የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ሁለተኛ መጽሐፈ ዜና መዋዕል 2

2
ቤተ መቅደሱን ለመሥራት የተደረገ ዝግጅት
(1ነገ. 5፥1-18)
1ሰሎሞንም ለእግዚአብሔር ስም ቤት፥ ለመንግሥቱም ቤት ይሠራ ዘንድ አሰበ። 2ሰሎሞንም የሚሸከሙትን ሰባ ሺህ፥ ከተራሮችም የሚጠርቡትን ሰማኒያ ሺህ፥ በእነርሱም ላይ የተሾሙትን ሦስት ሺህ ስድስት መቶ ሰዎች ቈጠረ። 3ሰሎሞንም እንዲህ ሲል ወደ ጢሮስ ንጉሥ ወደ ኪራም ላከ “ከአባቴ ከዳዊት ጋር እንዳደረግህ፥ የሚቀመጥበትንም ቤት ይሠራ ዘንድ የዝግባ እንጨት እንደ ሰደድህለት፥ እንዲሁ ለእኔ አድርግ። 4እነሆ፥ ለእስራኤል ለዘላለም እንደ ታዘዘው በእግዚአብሔር ፊት የጣፋጩን ሽቱ ዕጣን ለማጠን፥ የገጹንም ኅብስት ለማኖር፥ የሚቃጠለውንም መሥዋዕት በጥዋትና በማታ በሰንበታቱም በመባቻዎቹም በአምላካችንም በእግዚአብሔር በዓላት ለማቅረብ ለአምላኬ ለእግዚአብሔር ስም ቤት እሠራና እቀድስ ዘንድ አሰብሁ። 5አምላካችንም ከአማልክት ሁሉ በላይ ታላቅ ነውና የምሠራው ቤት ታላቅ ነው። 6ነገር ግን ሰማይና ከሰማያት በላይ ያለ ሰማይ ይይዘው ዘንድ አይችልምና ለእርሱ ቤት ይሠራ ዘንድ ማን ይችላል? በፊቱ ዕጣን ከማጠን በቀር ቤት እሠራለት ዘንድ እኔ ማን ነኝ? 7አሁንም አባቴ ዳዊት ካዘጋጃቸው በእኔ ዘንድ በይሁዳና በኢየሩሳሌም ካሉት ብልሃተኞች ጋር የሚሆን፥ ወርቁንና ብሩን፥ ናሱንና ብረቱን፥ ሐምራዊውንና ቀዩን ሰማያዊውንም ግምጃ የሚሠራ፥ ቅርጽንም የሚያውቅ ብልሃተኛ ሰው ላክልኝ። 8ደግሞም ባሪያዎችህ ከሊባኖስ እንጨት መቍረጥ እንዲያውቁ እኔ አውቃለሁና ከሊባኖስ የዝግባና የጥድ የሰንደልም እንጨት ስደድልኝ። 9የምሠራውም ቤት እጅግ ታላቅና ድንቅ ይሆናልና ብዙ እንጨት ያዘጋጁልኝ ዘንድ፥ እነሆ፥ ባሪያዎቼ ከባሪያዎችህ ጋር ይሆናሉ። 10እነሆም፥ እንጨቱን ለሚቈርጡ ለባሪያዎችህ ሃያ ሺህ የቆሮስ መስፈሪያ የተበጠረ ስንዴ፥ ሃያ ሺህም የቆሮስ መስፈሪያ ገብስ፥ ሃያ ሺህም የባዶስ መስፈሪያ የወይን ጠጅ፥ ሃያ ሺህም የባዶስ መስፈሪያ ዘይት እሰጣለሁ።”
11የጢሮስ ንጉሥ ኪራምም “እግዚአብሔር ሕዝቡን ወድዶአልና በላያቸው አነገሠህ፤” ብሎ ለሰሎሞን መልእክት ላከ። 12ኪራምም ደግሞ አለ “ሰማይንና ምድርን የፈጠረ፥ ለእግዚአብሔርም ቤት ለመንግሥቱም ቤት ይሠራ ዘንድ ጥበበኛና ብልሃተኛ አስተዋይም ልጅ ለንጉሡ ለዳዊት የሰጠ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ቡሩክ ይሁን። 13አሁንም ከብልሃተኛዎችህ ጋር ከጌታዬም ከአባትህ ከዳዊት ብልሃተኞች ጋር ይሆን ዘንድ ኪራምአቢ የሚባል ብልሃተኛና አስተዋይ ሰው ሰድጄልሃለሁ። 14እናቱ ከዳን ልጆች ናት፤ አባቱም የጢሮስ ሰው ነው፤ ወርቁንና ብሩንም፥ ናሱንና ብረቱን፥ ድንጋይንና እንጨቱን፥ ሐምራዊውንና ሰማያዊውን ቀዩንም ግምጃ፥ ጥሩውንም በፍታ ይሠራ ዘንድ፥ ቅርጽም ሌላም ነገር ሁሉ ያደርግ ዘንድ ያውቃል። 15አሁንም ጌታዬ የተናገረውን ስንዴውንና ገብሱን ዘይቱንና የወይን ጠጁን ወደባሪያዎቹ ይስደድ፤ 16እኛም ከሊባኖስ የምትሻውን ያህል እንጨት እንቈርጣለን፤ በታንኳም አድርገን በባሕር ላይ ወደ አንተ ወደ ኢዮጴ እንሰድዳለን፤ አንተም ወደ ኢየሩሳሌም ታስወስደዋለህ።”
17ሰሎሞንም በእስራኤል ምድር የነበሩትን መጻተኞች ሁሉ አባቱ ዳዊት እንደ ቈጠራቸው ቈጠረ፤ መቶ አምሳ ሦስት ሺህ ስድስት መቶ ተገኙ። 18ከእነርሱም የሚሸከሙትን ሰባ ሺህ፥ በተራሮችም ላይ የሚጠርቡትን ሰማንያ ሺህ፥ በሕዝቡም ሥራ ላይ የተሾሙትን ሦስት ሺህ ስድስት መቶ አደረገ።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ