አንደኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 30
30
1እንዲህም ሆነ፥ ዳዊትና ሰዎቹ በሦስተኛው ቀን ወደ ጺቅላግ በመጡ ጊዜ፥ አማሌቃውያን በደቡብ አገርና በጺቅላግ ላይ ዘምተው ነበር፥ ጺቅላግንም መትተው በእሳት አቃጥለዋት ነበር፥ 2ሴቶቹንና በውስጥዋም የነበሩትን ሁሉ ከታናሽ እስከ ታላቅ ድረስ ማርከው ነበር፥ ሁሉንም ወስደው መንገዳቸውን ሄዱ እንጂ አንድስ እንኳ አልገደሉም ነበር። 3ዳዊትና ሰዎቹም ወደ ከተማ በመጡ ጊዜ፥ እነሆ፥ በእሳት ተቃጥላ፥ ሚስቶቻቸውም ወንዶችና ሴቶች ልጆቻቸውም ተማርከው አገኙ። 4ዳዊት ከእርሱም ጋር የነበሩ ሕዝብ ድምፃቸውን ከፍ አድርገው ለማልቀስ ኃይል እስኪያጡ ድረስ አለቀሱ። 5የዳዊትም ሁለቱ ሚስቶቹ ኢይዝራኤላዊቱ አኪናሆምና የቀርሜሎሳዊው የናባል ሚስት የነበረችው አቢግያ ተማርከው ነበር። 6ስለ ወንዶችና ስለ ሴቶች ልጆቻቸው የሕዝቡ ሁሉ ልብ ተቆጥቶ ነበርና ሕዝቡ ሊወግሩት ስለ ተናገሩ ዳዊት እጅግ ተጨነቀ፥ ዳዊት ግን በአምላኩ በእግዚአብሔር ልቡን አበረታ።
7ዳዊትም የአቢሜሌክን ልጅ ካህኑን አብያታርን፦ ኤፉዱን አቅርብልኝ አለው፥ አብያታርም ኤፋዱን ለዳዊት አቀረበለት። 8ዳዊትም፦ የእነዚህን ሠራዊት ፍለጋ ልከተልን? አገኛቸዋለሁን? ብሎ እግዚአብሔርን ጠየቀ፥ እርሱም፦ ታገኛቸዋለህና፥ ፈጽመህም ምርኮውን ትመልሳለህና ፍለጋቸውን ተከተል ብሎ መለሰለት። 9ዳዊትም ከእርሱም ጋር የነበሩት ስድስት መቶ ሰዎች ሄዱ፥ እስከ ቦሦር ወንዝ ድረስም መጡ፥ ከእነርሱም የቀሩት በዚያ ተቀመጡ። 10ዳዊትም ከእርሱም ጋር ያሉት አራት መቶ ሰዎች አሳደዱ፥ ሁለቱ መቶ ሰዎች ግን የቦሦር ወንዝን መሻገር ደክመዋልና በኋላ ቀሩ።
11በበረሀውም ውስጥ አንድ ግብጻዊ አግኝተው ወደ ዳዊት ይዘውት መጡ፥ እንጀራም ሰጡትና በላ፥ ውኃም አጠጡት፥ 12ከበለሱም ጥፍጥፍ ቁራጭና ሁለት የወይን ዘለላ ሰጡት ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት እንጀራ አልበላም ውኃም አልጠጣም ነበርና በበላ ጊዜ ነፍሱ ወደ እርሱ ተመለሰች። 13ዳዊትም፦ አንተ የማን ነህ? ከወዴት መጣህ? አለው። እርሱም፦ እኔ የአማሌቃዊ ባሪያ ግብጻዊ ብላቴና ነኝ፥ ከሦስት ቀንም በፊት ታምሜ ነበርና ጌታዬ ጥሎኝ ሄደ። 14እኛም በከሊታውያን ደቡብ፥ በይሁዳም ምድር፥ በካሌብም ደቡብ ላይ ዘመትን፥ ጺቅላግንም በእሳት አቃጠልናት አለ። 15ዳዊትም፦ ወደ እነዚያ ሠራዊት ዘንድ ልትመራኝ ትወድዳለህን? አለው፥ እርሱም፦ እንዳትገድለኝ፥ ለጌታዬም እጅ አሳልፈህ እንዳትሰጠኝ በአምላክ ማልልኝ እንጂ ወደ እነዚያ ሠራዊት እመራሃለሁ አለ።
16ወደ ታችም እንዲወርድ ባደረገው ጊዜ፥ እነሆ፥ ከፍልስጥኤማውያንና ከይሁዳ ምድር ከወሰዱት ከብዙ ምርኮ ሁሉ የተነሣ በልተው ጠጥተውም የበዓልም ቀን አድርገው በምድር ሁሉ ላይ ተበትነው ነበር። 17ዳዊትም ከማታ ጀምሮ እስከ ማግሥቱ ማታ ድረስ መታቸው፥ ከእነርሱም በግመል ተቀምጠው ከሸሹ ከአራት መቶ ጕልማሶች በቀር አንድ ያመለጠ የለም። 18ዳዊትም አማሌቃውያን የወሰዱትን ሁሉ አስጣላቸው፥ ሁለቱንም ሚስቶቹን አዳነ። 19ከወንዶችና ከሴቶች ልጆች፥ ከወሰዱትም ምርኮ ሁሉ፥ ታላቅም ሆነ ታናሽም ሆነ፥ ምንም የጎደለባቸው የለም፥ ዳዊትም ሁሉን አስጣለ። 20ዳዊትም የበጉንና የላሙን መንጋ ሁሉ ወሰደ፥ ከራሱም ከብት ፊት እየነዳ፦ ይህ የዳዊት ምርኮ ነው አለ።
21ዳዊትም ደክመው ዳዊትን ይከተሉት ዘንድ ወዳልቻሉ፥ በቦሦር ወንዝ ወዳስቀራቸው ወደ ሁለቱ መቶ ሰዎች መጣ፥ እነርሱም ዳዊትን ከእርሱም ጋር የነበሩትን ሕዝብ ሊቀበሉ ወጡ፥ ዳዊትም ወደ ሕዝቡ በቀረበ ጊዜ ደኅንነታቸውን ጠየቀ። 22ከዳዊትም ጋር ከሄዱ ሰዎች ክፋዎቹና ምናምንቴዎቹ ሁሉ፦ እነዚህ ከእኛ ጋር አልመጡምና እየራሳቸው ሚስቶቻቸውንና ልጆቻቸውን ይዘው ይሂዱ እንጂ ካስጣልነው ምርኮ ምንም አንሰጣቸውም አሉ። 23ዳዊትም፦ ወንድሞቼ ሆይ፥ የጠበቀን በእኛም ላይ የመጣውን ጭፍራ በእጃችን አሳልፎ የሰጠን እግዚእብሔር በሰጠን ነገር እንዲህ አታድርጉ፥ 24ይህንስ ነገር ምን ይሰማችኋል? ነገር ግን የተዋጉትና ዕቃውን የጠበቁት እድል ፈንታ እኩል ይሆናል፥ አንድነት ይካፈላሉ አለ። 25ከዚያም ቀን ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ ይህን ለእስራኤል ሥርዓትና ፍርድ አደረገው።
26ዳዊትም ወደ ጺቅላግ በመጣ ጊዜ ለዘመዶቹ ለይሁዳ ሽማግሌዎች፦ እነሆ፥ ከእግዚአብሔር ጠላቶች ምርኮ በረከትን ተቀበሉ ብሎ ከምርኮው ሰደደላቸው። 27በቤቴል ለነበሩ፥ በራሞት በደቡብ ለነበሩ፥ 28በየቲር ለነበሩ፥ በአሮዔር ለነበሩ፥ በሢፍሞት ለነበሩ፥ በኤሽትሞዓ ለነበሩ፥ 29በቀርሜሎስ ለነበሩ፥ በይረሕምኤላውያንና 30-31በቄናውያን ከተሞችም ለነበሩ፥ በሔርማ ለነበሩ፥ በቦራሣን ለነበሩ፥ በዓታክ ለነበሩ፥ በኬብሮን ለነበሩ፥ ዳዊትና ሰዎቹም በተመላለሱበት ስፍራ ለነበሩ ሰዎች ሁሉ ላከ።
Currently Selected:
አንደኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 30: አማ54
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ