ሁለተኛ መጽሐፈ ዜና መዋዕል 18
18
ሚክያስ በአክዓብ ላይ ትንቢት እንደተናገረ (1ነገ.22፥1-28)
1ለኢዮሳፍጥም ብዙ ብልጥግናና ክብር ነበረው፤ ለአክዓብም ጋብቻ ሆነ። 2ከጥቂት ዓመት በኋላም ወደ አክዓብ ወደ ሰማርያ ወረደ። አክዓብም ለእርሱና ከእርሱ ጋር ለነበሩት ሕዝብ ብዙ በጎችና በሬዎችን አረደ፤ ከእርሱም ጋር ወደ ሬማት ዘገለዓድ ይሄድ ዘንድ አባበለው። 3የእስራኤልም ንጉሥ አክዓብ የይሁዳን ንጉሥ ኢዮሣፍጥን “ከእኔ ጋር ወደ ሬማት ዘገለዓድ ትሄዳለህን?” አለው። እርሱም“እኔ እንደ አንተ ነኝ፤ ሕዝቤም እንደ ሕዝብህ ናቸው፤ በሰልፍም ከአንተ ጋር እንሆናለን” ብሎ መለሰለት።
4ኢዮሳፍጥም የእስራኤልን ንጉሥ“የእግዚአብሔርን ቃል አስቀድመህ ትጠይቅ ዘንድ እለምንሃለሁ” አለው። 5የእስራኤልም ንጉሥ ነቢያቱን አራት መቶ ሰዎች ሰብስቦ“ወደ ሬማት ዘገለዓድ ለሰልፍ ልሂድን? ወይስ ልቅር?” አላቸው። እነርሱም “እግዚአብሔር በንጉሡ እጅ አሳልፎ ይሰጣታልና ውጣ” አሉት። 6ኢዮሳፍጥ ግን “እንጠይቀው ዘንድ የእግዚአብሔር ነብይ የሆነ ሌላ ሰው በዚህ አይገኝምን?” አለ። 7የእስራኤልም ንጉሥ ኢዮሳፍጥን “እግዚአብሔርን የምንጠይቅበት አንድ ሰው አለ፤ ነገር ግን ሁል ግዜ ክፉ እንጅ ከቶ መልካም ትንቢት አይናገርልኝምና እጠላዋለሁ፤ እርሱም የይምላ ልጅ ሚክያስ ነው” አለው። ኢዮሳፍጥም “ንጉሥ እንዲህ አይበል” አለው። 8የእስራኤልም ንጉሥ አንድ ጃንደረባ ጠርቶ “የይምላን ልጅ ሚክያስን ፈጥነህ አምጣው” አለው። 9የእስራኤል ንጉሥና የይሁዳ ንጉሥ ኢዮሳፍጥ ልብሰ መንግሥት ለብሰው በሰማርያ በር መግቢያ አጠገብ በአደባባይ በዙፋኖቻቸው ላይ ተቀምጠው ነበር፤ ነቢያትም ሁሉ በፊታቸው ትንቢትን ይናገሩ ነበር። 10የክንዓና ልጅ ሰዴቅያስም የብረት ቀንዶች ሠርቶ “እግዚአብሔር እንዲህ ይላል ‘ሶሪያውያንን እስኪጠፉ ድረስ በእነዚህ ትወጋለህ’” አለ። 11ነቢያትም ሁሉ “እግዚአብሔር በንጉሡ እጅ አሳልፎ ይሰጣታልና ወደ ሬማት ዘገለዓድ ሂድና ተከናወን” እያሉ እንዲሁ ትንቢት ይናገሩ ነበር።
12ሚክያስንም ሊጠራ የሄደ መልክተኛ “እነሆ፥ ነቢያት በአንድ አፍ ሆነው ለንጉሡ መልካም ይናገራሉ፤ ቃልህም እንደ ቃላቸው እንዲሆን መልካም እንድትናገር እለምንሃለሁ” አለው። 13ሚክያስም “ሕያው እግዚአብሔርን! አምላኬ የሚለውን እርሱን እናገራለሁ” አለ። 14ወደ ንጉሡም በመጣ ጊዜ ንጉሡ “ሚክያስ ሆይ! ወደ ሬማት ዘገለዓድ ለሰልፍ እንሂድን? ወይስ እንቅር?” አለው። እርሱም “ውጣ፤ ተከናወን፤ በእጅህም አልፈው ይሰጣሉ” አለ። 15ንጉሡም “በእግዚአብሔር ስም ከእውነት በቀር እንዳትነግረኝ ስንት ጊዜ አምልሃለሁ?” አለው። 16እርሱም “እስራኤል ሁሉ ጠባቂ እንደሌላቸው በጎች በተራሮች ላይ ተበትነው አየሁ፤ እግዚአብሔርም ‘ለእነዚህ ጌታ የላቸውም፤ እያንዳንዱም በሰላም ወደ ቤቱ ይመለስ’ አለ” ብሎ ተናገረ። 17የእስራኤልም ንጉሥ ኢዮሳፍጥን “ክፉ እንጂ መልካም ትንቢት አይናገርልኝም አላልሁህምን?” አለው። 18ሚክያስም አለ “እንግዲህ የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ፤ እግዚአብሔር በዙፋኑ ተቀምጦ፥ የሰማይም ሠራዊት ሁሉ በቀኙና በግራው ቆመው አየሁ። 19እግዚአብሔርም ‘ወጥቶ በሬማት ዘገለዓድ ይወድቅ ዘንድ የእስራኤልን ንጉሥ አክዓብን የሚያታልል ማን ነው?’ አለ። አንዱም እንደዚህ፥ ሌላውም እንደዚያ ያለ ነገር ተናገረ። 20መንፈስም መጣ፤ በእግዚአብሔርም ፊት ቆሞ ‘እኔ አታልልዋለሁ’ አለ። እግዚአብሔርም ‘በምን?’ አለው። 21እርሱም ‘ወጥቼ በነቢያቱ ሁሉ አፍ ሐሰተኛ መንፈስ እሆናለሁ’ አለ። እግዚአብሔርም ‘ታታልለዋለህ፤ ይቀናሃል፤ ውጣ፥ እንዲህም አድርግ’ አለ። 22አሁንም፥ እነሆ፥ እግዚአብሔር በእነዚህ በነቢያትህ አፍ ሐሰተኛ መንፈስን አድርጎአል፤ እግዚአብሔርም በአንተ ላይ ክፉ ተናግሮብሃል።”
23የክንዓናም ልጅ ሴዴቅያስ ቀረበ፤ ሚክያስንም በጥፊ መታውና “የእግዚአብሔር መንፈስ ከአንተ ጋር ይናገር ዘንድ በምን መንገድ ከእኔ አለፈ?” አለ። 24ሚክያስም “እነሆ፥ በዚያን ቀን ልትሸሸግ ወደ እልፍኝህ ስትሄድ ታያለህ” አለ። 25የእስራኤልም ንጉሥ “ሚክያስን ውሰዱ፤ ወደ ከተማይቱም አለቃ ወደ አሞን፥ ወደ ንጉሡም ልጅ ወደ ኢዮአስ መልሳችሁ፤ 26ንጉሡ እንዲህ ይላል ‘በደኅና እስክመለስ ድረስ ይህን ሰው በግዞቱ አኑሩት፤ የመከራም እንጀራ መግቡት፤ የመከራም ውኃ አጠጡት በሉ’ አለ።” 27ሚክያስም “በደህና ብትመለስ እግዚአብሔር በእኔ የተናገረ አይደለም” አለ። ደግሞም “እናንተ ሕዝብ ሁሉ፥ ስሙኝ” አለ።
አክዓብ በሬማት ዘገለዓድ እንደተገደለ (1ነገ.22፥29-35)
28የእስራኤል ንጉሥና የይሁዳ ንጉሥ ኢዮሣፍጥ ወደ ሬማት ዘገለዓድ ወጡ። 29የእስራኤል ንጉሥም ኢዮሣፍጥን “ልብሴን ለውጬ ወደ ሰልፍ እገባለሁ፤ አንተ ግን ልብስህን ልበስ” አለው። የእስራኤልም ንጉሥ ልብሱን ለወጠ፤ ወደ ሰልፍም ገቡ። 30የሶርያም ንጉሥ የሰረገሎቹን አለቆች “ከእስራኤል ንጉሥ በቀር ትንሽ ቢሆን ወይም ትልቅ ከማናቸውም ጋር አትጋጠሙ” ብሎ አዝዞ ነበር። 31የሰረገሎችም አለቆች ኢዮሣፍጥን ባዩ ጊዜ “የእስራኤል ንጉሥ ነው” አሉ፤ ሊጋጠሙትም ከበቡት፤ ኢዮሣፍጥ ግን ጮኸ፤ እግዚአብሔርም ረዳው፤ አምላኩም ከእርሱ መለሳቸው። 32የሰረገሎቹም አለቆች የእስራኤል ንጉሥ እንዳልሆነ ባዩ ጊዜ እርሱን ከማሳደድ ተመለሱ። 33አንድ ሰውም ቀስቱን በድንገት ገትሮ የእስራኤልን ንጉሥ በጥሩሩ መጋጠሚያ በኩል ሳንባውን ወጋው። ሰረጋለኛውንም “ተወግቻለሁና እጅህን ግታ፤ ከሰልፍም ውስጥ አውጣኝ” አለው። 34በዚያም ቀን ሰልፍ በረታ፤ የእስራኤልም ንጉሥ በሶርያውያን ፊት እስከ ማታ ድረስ በሰረገላው ላይ ራሱን ይደግፍ ነበር፤ ፀሐይም በገባ ጊዜ ሞተ።
Currently Selected:
ሁለተኛ መጽሐፈ ዜና መዋዕል 18: አማ54
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ