ሁለተኛ መጽሐፈ ዜና መዋዕል 28
28
አካዝ በይሁዳ እንደነገሠ (2ነገ. 16፥1-4)
1አካዝ መንገሥ በጀመረ ጊዜ የሃያ ዓመት ጕልማሳ ነበረ፤ በኢየሩሳሌምም አሥራ ስድስት ዓመት ነገሠ፤ እንደ አባቱም እንደ ዳዊት በእግዚአብሔር ፊት ቅን ነገር አላደረገም። 2ነገር ግን በእስራኤል ነገሥታት መንገድ ሄደ፤ ደግሞም ለበኣሊም ቀልጠው የተሠሩትን ምስሎችን ሠራ። 3ደግሞም በሄኖም ልጅ ሸለቆ ውስጥ ዐጠነ፤ እግዚአብሔር ከእስራኤል ልጆች ፊት እንዳሳደዳቸው እንደ አሕዛብም ክፉ ልማድ ልጆቹን በእሳት አቃጠለ። 4በኮረብታው መስገጃዎችና በተራሮች ላይ በለመለመውም ዛፍ ሁሉ በታች ይሠዋና ያጥን ነበር።
ሶርያና እስራኤል ይሁዳን ድል ማድረጋቸው (2ነገ. 16፥ 5-6)
5ስለዚህ አምላኩ እግዚአብሔር በሶርያ ንጉሥ እጅ አሳልፎ ሰጠው፤ ሶሪያውያንም መቱት፤ ከእርሱም ብዙ ምርኮኞች ወስደው ወደ ደማስቆ አመጡ። ደግሞም በእስራኤል ንጉሥ እጅ አሳልፎ ሰጠው፤ እርሱም በታላቅ አመታት መታው። 6የአባቶቻቸውንም አምላክ እግዚአብሔርን ትተው ነበርና የሮሜልዩ ልጅ ፋቁሔ በአንድ ቀን ከይሁዳ መቶ ሃያ ሺህ ገደለ፤ ሁሉም ጽኑአን ነበሩ። 7ከኤፍሬም ወገን የነበረው ኃይል ሰው ዝክሪ የንጉሡን ልጅ መዕሤያንና የቤቱን አዛዥ ዓዝሪቃምን፥ ለንጉሡም በማዕረግ ሁለተኛ የሆነውን ሕልቃናን ገደለ። 8የእስራኤል ልጆች ከወንድሞቻቸው ሁለት መቶ ሺህ ሴቶችን፥ ወንዶችና ሴቶች ልጆችንም ማረኩ፥ እጅግም ምርኮ ከእነርሱ ወስደው ወደ ሰማርያ አገቡ።
የነቢዩ ዖዴድ ተግሣፅ
9በዚያም ዖዴድ የተባለ የእግዚአብሔር ነቢይ ነበረ፤ ወደ ሰማርያም የሚመጣውን ጭፍራ ሊገናኘው ወጣ፤ እንዲህም አላቸው “እነሆ፥ የአባቶቻችሁ አምላክ እግዚአብሔር ይሁዳን ስለ ተቍጣ በእጃችሁ አሳልፎ ሰጣቸው፤ እናንተም ወደ ሰማይ በሚደርስ ቍጣ ገደላችኋቸው። 10አሁንም የይሁዳና የኢየሩሳሌም ልጆች ባሪያዎች ሆነው ይገዙላችሁ ዘንድ ታስባላችሁ፤ ነገር ግን አምላካችሁን እግዚአብሔርን የበደላችሁት በደል በእናንተ ዘንድ የለምን? 11አሁንም ስሙኝ፤ የእግዚአብሔር ቍጣ በላያችሁ ነድዶአልና ከወንድሞቻችሁ የወሰዳችኋቸውን ምርኮኞች መልሱ።” 12ደግሞም ከኤፍሬም ልጆች አለቆች የዮሐናን ልጅ ዓዛርያስ፥ የምሺሌሞትም ልጅ በራክያ፥ የሰሎምም ልጅ ይሒዝቅያ፥ የሐድላይም ልጅ ዓሜሳይ ከሰልፍ በተመለሱት ላይ ተቃወሙአቸው። 13ደግሞም “በእግዚአብሔር ፊት በእኛ ላይ በደል ታመጡብናላችሁና፥ ኃጢያታችንንና በደላችንን ታበዙብናላችሁና የተማረኩትን ወደዚህ አታግቡ፤ በደላችን ታላቅ ነውና፥ የመቅሰፍቱም ቍጣ በእስራኤል ላይ ነውና” አሉአቸው። 14ሰልፈኞቹም ምርኮኞቹንና ምርኮውን በአለቆችና በጉባኤው ሁሉ ፊት ተው። 15በስማቸውም የተጻፉ ሰዎች ተነሥተው ምርኮኞቹን ወሰዱ፤ በመካከላቸውም ራቁታቸውን ለነበሩት ሁሉ ከምርኮው አለበሱአቸው፤ አጎናጸፉአቸውም፤ ጫማም በእግራቸው አደረጉላቸው፤ መገቡአቸውም፤ አጠጡአቸውም፤ ቀቡአቸውም፤ ደካሞቹንም ሁሉ በአህዮች ላይ አስቀመጡአቸው፤ ዘንባባም ወዳለበት ከተማ ወደ ኢያሪኮ ወደ ወንድሞቻቸው አመጡአቸው፤ ወደ ሰማሪያም ተመለሱ።
አካዝ የአሦርን እርዳታ መጠየቁ (2ነገ. 16፥ 7-9)
16በዚያን ጊዜም ንጉሡ አካዝ እርዳታ ፈልጎ ወደ አሦር ንጉሥ ላከ፤ 17የኤዶምያስ ሰዎች ዳግመኛ መጥተው፥ ይሁዳንም መትተው ብዙ ምርኮኛ ወስደው ነበርና። 18ደግሞም ፍልስጤማውያን በቈላውና በደቡብ በኩል ባሉት በይሁዳ ከተሞች አደጋ ጥለው ነበር፤ ቤትሳሚስንና ኤሎንን፥ ግዴሮትንም፥ ሦኮንና መንደሮችዋን፥ ተምናንና መንደሮችዋን፥ ጊምዞንና መንደሮችዋን ወስደው በዚያ ተቀምጠው ነበር። 19የይሁዳም ንጉሥ አካዝ እግዚአብሔርን ክዶአልና፥ ከእርሱም እጅግ ርቍልና እግዚአብሔር ስለ እርሱ ይሁዳን አዋረደው። 20የአሦርም ንጉሥ ቴልጌልቴልፌልሶር መጥቶ አስጨነቀው እንጂ አልረዳውም። 21አካዝም ከእግዚአብሔር ቤት ከንጉሡና ከአለቆቹም ቤት እኵሌታውን ገፈፈ፤ ለአሦርም ንጉሥ ሰጠ፤ ነገር ግን አንዳች አልተጠቀመበትም።
የአካዝ በደልና ሞት
22ይህም ንጉሥ አካዝ በተጨነቀ ጊዜ እግዚአብሔርን መበደል አበዛ። 23ለመቱትም ለደማስቆ አማልክት “የሶሪያን ነገሥታት አማልክት ረድተዋቸዋልና እኔን ይረዱ ዘንድ እሠዋላቸዋለሁ” ብሎ ሠዋላቸው። ነገር ግን ለእርሱና ለእስራኤል ሁሉ እንቅፋት ሆኑ። 24አካዝም የእግዚአብሔርን ቤት ዕቃዎች ሁሉ ወስዶ ሰባበራቸው፤ የእግዚአብሔርንም ቤት ደጅ ቈለፈ፤ በኢየሩሳሌምም ማዕዘን ሁሉ መሠዊያ ሠራ። 25በይሁዳም ከተሞች ሁሉ ለሌሎች አማልክት ያጥን ዘንድ የኮረብታ መስገጃዎች አሠራ፤ የአባቶቹንም አምላክ እግዚአብሔርን አስቈጣ። 26የቀረውም ነገርና ሥራው ሁሉ፥ የፊተኛውና የኋለኛው፥ እነሆ፥ በይሁዳና በእስራኤል ነገሥታት መጽሐፍ ተጽፎአል። 27አካዝም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፤ በከተማይቱም በኢየሩሳሌም ቀበሩት፤ ነገር ግን ወደ እስራኤል ነገሥታት መቃብር አላገቡትም፤ ልጁም ሕዝቅያስ በእርሱ ፋንታ ነገሠ።
Currently Selected:
ሁለተኛ መጽሐፈ ዜና መዋዕል 28: አማ54
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ