የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ሁለተኛ መጽሐፈ ዜና መዋዕል 1

1
ንጉሥ ሰሎሞን ከእግዚአብሔር ጥበብን እንደ ለመነ
(1ነገ. 3፥1-15)
1የዳዊት ልጅ ሰሎሞንም በመንግሥቱ በረታ፤ አምላኩም እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ነበረ፤ እጅግም አገነነው። 2ሰሎሞንም ለእስራኤል ሁሉ፥ ለሻለቆች፥ ለመቶ አለቆችም፥ ለፈራጆችም፥ በእስራኤልም ሁሉ ዘንድ ለነበሩ መሳፍንት ሁሉ፥ ለአባቶች ቤቶች አለቆች ተናገረ። 3ሰሎሞንም ከእርሱም ጋር ጉባኤው ሁሉ የእግዚአብሔር ባሪያ ሙሴ በምድረ በዳ የሠራው የእግዚአብሔር መገናኛ ድንኳን በዚያ ነበረና በገባዖን ወዳለው የኮረብታው መስገጃ ሄዱ። 4ለእግዚአብሔር ታቦት ግን ዳዊት በኢየሩሳሌም ድንኳን ተክሎለት ነበርና ዳዊት ከቂርያትይዓሪም ወዳዘጋጀለት ስፍራ አምጥቶት ነበር። 5የሆርም ልጅ የኡሪ ልጅ ባስልኤል የሠራው የናስ መሠዊያ በዚያ በእግዚአብሔር ማደሪያ ፊት ነበረ፤ ሰሎሞንም ጉባኤውም ይህን ይፈልጉት ነበር። 6ሰሎሞንም በእግዚአብሔር ፊት በመገናኛው ድንኳን አጠገብ ወዳለው ወደ ናሱ መሠዊያ ወጣ፤ በዚያም አንድ ሺህ የሚቃጠል መሥዋዕት አቀረበ።
7በዚያም ሌሊት እግዚአብሔር “ምን እንድሰጥህ ለምነኝ፤” ሲል ለሰሎሞን ተገለጠ። 8ሰሎሞንም እግዚአብሔርን አለው “ከአባቴ ከዳዊት ጋር ታላቅ ምሕረት አድርገሃል፤ በእርሱም ፋንታ አንግሠኸኛል። 9አሁንም፥ አቤቱ አምላክ ሆይ! ቍጥሩ እንደ ምድር ትቢያ በሆነው በብዙ ሕዝብ ላይ አንግሠኸኛልና ለአባቴ ለዳዊት የሰጠኸው ተስፋ ይጽና። 10አሁንም በዚህ ሕዝብ ፊት እወጣና እገባ ዘንድ ጥበብንና እውቀትን ስጠኝ፤ ይህን በሚያህል በዚህ በታላቅ ሕዝብህ ላይ ይፈርድ ዘንድ የሚችል የለምና።” 11እግዚአብሔርም ሰሎሞንን “ይህ በልብህ ነበረና፥ ባለጠግነትንና ሀብትን ክብርንና የጠላቶችህን ነፍስ ረጅምም ዕድሜን አልለመንህምና፥ ነገር ግን ባነገሥሁህ በሕዝቤ ላይ ለመፍረድ ትችል ዘንድ ጥበብንና እውቀትን ለራስህ ለምነሃልና 12ጥበብንና እውቀትን ሰጥቼሃለሁ፤ ከአንተ በፊትም ከነበሩት ከአንተም በኋላ ከሚነሡት ነገሥታት አንድ ስንኳ የሚመስልህ እንዳይኖር ባለጠግነትንና ሀብትን ክብርንም እሰጥሃለሁ፤” አለው። 13ሰሎሞንም በገባዖን ካለው ከኮረብታው መስገጃ ከመገናኛው ድንኳን ወደ ኢየሩሳሌም መጣ፤ በእስራኤልም ላይ ነገሠ።
የንጉሥ ሰሎሞን ሥልጣንና ሀብት
(1ነገ. 10፥26-29)
14ሰሎሞንም ሠረገሎችንና ፈረሰኞችን ሰበሰበ፤ አንድ ሺህ አራት መቶም ሠረገሎች፥ ዐሥራ ሁለት ሺህም ፈረሰኞች ነበሩት፤ በሠረገሎች ከተሞችና ከእርሱ ጋር በኢየሩሳሌም አኖራቸው። 15ንጉሡም ብሩንና ወርቁን በኢየሩሳሌም እንደ ድንጋይ እንዲበዛ አደረገው፤ የዝግባም እንጨት ብዛት በቈላ እንደሚበቅል ሾላ ሆነ። 16ሰሎሞንም ፈረሶችን ከግብጽና ከቀዌ አስመጣ፤ የንጉሡም ነጋዴዎች በገንዘብ እየገዙ ከቀዌ ያመጡአቸው ነበር። 17አንዱም ሠረገላ በስድስት መቶ፥ አንዱም ፈረስ በመቶ አምሳ ሰቅል ብር ከግብጽ ይወጣ ነበር፤ እንዲሁም ለኬጢያውያንና ለሶርያ ነገሥታት ሁሉ በእጃቸው ያመጡላቸው ነበር።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ