ሁለተኛ መጽሐፈ ዜና መዋዕል 36:15-21

ሁለተኛ መጽሐፈ ዜና መዋዕል 36:15-21 አማ54

የአባቶቻቸውም አምላክ እግዚአብሔር ለሕዝቡና ለማደሪያው ስላዘነ ማለዳ ተነሥቶ በመልክተኞቹ እጅ ወደ እነርሱ ይልክ ነበር። እነርሱ ግን የእግዚአብሔር ቍጣ በሕዝቡ ላይ እስኪወጣ ድረስ፥ ፈውስም እስከማይገኝላቸው ድረስ፥ በእግዚአብሔር መልክተኞች ይሳለቁ፥ ቃሉንም ያቃልሉ፥ በነቢያቱም ላይ ያፌዙ ነበር። ስለዚህም የከለዳውያንን ንጉሥ አመጣባቸው፤ እርሱም ጕልማሶቻቸውን በቤተመቅደሱ ውስጥ በሰይፍ ገደላቸው፤ ጕልማሳውንና ቈንጆይቱን ሽማግሌውንና አሮጌውን አልማረም፤ ሁሉንም በእጁ አሳልፎ ሰጠው። የእግዚአብሔርንም ቤት ዕቃ ሁሉ፥ ታላቁንና ታናሹን፥ የእግዚአብሔርንም ቤት መዝገብ፥ የንጉሡንና የአለቆቹን መዝገብ፥ እነዚህን ሁሉ ወደ ባቢሎን ወሰደ። የእግዚአብሔርንም ቤት አቃጠሉ፤ የኢየሩሳሌምንም ቅጥር አፈረሱ፤ አዳራሾችዋንም በእሳት አቃጠሉ፤ መልካሙንም ዕቃዋን ሁሉ አጠፉ። ከሰይፍም ያመለጡትን ወደ ባቢሎን ማረካቸው፤ የፋርስ ንጉሥም እስኪነግሥ ድረስ ለንጉሡና ለልጆቹ ባሪያዎች ሆኑ፤ በኤርምያስ አፍ የተናገረው የእግዚአብሔር ቃል እንዲፈጸም፥ ምድሪቱ ሰንበትን በማድረግዋ እስክታርፍ ድረስ፥ በተፈታችበትም ዘመን ሁሉ ሰባ ዓመት እስኪፈጸም ድረስ ሰንበትን አገኘች።