አንደኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 8
8
1እንዲህም ሆነ፥ ሳሙኤል በሸመገለ ጊዜ ልጆቹን በእስራኤል ላይ ፈራጆች አደረጋቸው። 2የበኩር ልጁም ስም ኢዮኤል፥ የሁለተኛውም ስም አብያ ነበረ። እነርሱም በቤርሳቤህ ይፈርዱ ነበር። 3ልጆቹም በመንገዱ አልሄዱም፥ ነገር ግን ረብ ለማግኘት ፈቀቅ አሉ፥ ጉቦም እየተቀበሉ ፍርድን ያጣምሙ ነበር።
4የእስራኤልም ሽማግሌዎች ሁሉ ተሰብስበው ወደ ሳሙኤል ወደ አርማቴም መጡና፦ 5እነሆ፥ አንተ ሸምግለሃል፥ ልጆችህም በመንገድህ አይሄዱም፥ አሁንም እንደ አሕዛብ ሁሉ የሚፈርድልን ንጉሥ አድርግልን አሉት። 6የሚፈርድልንም ንጉሥ ስጠን ባሉት ጊዜ ነገሩ ሳሙኤልን አስከፋው፥ ሳሙኤልም ወደ እግዚአብሔር ጸለየ። 7እግዚአብሔርም ሳሙኤልን አለው፦ በእነርሱ ላይ እንዳልነግሥ እኔን እንጂ አንተን አልናቁምና በሚሉህ ነገር ሁሉ የሕዝቡን ቃል ስማ። 8ከግብጽ ካወጣኋቸው ቀን ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ እኔን ትተው እንግዶች አማልክት በማምለካቸው እንደ ሠሩት ሥራ ሁሉ እንዲሁ በአንተ ደግሞ ያደርጉብሃል። 9አሁንም ቃላቸውን ስማ፥ ነገር ግን ጽኑ ምስክር መስክርባቸው፥ በእነርሱም ላይ የሚነግሠውን የንጉሡን ወግ ንገራቸው።
10ሳሙኤልም የእግዚአብሔርን ቃል ሁሉ ንጉሥን ለፈለጉ ሕዝብ ነገራቸው። 11እንዲህም አለ፦ በእናንተ ላይ የሚነግሠው የንጉሡ ወግ ይህ ነው፥ ወንዶች ልጆቻችሁን ወስዶ ሰረገለኞችና ፈረሰኞች ያደርጋቸዋል፥ በሰረገሎቹም ፊት ይሮጣሉ፥ 12ለራሱም የሻለቆችና የመቶ አለቆች ያደርጋቸዋል፥ እርሻውንም የሚያርሱ እህሉንም የሚያጭዱ የጦር መሣሪያውንና የሰረገሎቹንም ዕቃ የሚሠሩ ይሆናሉ። 13ሴቶች ልጆቻችሁንም ወስዶ ሽቶ ቀሚሚዎችና ወጥቤቶች አበዛዎችም ያደርጋቸዋል። 14ከእርሻችሁና ከወይናችሁም መልካም መልካሙን ወስዶ ለሎሌዎቹ ይሰጣቸዋል። 15ከዘራችሁና ከወይናችሁም አሥራት ወስዶ ለጃንደረቦቹና ለሎሌዎቹ ይሰጣቸዋል። 16ሎሌዎቻችሁንና ገረዶቻችሁን፥ ከከብቶቻችሁና ከአህዮቻችሁም መልካም መልካሞቹን ወስዶ ያሠራቸዋል። 17ከበጎቻችሁና ከፍየሎቻችሁ አሥራት ይወስዳል፥ እናንተም ባሪያዎች ትሆኑታላችሁ። 18በዚያም ቀን ለእናንተ ከመረጣችሁት ከንጉሣችሁ የተነሣ ትጮኻላችሁ፥ በዚያም ቀን እግዚአብሔር አልሰማችሁም። 19ሕዝቡ ግን የሳሙኤልን ነገር ይሰማ ዘንድ እንቢ አለ፦ እንዲህ አይሁን፥ ነገር ግን ንጉሥ ይሁንልን፥ 20እኛም ደግሞ እንደ አሕዛብ ሁሉ እንሆናለን፥ ንጉሣችንም ይፈርድልናል፥ በፊታችንም ወጥቶ ስለ እኛ ይዋጋል አሉት። 21ሳሙኤልም የሕዝቡን ቃል ሁሉ ሰማ፥ ለእግዚአብሔርም ተናገረ። 22እግዚአብሔርም ሳሙኤልን፦ ቃላቸውን ስማ፥ ንጉሥም አንግሥላቸው አለው። ሳሙኤልም የእስራኤልን ሰዎች፦ እያንዳንዳችሁ ወደ ከተማችሁ ሂዱ አላቸው።
Currently Selected:
አንደኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 8: አማ54
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ