ሁለተኛ መጽሐፈ ዜና መዋዕል 16
16
በይሁዳና በእስራኤል መካከል የተደረገ ጦርነት (1ነገ.15፥17-22)
1አሳ በነገሠ በሠላሳ ስድስተኛው ዓመት የእስራኤል ንጉሥ ባኦስ በይሁዳ ላይ ወጣ፤ ወደ ይሁዳም ንጉሥ ወደ አሳ ማንም መውጣትና መግባት እንዳይችል ራማን ሠራ። 2አሳም ከእግዚአብሔር ቤትና ከንጉሡ ቤት መዝገብ ብርና ወርቅ ወስዶ 3“በአባቴና በአባትህ መካከል እንደ ነበረው ቃል ኪዳን በእኔና በአንተ መካከል ይሆናል፤ እነሆ፥ ብርና ወርቅ ሰድጄልሃለሁ፤ እርሱ ከእኔ ዘንድ እንዲርቅ ሄደህ ከእስራኤል ንጉሥ ከባኦስ ጋር ያለህን ቃል ኪዳን አፍርስ” ብሎ በደማስቆ ወደተቀመጠው ወደ ሶሪያ ንጉሥ ወደ ቤንሀዳድ ሰደደ። 4ቤንሀዳድ ንጉሡን አሳን“እሺ” አለው፤ የሠራዊቱንም አለቆች በእስራኤል ከተሞች ላይ ሰደደ፤ እነርሱም ዒዮንንና ዳንን፥ አቤልማይምንና የንፍታሌምን የዕቃ ቤት ከተሞች ሁሉ መቱ። 5ባኦስም በሰማ ጊዜ ራማን መሥራት ተወ፤ ሥራውንም አቍረጠ። 6ንጉሡም አሳ የይሁዳን ሰዎች ሁሉ ሰበሰበ፤ ባኦስ ይሠራበት የነበረውን የራማን ድንጋይና እንጨት አስወገዱ፤ እርሱም ጌባንና ምጽጳን ሠራበት።
ነቢዩ አናን የተናገረዉ ቃል
7በዚያን ጊዜም ባለ ራእዩ አናኒ ወደ ይሁዳ ንጉሥ ወደ አሳ መጥቶ እንዲህ አለው“በሶሪያ ንጉሥ ታምነሃልና፥ በአምላክህም በእግዚአብሔር አልታመንህምና ስለዚህ የሶርያ ንጉሥ ጭፍራ ከእጅህ አምልጦአል። 8ኢትዮጵያውያንና የልብያ ሰዎች እጅግ ብዙ ሰረገሎችና ፈረሰኞች የነበሩአቸው እጅግ ታላቅ ጭፍራ አልነበሩምን? በእግዚአብሔር ስለ ታመንህ በእጅህ አሳልፎ ሰጣቸው። 9እግዚአብሔር ልቡ በእርሱ ዘንድ ፍጹም የሆነውን ያጸና ዘንድ ዓይኖቹ በምድር ሁሉ ይመለከታሉና። አሁንም ስንፍና አድርገሃል። ስለዚህም ከዛሬ ጀምሮ ሰልፍ ይሆንብሃል።” 10አሳም በባለ ራእዩ ላይ ተቈጣ፤ ስለዚህም ነገር ተቈጥቶአልና በግዞት አኖረው፤ በዚያን ጊዜም አሳ ከሕዝቡ አያሌ ሰዎችን አስጨነቀ።
የአሳ ህመምና አማሟት (1ነገ.15፥23-24)
11የአሳም የፊተኛውና የኋለኛው ነገር እነሆ፥ በይሁዳና በእስራኤል ነገሥታት መጽሐፍ ተጽፎአል። 12በነገሠም በሠላሳ ዘጠኝኛው ዓመት አሳ እግሩን ታመመ፤ ደዌውም ጸናበት፤ ነገር ግን በታመመ ጊዜ ባለ መድኃኒቶችን እንጂ እግዚአብሔርን አልፈለገም። 13አሳም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፤ በነገሠም በአርባ አንደኛው ዓመት ሞተ። 14ለእርሱም ለራሱ በሠራው መቃብር በዳዊት ከተማ ቀበሩት፤ በቀማሚ ብልሃት የተሰናዳ ልዩ ልዩ መልካም ሽቱ በተሞላው አልጋ ላይም አኖሩት፤ እጅግም ታላቅ የሆነ የመቃብር ወግ አደረጉለት።
Currently Selected:
ሁለተኛ መጽሐፈ ዜና መዋዕል 16: አማ54
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ