ሁለተኛ መጽሐፈ ዜና መዋዕል 5
5
1እንዲሁም ሰሎሞን ስለ እግዚአብሔር ቤት የሠራው ሥራ ሁሉ ተጨረሰ። አባቱም ዳዊት የቀደሰውን የብርና የወርቅ ዕቃ ሁሉ ሰሎሞን አምጥቶ በእግዚአብሔር ቤት ውስጥ በነበረው ግምጃ ቤት አኖረው።
የቃል ኪዳኑ ታቦት ወደ ቤተ መቅደስ እንደ ገባ
(1ነገ. 8፥1-9)
2በዚያን ጊዜም ሰሎሞን የእግዚአብሔርን ቃል ኪዳን ታቦት ከዳዊት ከተማ ከጽዮን ያመጡ ዘንድ የእስራኤልን ሽማግሌዎችና የነገድ አለቆችን ሁሉ የእስራኤልንም ልጆች አባቶች ቤቶች መሳፍንት ወደ ኢየሩሳሌም ሰበሰበ። 3የእስራኤልም ሰዎች ሁሉ በሰባተኛው ወር በበዓሉ ጊዜ ወደ ንጉሡ ተከማቹ። 4የእስራኤልም ሽማግሌዎች ሁሉ መጡ፤ ሌዋውያንም ታቦቱን አነሡ። 5ታቦቱንም የመገናኛውንም ድንኳን በድኳኑም ውስጥ የነበረውን የተቀደሰውን ዕቃ ሁሉ አመጡ፤ እነዚህንም ሁሉ ካህናቱና ሌዋውያኑ አመጡ። 6ንጉሡም ሰሎሞን ከእርሱም ጋር የተሰበሰቡ የእስራኤል ማኀበር ሁሉ በታቦቱ ፊት ሆነው ከብዛት የተነሣ የማይቈጠሩትንና የማይመጠኑትን በጎችና በሬዎች ይሠዉ ነበር። 7ካህናቱም የእግዚአብሔርን ቃል ኪዳን ታቦት ወደ ቤቱ አምጥተው በቅድስተ ቅዱሳን ውስጥ ከኪሩቤል ክንፍ በታች በነበረው በስፍራው አኖሩት። 8ኪሩቤልም በታቦቱ ስፍራ ላይ ክንፎቻቸውን ዘርግተው ነበር፤ ኪሩቤልም ታቦቱንና መሎጊያዎቹን በስተ ላዩ በኩል ይሸፍኑ ነበር። 9መሎጊያዎቹም ረጃጅሞች ነበሩና በቅድስተ ቅዱሳን ፊት ከመቅደሱ ውስጥ ጫፎቻቸው ይታዩ ነበር፤ ነገር ግን ከውጪ አይታዩም ነበር፤ እስከ ዛሬም ድረስ እዚያ አሉ። 10በታቦቱም ውስጥ የእስራኤል ልጆች ከግብጽ ምድር በወጡ ጊዜ፥ እግዚአብሔርም ከእነርሱ ጋር ቃል ኪዳን ባደረገ ጊዜ ሙሴ በኮሬብ ካስቀመጣቸው ከሁለቱ ጽላቶች በቀር ምንም አልነበረበትም።
የእግዚአብሔር ክብር መገለጥ
(1ነገ. 8፥10-11)
11በዚያም የነበሩት ካህናት ሁሉ ተቀድሰው ነበር፤ በሰሞናቸውም አልተከፈሉም ነበር፤ 12መዘምራንም የነበሩት ሌዋውያን ሁሉ፥ አሳፍና ኤማን ኤዶታምም ልጆቻቸውም ወንድሞቻቸውም ጥሩ በፍታ ለብሰው ጽናጽልና በገና መሰንቆም እየመቱ በመሠዊያው አጠገብ በምሥራቅ በኩል ቆመው ነበር፤ ከእነርሱም ጋር መቶ ሃያ ካህናት መለከት ይነፉ ነበር። ካህናቱም ከመቅደሱ በወጡ ጊዜ፥ 13መለከቱንም የሚነፉ መዘምራኑም በአንድነት ሆነው እግዚአብሔርን እያመሰገኑና እያከበሩ “እግዚአብሔር ቸር ነውና፥ ምሕረቱም ለዘላለም ነውና እግዚአብሔርን አመስግኑ!” እያሉ በአንድ ቃል ድምጻቸውን ወደ ላይ ከፍ አድርገው በመለከትና በጸናጽል በዜማም ዕቃ ሁሉ እግዚአብሔርን ባመሰገኑ ጊዜ፥ ደመናው የእግዚአብሔርን ቤት ሞላው። 14የእግዚአብሔርም ክብር የእግዚአብሔርን ቤት ሞልቶት ነበርና ካህናቱ ከደመናው የተነሣ መቆምና ማገልገል አልተቻላቸውም።
Currently Selected:
ሁለተኛ መጽሐፈ ዜና መዋዕል 5: አማ54
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ