እንዲህም ሆነ፥ በዚያ ወራት ከእስራኤል ጋር ይዋጉ ዘንድ ፍልስጥኤማውያን ጭፍሮቻቸውን ለሰልፍ ሰበሰቡ፥ አንኩስም ዳዊትን፦ አንተና ሰዎችህ ከእኔ ጋር ወደ ሰልፍ እንድትወጡ በእርግጥ እወቅ አለው። ዳዊትም አንኩስን፦ አሁን ባሪያህ የሚያደርገውን ታያለህ አለው። አንኩስም ዳዊትን፦ እንግዲህ በዘመኑ ሁሉ ራሴን ጠባቂ አደርግሃለሁ አለው። ሳሙኤል ግን ሞቶ ነበር፥ እስራኤልም ሁሉ አልቅሰውለት ነበር፥ በከተማውም በአርማቴም ቀብረውት ነበር። ሳኦልም መናፍስት ጠሪዎችንና ጠንቋዮችን ከምድር አጥፍቶ ነበር። ፍልስጥኤማውያንም ተሰብስበው መጡ በሱነምም ሰፈሩ፥ ሳኦልም እስራኤልን ሁሉ ሰበሰበ፥ በጊልቦዓም ሰፈሩ። ሳኦልም የፍልስጥኤማውያንን ጭፍራ ባየ ጊዜ ፈራ፥ ልቡም እጅግ ተንቀጠቀጠ። ሳኦልም እግዚአብሔርን ጠየቀ፥ እግዚአብሔርም በሕልም ወይም በኡሪም ወይም በነቢያት አልመለሰለትም። ሳኦልም ባሪያዎቹን፦ ወደ እርስዋ ሄጄ እጠይቅ ዘንድ መናፍስትን የምትጠራ ሴት ፈልጉልኝ አላቸው፥ ባሪያዎቹም፦ እነሆ፥ መናፍስትን የምትጠራ አንዲት ሴት በዓይንዶር አለች አሉት። ሳኦልም መልኩን ለውጦ ሌላ ልብስም ለብሶ ሄደ፥ ሁለትም ሰዎች ከእርሱ ጋር ነበሩ፥ በሌሊትም ወደ ሴቲቱ መጡ። እርሱም፦ እባክሽ፥ በመናፍስት አምዋርቺልኝ፥ የምልሽንም አስነሽልኝ አላት። ሴቲቱም፦ እነሆ፥ መናፍስት ጠሪዎችንና ጠንቋዮችን ከምድር እንዳጠፋ ሳኦል ያደረገውን ታውቃለህ፥ ስለ ምን እኔን ለማስገደል ወጥመድ ለነፍሴ ታደርጋለህ? አለችው። ሳኦልም፦ ሕያው እግዚአብሔርን! በዚህ ነገር ቅጣት አያገኝሽም ብሎ በእግዚአብሔር ማለላት። ሴቲቱም፦ ማንን ላስነሣልህ? አለች፥ እርሱም፦ ሳሙኤልን አስነሽልኝ አለ። ሴቲቱም ሳሙኤልን ባየች ጊዜ በታላቅ ድምፅ ጮኸች፥ ሴቲቱም ሳኦልን፦ አንተ ሳኦል ስትሆን ለምን አታለልኸኝ? ብላ ተናገረችው። ንጉሡም፦ አትፍሪ፥ ያየሽው ምንድር ነው? አላት። ሴቲቱም ሳኦልን፦ አማልክት ከምድር ሲወጡ አየሁ አለችው። እርሱም፦ መልኩ ምን ዓይነት ነው? አላት። እርስዋም፦ ሽማግሌ ሰው ወጣ፥ መጎናጸፊያም ተጎናጽፎአል አለች። ሳኦልም ሳሙኤል እንደ ሆነ አወቀ፥ በፊቱም ተጎነበሰ፥ በምድርም ላይ እጅ ነሣ። ሳሙኤልም ሳኦልን፦ ለምን አወክኽኝ? ለምንስ አስነሣኸኝ? አለው። ሳኦልም መልሶ፦ ፍልስጥኤማውያን ይወጉኛልና እጅግ ተጨንቄአለሁ፥ እግዚአብሔርም ከእኔ ርቆአል፥ በነቢያት ወይም በሕልም አልመለሰልኝም፥ ስለዚህም የማደርገውን ታስታውቀኝ ዘንድ ጠራሁህ አለው። ሳሙኤልም አለ፦ እግዚአብሔር ከራቀህ ጠላትም ከሆነህ ለምን ትጠይቀኛለህ? እግዚአብሔርም በቃሌ እንደ ተናገረ አድርጎአል፥ እግዚአብሔርም መንግሥትህን ከእጅህ ነጥቆ ለጎረቤትህ ለዳዊት ሰጥቶታል። የእግዚአብሔርን ቃል አልሰማህምና፥ በአማሌቅም ላይ ታላቅ የሆነ ቁጣውን አላደረግህምና ስለዚህ ዛሬ እግዚአብሔር ይህን ነገር አድርጎብሃል። እግዚአብሔርም እስራኤልን ከአንተ ጋር በፍልስጥኤማውያን እጅ አሳልፎ ይሰጣል፥ ነገም አንተና ልጆችህ ከእኔ ጋር ትሆናላችሁ፥ እግዚአብሔርም የእስራኤልን ጭፍራ ደግሞ በፍልስጥኤማውያን እጅ አሳልፎ ይሰጣል።
አንደኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 28 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: አንደኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 28:1-19
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች