ሁለተኛ መጽሐፈ ዜና መዋዕል 7
7
የቤተ መቅደሱ መመረቅ
(1ነገ. 8፥62-66)
1ሰሎሞንም ጸሎቱን በፈጸመ ጊዜ እሳት ከሰማይ ወርዶ የሚቃጠለውን መሥዋዕትና ሌላ መሥዋዕቱን በላ፤ የእግዚአብሔርም ክብር ቤቱን ሞላ። 2የእግዚአብሔርም ክብር የእግዚአብሔርን ቤት ሞልቶት ነበርና ካህናቱ ወደ እግዚአብሔር ቤት መግባት አልቻሉም። 3የእስራኤልም ልጆች ሁሉ እሳቱ ሲወርድ የእግዚአብሔርም ክብር በቤቱ ላይ ሲሆን ያዩ ነበር፤ በወለሉም ላይ በግምባራቸው ወደ ምድር ተደፍተው ሰገዱ “እርሱ መልካም ነውና፥ ምሕረቱም ለዘላለም ነውና” ብለውም እግዚአብሔርን አመሰገኑ።
4ንጉሡም ሕዝቡም ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት መሥዋዕት ያቀርቡ ነበር። 5ንጉሡም ሰሎሞን ሃያ ሁለት ሺህ በሬዎችና መቶ ሃያ ሺህ በጎች ሠዋ። እንዲሁ ንጉሡና ሕዝቡ ሁሉ የእግዚአብሔርን ቤት ቀደሱ። 6ካህናቱም በየሥርዓታቸው፥ ሌዋውያኑም ደግሞ “ምሕረቱ ለዘላለም ነውና እግዚአብሔርን አመስግኑ፤” የሚለውን የዳዊትን መዝሙር እየዘመሩ፥ ንጉሡ ዳዊት እግዚአብሔርን ለማመስገን የሠራውን የእግዚአብሔርን የዜማ ዕቃ ይዘው ቆመው ነበር፤ ካህናቱም በፊታቸው መለከት ይነፉ ነበር፤ እስራኤልም ሁሉ ቆመው ነበር። 7ሰሎሞን በእግዚአብሔር ቤት ፊት የነበረውን የአደባባዩን ውስጥ ቀደሰ፤ ሰሎሞንም የሠራው የናስ መሠዊያ የሚቃጠለውን መሥዋዕትና የእህሉን ቍርባን ስቡንም መያዝ አልቻለምና የሚቃጠለውን መሥዋዕትና የደኅንነቱን መሥዋዕት ስብ በዚያ አቀረበ።
8ሰሎሞንም ከእርሱም ጋር እጅግ ታላቅ ጉባኤ የሆኑ፥ ከሐማት መግቢያ ጀምሮ እስከ ግብጽ ወንዝ ድረስ ያሉ እስራኤል ሁሉ፥ በዚያን ጊዜ ሰባት ቀን በዓል አደረጉ። 9ሰባት ቀንም መሠዊያውን ቀድሰው፥ ሰባት ቀንም በዓል አድርገው ነበርና በስምንተኛው ቀን የተቀደሰውን ጉባኤ አደረጉ። 10በሰባተኛውም ወር በሃያ ሦስተኛውም ቀን ሕዝቡን ወደ ድንኳናቸው አሰናበተ፤ እግዚአብሔር ለዳዊትና ለሰሎሞን ለሕዝቡም ለእስራኤል ስላደረገው ቸርነት ደስ ብሎአቸው ሐሴትን እያደረጉ ሄዱ።
እግዚአብሔር ለሰሎሞን ዳግመኛ እንደ ተገለጠ
(1ነገ. 9፥1-9)
11ሰሎሞንም የእግዚአብሔርን ቤትና የንጉሡን ቤት ጨረሰ፤ በእግዚአብሔር ቤትና በራሱ ቤት ይሠራው ዘንድ በልቡ ያሰበውን ሁሉ አከናወነ። 12እግዚአብሔርም ለሰሎሞን በሌሊት ተገልጦ እንዲህ አለው “ጸሎትህን ሰምቻለሁ፤ ይህንም ስፍራ ለራሴ ለመሥዋዕት ቤት መርጫለሁ። 13ዝናብ እንዳይወርድ ሰማያቱን ብዘጋ፥ ወይም ምድሪቱን ይበላ ዘንድ አንበጣን ባዝዘው፥ ወይም በሕዝብ ላይ ቸነፈር ብሰድድ፥ 14በስሜ የተጠሩት ሕዝቤ ሰውነታቸውን አዋርደው ቢጸልዩ፥ ፊቴንም ቢፈልጉ፥ ከክፉ መንገዳቸውም ቢመለሱ፥ በሰማይ ሆኜ እሰማለሁ፤ ኀጢአታቸውንም ይቅር እላለሁ፤ ምድራቸውንም እፈውሳለሁ። 15አሁንም በዚህ ስፍራ ለሚጸለይ ጸሎት ዐይኖቼ ይገለጣሉ፤ ጆሮቼም ያደምጣሉ። 16አሁንም ስሜ ለዘላለም በዚያ ይኖር ዘንድ ይህን ቤት መርጫለሁ፤ ቀድሻለሁም፤ ዐይኖቼና ልቤም ዘወትር በዚያ ይሆናሉ። 17አንተም ደግሞ አባትህ ዳዊት እንደ ሄደ በፊቴ ብትሄድ፥ እንዳዘዝሁህም ሁሉ ብታደርግ፥ ሥርዓቴንና ፍርዴንም ብትጠብቅ፥ 18ከአባትህ ከዳዊት ጋር ‘በእስራኤል ላይ አለቃ የሚሆን ከዘርህ አይታጣም፤’ ብዬ ቃል ኪዳን እንዳደረግሁ የመንግሥትህን ዙፋን አጸናለሁ።
19“እናንተ ግን እኔን ከመከተል ብትመለሱ፥ የሰጠኋችሁንም ሥርዓቴንና ትእዛዜን ብትተዉ፥ ሄዳችሁም ሌሎችን አማልክት ብታመልኩ ብትሰግዱላቸውም፥ 20ለአባቶቻችሁ ከሰጠኋቸው ምድር እነቅላችኋለሁ፤ ለስሜም የቀደስሁትን ይህን ቤት ከፊቴ እጥለዋለሁ፤ በአሕዛብም ሁሉ መካከል ምሳሌና ተረት አደርገዋለሁ። 21ከፍ ከፍ ብሎ የነበረውንም ይህን ቤት እያዩ በዚያ የሚያልፉ ሰዎች ሁሉ ‘እግዚአብሔር በዚህ አገርና በዚህ ቤት ስለ ምን እንዲህ አደረገ?’ ብለው ይደነቃሉ። 22መልሰውም ‘ከግብጽ ምድር ያወጣቸውን የአባቶቻቸውን አምላክ እግዚአብሔርን ትተው ሌሎችን አማልክት ስለ ተከተሉ፥ ስለ ሰገዱላቸውም፥ ስለ አመለኩአቸውም፥ ስለዚህ ይህን ክፉ ነገር ሁሉ አመጣባቸው፤’ ይላሉ።”
Currently Selected:
ሁለተኛ መጽሐፈ ዜና መዋዕል 7: አማ54
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ
![None](/_next/image?url=https%3A%2F%2Fimageproxy.youversionapi.com%2F58%2Fhttps%3A%2F%2Fweb-assets.youversion.com%2Fapp-icons%2Fam.png&w=128&q=75)
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ