አንደኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 9
9
1ስሙ ቂስ የተባለ አንድ ብንያማዊ ሰው ነበረ፥ እርሱም የአቢኤል ልጅ፥ የጽሮር ልጅ፥ የብኮራት ልጅ፥ የብንያማዊው የአፌቅ ልጅ፥ ጽኑዕ ኃያል ሰው ነበረ። 2ለእርሱም ሳኦል የሚባል የተመረጠ መልካም ልጅ ነበረው፥ ከእስራኤልም ልጆች ከእርሱ ይልቅ መልካም የሆነ ሰው አልነበረም፥ ከሕዝቡም ሁሉ ይልቅ ከትከሻውና ከዚያም በላይ ቁመቱ ዘለግ ያለ ነበረ። 3የሳኦልም አባት የቂስ አህዮች ጠፍተው ነበር፥ ቂስም ልጁን ሳኦልን፦ ከብላቴኖቹ አንዱን ወስደህ ተነሣ፥ አህዮችንም ለመሻት ሂድ አለው። 4በተራራማው በኤፍሬም አገርና በሻሊሻ አለፉ፥ አላገኙአቸውምም፥ በሻዕሊም ምድርም አለፉ፥ በዚያም አልነበሩም፥ በብንያም ምድርም አለፉ፥ አላገኙአቸውምም።
5ወደ ጹፍ ምድር በመጡ ጊዜም ሳኦል ከእርሱ ጋር የነበረውን ብላቴና፦ አባቴ ስለ አህዮች ማሰብ ትቶ ስለ እኛ እንዳይጨነቅ፥ ና፥ እንመለስ አለው። 6እርሱም፦ እነሆ፥ አንድ የእግዚአብሔር ሰው በዚህች ከተማ አለ፥ እርሱም የተከበረ ሰው ነው፥ የሚናገረውም ሁሉ በእውነት ይፈጸማል፥ አሁን ወደዚያ እንሂድ፥ ምናልባት የምንሄድበትን መንገድ ይነግረናል አለው። 7ሳኦልም ብላቴናውን፦ እነሆ፥ እንሄዳለን፥ ነገር ግን ለእግዚአብሔር ሰው ምን እናመጣለታለን? እንጀራ ከከረጢታችን አልቆአልና፥ እጅ መንሻም የለንምና ለእግዚአብሔር ሰው የምናመጣለት ምን አለን? አለው። 8ብላቴናው ደግሞ ለሳኦል መልሶ፦ እነሆ፥ በእጄ የሰቅል ብር ሩቡ አለኝ፥ እርሱንም መንገዳችንን እንዲነግረን ለእግዚአብሔር ሰው እሰጣለሁ አለ። 9ዛሬ ነቢይ የሚባለው ቀድሞ ባለ ራእይ ይባል ነበርና አስቀድሞ በእስራኤል ዘንድ ሰው እግዚአብሔርን ለመጠየቅ ሲሄድ፦ ኑ፥ ወደ ባለ ራእይ እንሂድ ይል ነበር። 10ሳኦልም ብላቴናውን፦ የተናገረኸው ነገር መልካም ነው፥ ና፥ እንሂድ አለውና የእግዚአብሔር ሰው ወዳለበት ከተማ ሄዱ። 11በከተማይቱም ዳገት በወጡ ጊዜ ቆነጃጅት ውኃውን ሊቀዱ ሲወጡ አገኙና፦ ባለ ራእይ በዚህ አለ ወይ? አሉአቸው። 12እነርሱም፦ አዎን፥ እነሆ፥ በፊታችሁ ነው፥ ዛሬ ወደ ከተማይቱ መጥቶአልና፥ ዛሬም ሕዝቡ በኮረብታው ላይ ባለው መስገጃ መሥዋዕት ማቅረብ አለባቸውና ፈጥናችሁ ውጡ። 13ወደ ከተማይቱም በገባችሁ ጊዜ መሥዋዕቱን እርሱ የሚባርክ ስለ ሆነ እርሱ ሳይወጣ ሕዝቡ ምንም አይቀምሱምና፥ ከዚያም በኋላ የተጠሩት ይበላሉና ለመብላት ወደ ኮረብታው መስገጃ ሳይወጣ ታገኙታላችሁ፥ በዚህም ጊዜ ታገኙታላችሁና አሁን ውጡ አሉአቸው። 14ወደ ከተማይቱም ወጡ፥ በከተማይቱም ውስጥ በገቡ ጊዜ እነሆ፥ ሳሙኤል ወደ ኮረብታው መስገጃ ለመውጣት ወደ እነርሱ መጣ።
15ገናም ሳኦል ሳይመጣ ከአንድ ቀን በፊት እግዚአብሔር ሳሙኤልን እንዲህ ብሎ ገልጦለት ነበር፦ 16ነገ በዚህች ሰዓት ከብንያም አገር አንድ ሰው እሰድድልሃለሁ፥ ልቅሶአቸው ወደ እኔ የደረስ ሕዝቤን ተመልክቻለሁና ለሕዝቤ ለእስራኤል አለቃ ይሆን ዘንድ ትቀባዋለህ፥ ከፍልስጥኤማውያን እጅ ሕዝቤን ያድናል። 17ሳሙኤልም ሳኦልን ባየ ጊዜ እግዚአብሔር፦ ያ የነገርሁህ ሰው እነሆ፥ እርሱም በሕዝቤ ላይ ይሠለጥናል አለው። 18ሳኦልም በበሩ ወደ ሳሙኤል ቀርቦ፦ የባለ ራእዩ ቤት ወዴት እንደ ሆነ፥ እባክህ፥ ንገረኝ አለው። 19ሳሙኤልም መልሶ ሳኦልን፦ ባለ ራእዩ እኔ ነኝ፥ ዛሬም ከእኔ ጋር ትበላላችሁና በፊቴ ወደ ኮረብታው መስገጃ ውጡ፥ ነገም አሰናብትሃለሁ፥ በልብህም ያለውን ሁሉ እነግርሃለሁ፥ 20ከሦስት ቀንም በፊት የጠፉ አህዮችህ ተገኝተዋልና ልብህን አትጣልባቸው። የእስራኤልም ምኞት ለማን ነው? ለአንተና ለአባትህ ቤት አይደለምን? አለው። 21ሳኦልም መልሶ፦ እኔ ከእስራኤል ነገዶች ከሚያንስ ወገን የሆንሁ ብንያማዊ አይደለሁምን? ወገኔስ ከብንያም ነገድ ወገኖች ሁሉ የሚያንስ አይደለምን? እንዲህስ ያለውን ነገር ለምን ነገርኸኝ? አለ። 22ሳሙኤልም ሳኦልንና ብላቴናውን ወስዶ ወደ አዳራሽ አገባቸው፥ በመርፈቂያውም ራስ አስቀመጣቸው፥ የተጠሩትም ሠላሳ ሰዎች ያህል ነበሩ። 23ሳሙኤልም ወጥቤቱን፦ በአንተ ዘንድ አኑረው ብዬ የሰጠሁህን እድል ፈንታ አምጣ አለው። 24ወጥቤቱም ጭኑንና በእርሱ ላይ የነበረውን አምጥቶ በሳኦል ፊት አኖረው። ሳሙኤልም፦ ሕዝቡን ከጠራሁ ጀምሮ እስከ ተወሰነው ጊዜ ድረስ ለአንተ ተጠብቆአልና እነሆ፥ የተቀመጠልህን በፊትህ አኑረህ ብላው አለ። በዚያም ቀን ሳኦል ከሳሙኤል ጋር በላ።
25ከኮረብታውም መስገጃ ወደ ከተማይቱ ወረዱ፥ ሳሙኤልም ለሳኦል በሰገነቱ ላይ መኝታ አዘጋጀለት፥ እርሱም ተኛ። 26ማልዶም ተነሡ፥ በነጋም ጊዜ ሳሙኤል ሳኦልን ከሰገነቱ ላይ ጠርቶ፦ ተነሣና ላስናብትህ አለው። ሳኦልም ተነሣ፥ እርሱና ሳሙኤልም ሁለቱ ወደ ሜዳ ወጡ። 27እነርሱም በከተማይቱ ዳር ሲወርዱ ሳሙኤል ሳኦልን፦ ብላቴናውን ወደ ፊታችን እንዲያልፍ እዘዘው፥ አንተ ግን የእግዚአብሔርን ቃል አሰማህ ዘንድ በዚህ ቁም አለው። ብላቴናውም አለፈ።
Currently Selected:
አንደኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 9: አማ54
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ