በከተማ ፍርሃት፥ በምድረ በዳ ፍርሃት፥ በባሕር ፍርሃት፥ በውሸተኞች ወንድሞች በኩል ፍርሃት ነበረብኝ፤ በድካምና በጥረት ብዙ ጊዜም እንቅልፍ በማጣት፥ በራብና በጥም ብዙ ጊዜም በመጦም፥ በብርድና በራቁትነት ነበርሁ። የቀረውንም ነገር ሳልቆጥር፥ ዕለት ዕለት የሚከብድብኝ የአብያተ ክርስቲያናት ሁሉ አሳብ ነው። የሚደክም ማን ነው፥ እኔም አልደክምምን? የሚሰናከል ማን ነው፥ እኔም አልናደድምን? ትምክህት የሚያስፈልግ ከሆነ፥ ከድካሜ በሚሆነው ነገር እመካለሁ። ለዘላለም የተባረከ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አምላክና አባት እንዳልዋሽ ያውቃል። በደማስቆ አርስጦስዮስ ከተባለ ንጉሥ በታች የሆነ የሕዝብ ገዥ ሊይዘኝ እየወደደ የደማስቆ ሰዎችን ከተማ ያስጠብቅ ነበር፥ በቅጥሩም ባለ መስኮት በቅርጫት አወረዱኝና ከእጁ አመለጥሁ።